በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጨፋ ሮቢት ከተማ ጃራ ድልድይ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በደረሰ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 23 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
አደጋው የደረሰው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት 73290 የሆነ አውቶብስ እና ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት 41157 ተሳቢ መኪና ጃራ ድልድይ አካባቢ በመጋጨታቸው ነው ተብሏል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ዑመር መሐመድ በአደጋው እስካሁን የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልፀው 23 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ቀላል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ጠቅሰው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በጨፋ ሮቢት ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም የገለፁት ኀላፊው አያይዘውም አሽከርካሪዎች በሚጓዙበት ወቅት በጥንቃቄ ሊያሽከረክሩ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አከባቢዎች የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች መባባሳቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ አደጋዎቹ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ሲሆን አያሌ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት አስከትለዋል፡፡