“የኃይል አቅርቦት ሳይረጋገጥ ከድህነት መውጣት የማይታሰብ ነው”-
የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል ልማት መርኃ ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚና የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር በመሆኗ ለሚያስፈልጋት አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት የኒውክለር ኃይል ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረጓን ተናግረዋል።
የኃይል አቅርቦት ሳይረጋገጥ ከድህነት መውጣት የማይታሰብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም ደህንነትና ሌሎች የአለም አቀፉን የአቶሚክ ኢነርጂ ህግን የሚከተል ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሰንዶካን ደበበ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም መጀመር እና የኮሚሽኑ ወደ ስራ መገባት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ለመከታተል የወሰደችው ጠንካራ ውሳኔ ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በጤና አጠባበቅ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በምርምር ዘርፎች በማዋል የኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማሻሻልም ያለመ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በመርኃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሰንዶካን ደበበ፣ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቹዳኮቭ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
