ትግራይ የሚገኙት የህወሓት አመራሮች ከሻዕቢያ (ከኢሳያስ መንግሥት ጋር) ሽርክና በመፍጠር ጦርነት ለመቀስቀስ እየሰሩ እንደሚገኙ የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ተናገሩ።
ሌ/ጄነራል ፃድቃን ፤ የህወሓት ሰዎች ከኢሳያስ መንግስት ጋር በማበር ጦርነት ለመቀስቀስ እየሰሩ ያሉት የወንጀል ስራዎቻቸውን ለመሸፈን እንደሆነ ጠቁመዋል።
” የወንጀል ስራዎች እና ወደ ጦርነት የተገባበት ውሳኔ እራሱ (የቀድሞው ጦርነት) accountable መሆን አለበት ” ብለዋል።
ሌ/ጄነራሉ ፥ እጅግ በጣም ብዙ የጠፉ ፣ የተሰረቁ ፣ የተዘረፉ ንብረቶች፣ ወርቅ፣ መሬት ፣ ገንዘብ እንዳለ ጠቁመዋል። በዚህ የወንጀል ተግባር ውስጥ በግልጽ የሚታወቁ ትላልቅ አመራሮች እንዳሉበት ገልጸዋል።
እነዚህ አካላት የወንጀል ስራዎቻቸውና የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎታቸው አንድ ላይ እንደተቀላቀሉ ፤ ይህን ለመከላከል ወይም ከሰሯቸው የወንጀል ስራዎች ነጻ ለመሆን የሚያስችላቸው አንዱ መንገድ #ጦርነት መፍጠር እንደሆነ እንደሚያምኑ አመልክተዋል። ለዚህም ” ከኢሳያስ መንግሥት ጋር መተባበር ነው – ፅምዶ ” ብለው እየሰሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
” የትግራይ ህዝብ እያንዳንዱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አውቆባቸዋል ” ያሉት ሌ/ጄነራሉ ፤ የትግራይ ጄኖሳይድ ኮሚሽን ባጠናው ጥናት በትግራይ ጦርነት ወቅት 75% የግፍና የወንጀል ስራዎችን የሰራው የኤርትራ ሰራዊት እንደሆነ መመላከቱን ተናግረዋል።
– ሰው የገደለው
– ሴቶች የደፈረው
– ሴቶች ማዕፀን ላይ ያልሆነ ነገር ያስገባው የኤርትራ ሰራዊት እንደሆነ ገልጸዋል።
” የአክሱም ነፍሰ ገዳይ የሻዕቢያ ወታደር ነው ፤ የማህበረ ደጎ ነፍሰ ገዳይ የሻዕቢያ ወታደር ነው ፤ የማርያም ደንገላት ነፍሰ ገዳይ የሻዕቢያ ወታደር ነው ፤ ደቡብ ትግራይ ራያ ላይ መጥቶ በመቶዎች የሚሆኑ ሰዎችን ረሽኖ የሄደው የሻዕቢያ ወታደር ነው ” ብለዋል።
ህዝቡ ይሄንና የወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎቹን ፍላጎት እንዲሁም የሚያደርጉትን ግንኙነት ስለሚያውቅ ከሻዕቢያ ጋር የሚደረግ ትብብር /ፅምዶ ” አልፈልግም ” ነው ያለው ሲሉ ተናግረዋል።
ከእነሱ ጋር በወንጀል የተሳሰረው ካልሆነ በስተቀር ህዝቡ ከኢሳያስ መንግሥት ጋር መተባበር ጥፋት እንደሚያመጣ አምኖ አልተቀበለውም ሲሉ አክለዋል።
እነዚህ ጦርነት እንዲነሳ የሚፈልጉ እና እየሰሩ ያሉ አካላት በኤርትራ ፣ በሱዳን በኩል ጥይት፣ ጠመንጃ እንደሚያስገቡ ፤ የጦር መሳሪያም እንደሚገዙ ይህንንም ሰው እንደሚያውቅ ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ተናግረዋል።
ሌ/ጄነራሉ በትግራይ ጦርነት ወቅት ጦር የመሩ፣ በኃላም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ አመራር ሆነው የሰሩ ፣ አለመግባባት ሲፈጠር ትግራይን ለቀው የወጡ አንጋፋ የትግራይ ጄነራል ናቸው።
ኤን ቢ ሲ – ኢትዮጵያ የቴሌቪዥ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ
