ወንድሜን ለማታውቁት?!…

Date:


አያሌው ከበደ ተሰማ


አስፍሽ የሁለት ታላቄ ነው፡፡ በመካከላችን ጠንሽ አለ፡፡ ብዙውን የልጅነትና የወጣትነት ጊዜያችንን አብረን ነው ያሳለፍነው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ተኝተን፣ አንድ ገበታ ከበን በልተን፣ አንድ ትምህርት ቤት ተምረን፣ ለአንድ እግር ኳስ ቡድን አንድ ማልያ ለብሰን ተሰልፈንና ተጫውተን፣ በሥራ ዓለም ላይ ሆነን ደግሞ ከቤተሰብ ራቅ ብለን በሐረርጌ ክፍለ ሀገር እርሱ ለወባ ማጥፊያ ድርጅት በዋና መካኒክነት፣ እኔ ደግሞ በሐረር መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት እየሠራሁ በየሳምንቱ እየተገናኘን፣ እየተመካከርንና እየተጨዋወትን ለአንድ ዓመት ያህል አብረን ኖረናል፡፡


አስፍሽ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ በወጣትነት የፖለቲካ ሕይወቴ ስታሠርና ስፈታ በነበርኩበት በዚያ የፈተና ዘመን፣ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ዋስ ሆኖ አስፈትቶኛል፡፡ ይኸ ሁሉ ሲሆን፣ እንደታላቅ ወንድም መክሮ፣ ወድቄና ባክኜ እንዳልቀር ዘክሮና ቤተሰቦቻችን እንዳያስቡ ምስጢሩን ጠብቆና አፍኖ የፈተና ጊዜያትን ያሻገረኝ ወንድሜ ነው፡፡


አስፍሽ አደራውን የሚያከብር፣ ወጀብ የማያናውጠው፣ ቃሉን የሚጠብቅ ወኪላችን፣ አርማችን፣ የብረት መዝጊያችን፣ አድባራችን፣ ሽማግሌያችንና መካሪያችን፣ አስታራቂያችን፣ የትዕግሥት አብነታችን ነበር፡፡ የኔ አስፋው ከበደ!!!


ወንድሜን ለማታውቁት አስፋው ከበደ ይባላል፡፡  አስፋው ባሪያውም ይባል ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ዘንድ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እያለን፤
ያ አስፋው ከበደ
ያየው ሁሉ አበደ

የተባለበትም ዘመን ነበር፡፡ አስፍሽ እኮ እግሩ ወርቅ፣ እጁ ወርቅ፣ ጠባዩ ወርቅ፣ ሁለመናው ወርቅ ነበር፡፡  ታዲያ ወርቅን ማን ይጠላል?

አስፍሽ የትዳር አጋሩን እትዬ! ይላታል፡፡ ግራ ጎኑን፣ ከእግዜር የተሰጠች ረዳቱን፣ የቤት እመቤቱን፣ እህቱን፣ የልጆቹን እናት፣ መከታውን፣ አንደበቱን፣ ጠበቃውን ያከብራታል፤ ይወዳታል፡፡  እርሷም ትዳሯን አክብራ፣ ቃል ኪዳኗን ዘክራ፣ ደስታውን ተጋርታ፣ ሕመሙን ታማ፣ አንድ ቀን ሳትሰለች፣ ወንድም ሴትም ሆና ወንድማችንን እንዳመሉ ሸፍና፣ የሚቻላትን ሁሉ አድርጋ አብራው የቆመች የትዳር ቃል ኪዳን አብነት ናትና እጅግ አከብራታለሁ።

ይቻላል! ችግር የለውም ነው ቋንቋው፡፡ ሲበዛበትና ነገር ካላማረው ግን አያያይ!!! ይላል፣ ይዘጋል፡፡  እዚያ ለመድረስ ግን ዘንቦ ተባርቆ፣ ዛር ወጥቶ ተንቀጥቅጦ ነው፡፡

ልጆቹን ይወዳል፣ ያከብራል፣ ጮክ ብሎ ሲናገራቸው ሰምቼ አላውቅም፡፡ እነርሱን የሚጠራበትና የሚያናግርበት የራሱ ልዩ ቋንቋ አለው፡፡

ለምን እንደሆን ጠይቄው ባላውቅም የመጀመሪያ ልጁን ዳግማዊን፣ “ዶርዜው” ይለዋል፤ “ዳግሙ” ብሎ ያቆላምጠዋል፡፡ የሥራውን ገበሬ፣ መሀንዲሱን፣ የጥበብ ሸማኔውን ይመካበታል።

አምሳያ ልጁንና የሆድ የሆዱን የሚያጫውተውን ሣልሳዊን “ሣልስ!” እያለ ትህትና ከፍቅር፣ ሽቁጥቁጥነትን ከአክብሮት ጋር አዋርሶ ነይ እስቲ! ይለዋል በሴትኛ መስሎ፡፡ “እስቲ መላ ፈልጊ” ብሎ ዝቅ ብሎ በስስት ዓይን እያየ ፍቅሩን ምክሩንና መላውን በአንክሮ ያዳምጣል።

በወላጅ አባታችን ስም የሚያቆላምጠውን ከቤን የቤቱ ሞተር ነው ብሎ አጫውቶኛል፡፡ ፍጥነቱን፣ ቀልጣፋነቱን ያደንቅለታል፡፡ ከቤንማ መላውን፣ ሙያውንና የእጅ ጥበቡን ሁሉ አውርሶታል፡፡ በግ አርዶ፣ በልቶ፣ እሳት አንድዶ የብረት ምጣድ ጥብስ ያዘጋጀ እንደሆን አስፋውን ምስጋን ይንሳው፡፡

ዝምተኛውንና ህፃናት ወዳዱን አርክቴክት ዶዮዬ! ይለዋል፡፡ እንደ ውሃ ልክ የረጋውንና የእሺታ መለኪያውን ሮቤልን፡፡ 

የቤቴ ማዕዘን የሚላትን ሴት ልጁን ዘኒን አንስቶ አይጥግባትም፤ ካይኑ ሊያርቃት አይፈልግም፤ እርሷኮ ብሌኔ ናት ብሎኛል ስንጨዋወት፡፡

ወንድሜን ለማታውቁት አስፍሽ እኮ ፍቅር ነው፡፡ እልብ ውስጥ እንደ ሙጫ የሚጣበቅና የማይለቅ፣ የማይላቀቅ የቁም ነገር ጠበል ነው፡፡ ቃሉም ድርጊቱም የሚፈውስ ሀቀኛ ነው አስፍሽ!  ለእኔማ ልዩ ነው፡፡  ዋሴም ጠበቃዬም የአደራ ማህደሬም ነው፡፡

ልጆች ሆነን እስር እስሩ ስሄድ፣ ኳስ ስንጫወት፣ ስንሯሯጥ፣ ብስክሌት ስንነዳ፣ ዘወር በል የማይለኝ፣ በስስት ዓይን የሚያየኝ ወንድሜ ነበር፡፡  እርሱ ቀዝቃዛ እኔ ደግሞ ትኩስ፣ እርሱ ሰላማዊ እኔ ደግሞ ሞገደኛ ነበርኩ፡፡ በጣም ሳባዛው “አንተ ልጅ ለምን ረጋ አትልም? ለምን ከሰው ትጋጫለህ?” በማለት በለሆሳስ ይመክረኛል፡፡ መልሼ እንዳልቆጣ ተጨንቆና ተጠቦ ስሜቴ እንዳይጎዳ ተጠንቅቆ ይነግረኛል፣ይመክረኛል፡፡

አስፍሽ ዋና ይወዳል፤ እርሱና ጋሽ ካሣ አቃቂ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ስንማር የውሃ እናት ነበር የሚባሉት፡፡  አቃቂ ወንዝ ጢም ብሎ ሞልቶ ከድልድዩ ዘለው ይገባሉ፡፡ ደብረ ዘይት የሄድን እንደሆን ሆራ ውሃ ውስጥ ይዋኛሉ፡፡  ከደብረ ዘይት ልጆችና ከአየር ሃይል መኮንኖች ዋናተኞች ጋር ይወዳደራሉ፡፡

እኔ ዋና አልችልም፡፡ አንድ ጊዜ ሲያቀብጠኝና ከማን አንሳለሁ ብዬ አቃቂ ወንዝ ሊወስደኝ፣ ውሃ እየጠጣሁ ተደፍቄ ብቅ ጥልቅ ስል ህይወቴን ያተረፉት አስፍሽና ታዱ ወልደ አማኑኤል ነበሩ፡፡ እኔንማ ወንድሙን በስስት ዓይን ነበር የሚያየኝ፡፡ አዩ! ነበር የሚለኝ እናታችን እንደምትጠራኝ፡፡ ልጆቼንና ባለቤቴ ሳይቀር በቁልምጫ ዱኒሻ፣ ቶትሻ ጃምዬ! እያለ ተራ በተራ ይጠራቸዋል፣ ያቆላምጣቸዋል፡፡

እኔና ጠንሽ ታዲያ በልጅነታችን አስፋውን ሙጢ እንለው ነበር፡፡ ከእኛ ጋር ስለማያጠፋና ስለማይቀጣ፣ ቀልጥፎ ጥፋቱን ስለሚያምን እናብርበት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከጠንሽ ጋር ይጣላሉ፡፡ እኔ ግን እልሁ ቢኖረኝም ጉልበቴ ኩርፊያ ነበር፡፡ እስኪጨንቀው ድረስ አኮርፈው ነበር፡፡  ታዲያ ዝቅ ብሎ፣ ተለማምጦና አይለምደኝም ብሎ ይታረቀኛል፡፡

የኔታ ቤት እያለን ፊደል በስንደዶ ስንጠነቁል፣ ሀሁ! ስንል፣ አቡጊዳን ስንቀጥል፣ መልእክተ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ዘብዴዎስ ስንል፣ ፀሎተ ሃይማኖትን ስናነበንብ፣ መዝሙረ ዳዊትን ስንደግም ጨዋታ የማያታልለውና የየኔታ ልምጭ ያልነካው፣ ቁንጢጥና አለንጋ ያልጎበኘው፣ አስፍሽ! ፈሪና ሽቁጥቁጥ ነው፡፡

አብረን ተማክረን አጥፍተን፣ ጎረቤት ጣራ ላይ ድንጋይ ወርውረን፣ በባላ ባልቾ ጠርሙስና ብርጭቆ አነጣጥረን ሰብረን፣ የተቀየመ ጎረቤት ለአባታችን አቤት ብሎ ከከሰሰን የአባታችን ቁጣ ማስታገሻ አስፋው ነበር፡፡ የአባ ይባስ ከቤን የቁጣ ፈረስ ማስታገሻ የሚያውቀው እሱ ነበር፡፡  “በተሰማ ሞት”! ይላቸውና የአባታችንን ቁጣ ያበርደዋል፡፡  በጠናና በእኔ ከተጀመረ ግን አያድርስ ነው፡፡

ትንሽ ከፍ ብለን ክቡር ዘበኛ ፈረሰኛ ግቢ ፈረስ ስንጋልብ አስተማሪያችን አሥር አለቃ አሰፋ ምንዳ ነበሩ፡፡ “ቀላል ሶምሶማ ሂድ! ሶምሶማ ሂድ! ዳንገላሳ ሂድ!” እያሉ ያስተምሩናል፡፡  አሥር አለቃ አሰፋ ምንዳ መሬቱን ገለባ ያድርግላቸውና ለሽርሽር ብለው ራስ አባተ ሰፈር ይወስዱናል፡፡  የደጃዝማች መኮንን ወሰኔ ሜዳ ለጥ ያለ ነው፡፡  አስፍሽ በዚህ መስክ እምብዛም ነበር፡፡  አንድ ቀን ሸዋፈራው የተባለ ፈረስ ተመደበለት፡፡ ይህ ፈረስ ደግሞ እንደሰው የፈረሰኛን አቅም ይገምትና ይለግማል፡፡ 


አሥር አለቃ አሰፋ ምንዳ “ዳንገላሳ ሂድ!” ሲሉና ፈረሶቹ ሁሉ ከግራና ከቀኝ ሲፈተለኩ ሸዋፈራው ግን ለግሞ አልሄድም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አሥር አለቃ አሰፋ እሳት ለብሰውና እሳት ጎርሰው “ምን ይጎትትሃል?” በማለት አስፋው ላይ ጮሁበት፡፡ ከኪሱ የኤሌክትሪክ ሽቦ የማይለየው አስፍሽ ያንን ሽቦ ከኪሱ በመምዘዝ አንድ ጊዜ ፈረሱን ሾጥ ሲያደርገው፣ ሸዋፈራው ድንገት ፈትለክ ብሎ አጠበቀና ማን ያቁመው? በስንት መከራ ከግራና ከቀኝ ከበን አቆምነውና ወደ ሠፈር መልስ ሆነ፡፡

ልክ ሠፈር ስንደርስና ኮርቻችንን ከማራገፋችን በፊት፣ አስር አለቃ አሰፋ “በሉ ፈረሶቻችሁን አመስግኑና ስም አውጡላቸው” የሚል ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ በዚህ ጊዜ የአስፍሽ ተራ ሲደርስ ፈረሱን “አስቆጣኸኝ” ብሎ ስም አወጣለትና በሳቅ ገደለን፡፡ አንድ ሰሞን አስፍሽን “አስቆጣኸኝ” እንለው ነበር፡

፡ እናታችን ለአስፍሽ ስስ ልብ ነበራት “አስፍዬ እንዲህ አድርግ እንደዚያ አድርግ” ብላ ታዘው ነበር፡፡ “እስቲ የቋንጣ መስቀያ ገመድ ስቀልልኝ” ከተባለ መሰላሉን ይዞ ያንን ገመድ ይወጥርና ቋንጣ ሲሰቅልና ሲያወርድ ይውላል፡፡ ታዲያ ያኔ ልዩ ጥቅም ነበረው፡፡ እማማ ሳታየው ኪሱን ሞልቶ ይመጣና እየቆነጠረ በመብላት ያስቀናናል፡፡ ሲተኛም የተረፈውን ራስጌው ይደብቃል፡፡ ይሄኔ እኔና ጠንሽ እንማከርና ሌሊት እንቅልፍ ሲጥለው ጠብቀን የደበቀውን ቋንጣ እንወስድበትና እኛም በተራችን እየቆነጠርን ቋንጣውን በማኘክ ስናበሽቀው እንውላለን፡፡

ትንሽ ከፍ እያልን ስንሄድ አስፋው ቁመቱ ባንድ ጊዜ ተመዘዘ፣ በኳስም ስሙ መጠራት ጀመረ፤ እጣ ክፍሉና መለያው ቆዳ ማልፋት ሆነ፡፡ ገና ተፈሪ መኮንን እየተማርን ጥበበ መንክር፣ ፋሲል ዳዊትና ጌታቸው በላይነህ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የህፃናት ቡድን ተመርጠው ሲገቡ፣ በዚያን ጊዜ ሠፈራችን ክቡር ዘበኛ ካምፕ ውስጥ ይኖር የነበረው የኮሎኔል አስመሮም ረታ ልጅ ግርማ አስመሮም የአስፋው አዲሱ ጓደኛ ሆነ፡፡ ተያይዘው አስፋው ወሰን ትምህርት ቤት ካዛንችስ መሄድና መጫወት ጀመሩ፡፡

በዚያው ለዳኘው የህፃናት ቡድን ተመለመሉና መጫወት ጀመሩ፡፡ አስፋውም የዳኘው ቡድን ተጫዋች ሆነ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ጓደኞቹ ከሆኑት ከበለጠ በቀለ፣ አስራት ገብሬ፣ ነጋሽ ወደሬ፣ ተፈራ መታፈሪያና ገዛኸኝ ነዲ ጋር ተዋወቀ፡፡ ከህፃናት ቡድን ወጥቶ በዳኘው ቡድን በሁለት ቁጥር ቦታ የክንፍ ተከላካይ ሆነ፡፡ ከዚያማ ማን ይለፈው?

የጊዮርጊሱ ሸዋንግዛው ፈተና ገጠመው፤ የአየር መንገዱ ገረመው ዘርጋው ጨነቀው፡፡ አስፋው ወጥሮ ነበር የሚይዘው፡፡ ወዲያው ወደ ሸዋ ምርጥ ወዲያው ወደ ኢትዮጵያ ቡድን ተሸጋገረ፤ ቋሚ ተሰላፊ ሆነ፡፡ ከአገር አገር ሄደ፣ በእግር ኳስ ዓለምን ዞረ፡፡ በ1968 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ከተሳተፈው ቡድን ጋር ወደ ኦሎምፒክ መንደር ዘመተ፡፡

በቴሊቪዥን፣ በጋዜጣና በራዲዮ አስፋው ከበደ ገነነ፡፡ ሰለሞን ተሰማ፣ ነጋ ወልደ ሥላሴና አልፎ አልፎም ይንበርበሩ ምትኬ አስፋውን የስፖርት ዜና ማሟሻ አደረጉት፡፡ አባታችንም ተናደውና ተቆጥተው ወጣላቸው፡፡ በትምህርቱም ሆነ በሥራው አልሰነፈም፡፡ የጀመረውን አጥብቆ የመያዝ ልምድ ያለው አስፍሽ አባታችንንም እያስደሰተ፣ ትእዛዛቸውን እየፈፀመና ስማቸውንም እያስጠራ ዘለቀ፡፡

ወባ ማጥፊያ ድርጅት ሥራ ሲጀምር ግን ከቤቱ እየተመላለሰ መሥራቱ ቀረና ትንሽ ቆይቶ ወደ ድሬ ዳዋ ተዛወረ፡፡ ያን ጊዜ ከቤተሰብ ተለየ፡፡ ውሎና አዳሩ በየበረሃው ሆነ፤ የኢትዮጵያን ግዛቶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስክ ምሥራቅ አካለለ፡፡ ባንድ ወቅት የአባይን ሸለቆ በመኪና ሲሻገር ድንገት የደነበረ ፈረስ መስታወቱ ላይ ወጥቶበት ከከባድ የሞት አደጋ እጁ ክፉኛ ቆስሎ ተረፈ፡፡

የእናት አባቱ ፀሎት አወጣው እንጂ እጅግ አሰቃቂ ሁኔታ ነበር፡፡ ያም ሆኖ በሥራውም ተመሰገነና ከአንድ ዓመት በኋላ በእድገት ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ቴክኒክና አስፋው ተዋድደው ከአውቶ መካኒክነት ወደ ጀነራል ሜካኒክነት ተሸጋገረ፡፡ በተለይ የህትመት መኪና ተከላና ጥገና ልዩ ሙያው ሆነ፡፡ አዳዲስ ሞተሮችን ለመትከልና ለመገጣጠም ከሀገር ውጭ መሄድ ጀመረ፡፡

ጎረቤት ሀገር ጂቡቲ ሄዶ የማተሚያ ቤት ሞተር ተከለ፤ እዚያም ተሸለመ፡፡ በፍጥነቱና በሥራ ጥራቱ ዓለምን አስደመመ፤ ሀገሩን አስከበረ፤ አስፍሽ ገነነ፡፡ ብርሃንና ሰላም፤ ቦሌ ማተሚያ ቤት፣ አርቲስቲክና ንግድ ማተሚያ ቤትና አስፋው አንድም ሁለትም ሆኑ፡፡ ኮከብ ወዛደር፣ ኮከብ መሪ፣ ኮከብ አስተዳዳሪ ተባለ፡፡

በማኅበራዊ ህይወቱስ የተዋጣለት እንደ አስፍሽ ማናለ? ከሰው አይጣላ፣ ክፉ አይናገር፣ እንዲሁ እያለ ቀጠለ፡፡ እኔ ወንድሙ በነዚህ ረጅም ዓመታት ትውውቃችን አስፋው ከሰው ጋር ቡጢ የተሰናዘረበትን አንድ አጋጣሚ ብቻ አውቃለሁ፡፡ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ስንማር ትምህርት ቤት ሲዘጋ እየጠበቁ ጠብ የሚቆሰቁሱ አንዳንድ ሞገደኛ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አንድ መንክር የተባለ ተማሪ በዚህ ባህርይው ይታወቅ ነበር፡፡ እንዲያው ጠብ ያለሽ በዳቦ ነበር የሚለው፡፡

ታዲያ ትምህርት ቤት ተዘግቶ፣ የትምህርት ማስረጃችንን ተቀብለን፣ ከጓደኞቻችን ተሰነባብተን “ነወይ ልንለያይና ልንበታተን፤”… የሚለውን መዝሙር ዘምረን መንገዳችንን ስንቀጥል፣ ወደ ሦስተኛ ሻለቃ በሚወስደው በትምህርት ቤታችን የታችኛው በር አቅጣጫ ይዘን በመሄድ ላይ እያለን፣ መንክር ሆዬ እንደልማዱ ትንኮሳ ጀመረ፤ አስፋውን እየተከታተለ ከኋላው በሾኬ ይጠልፈዋል፤ አስፋውም ለትንኮሳው ቁብ ሳይሰጥ ዝም ብሎት ይጓዛል፤ አሁንም እየተከታተለ ይጠልፈዋል፤ እረፍ እንጂ እያለ ዝም ብሎ ይጓዛል፡፡

ይባስ አለና የትምህርት ማስረጃውን ከእጁ ላይ አስጣለውና ሪፖርት ካርዱ ውሃ ውስጥ ወደቀበት፤ ይሄን ጊዜ አስፋው በጣም ተናደደና መንፈሱ ተለውጦ መንክርን ገጠመው፤ በሁለት እጁ ተሸክሞ ከመሬት ጋር ደባለቀው፤ ከዚያ ሊለቀው ነው እንዴ? የምድር ዝላይ የምንጫወትበት በሰጋቱራ የተሞላ ሥፍራ ላይ ጎትቶ ወሰደውና ሰጋቱራውን እያፈሰ ባፉ ጎሰጎሰበት፤ መንክር ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ ሲል በስንት ገላጋይ አስፋው ከላዩ ላይ ተነስቶ ሄደ፡፡ ወሬው በትምህርት ቤቱ ሁሉ ተዳረሰ፤ አስፋው እኮ መንክርን አርመጠመጠው ተባለና ስሙ ናኘ፡፡

የአስፋው ትእግሥት ድካ የለውም፡፡ አንዳንዴ ይገርመኛል፡፡ ይህንንማ ታሪክ አወራዋለሁ፡፡ እኔም ተሳታፊ ነበርኩና፡፡ አስፍሽና የዛሬ ባለቤቱና የልጆቹ እናት ገና የተዋወቁ ሰሞን አንድ ሰው ከሥራዋ ስትወጣ እየተከተለ በጣም ያስቸግራት ነበር፡፡ ታዩ በጣም ቆንጆና የሠፈር ሁሉ መወራረጃ ነበረች፡፡ አንገቷን የደፋች ጨዋ ብትሆንም ውበቷ አይደበቅምና ተመልካቿ ብዙ ነበር፡፡

አንድ ቀን ታዲያ ይኸው ልማደኛ ሰው እየተከተለ ሲያስቸግራት ቆይቶ፣ እቤታችን ደጃፍ ሲደርሱ እኔና ጠንሽ ቆመን እየተመለከትን ይጎትታታል፤ እርሷ መንጭቃው ስትሄድም መንገድ ይዘጋባታል፤ ከዚያ እንደምንም ብላ እኛ ወደቆምንበት መጣችና ከጀርባዬ ቆመች፡፡ ሞገደኛውን ሰውዬ “ተዋት እንጂ፣ ምን አድርጊ ነው የምትላት፤ እርሷ እኮ እጮኛ አላት”አልኩት፡፡

እርሱም በትእቢት የተወጠረ ነበረና “አንተ ምን አገባህ?” ብሎ ከእኔ በስተኋላ በመራመድ ሊይዛት ሲል፣ ጠንሽ ከግራ በኩል ጆሮ ግንዱ ስር ሲያቀምሰውና መግተርተር ሲጀምር እኔ ደግሞ ተቀበልኩና በአየር ላይ አንሳፈፍኩት፡፡

በኪሱ ውስጥ ይዞት የነበረው ትንሽ ሽጉጥ መሬት ላይ ወደቀ፤ መታወቂያ ወረቀቱና ሌላም በኪሱ ውስጥ ይዟቸው የነበረው ወረቀቶች በአስፋልቱ ላይ ተበተኑ፡፡ እኔም ቶሎ ብዬ ሽጉጡንና የተበተነውን ወረቀት ለቃቀምኩና ቀጥ ብሎ ወደ መጣበት እንዲሄድ ነገርኩት፡፡ ፊቱን እየጠራረገና እየተደናበረ ቁልቁል ወደ ግንፍሌ ወረደ፡፡

አስፍሽ በዚህ ጊዜ ሁሉ ቤት ውስጥ ቆይቶ ኖሮ ማን እንደጠራው ባላውቅም ጋቢውን ተሸፋፍኖ ብቅ አለና፣ “እናንተ ሰው ልትገድሉ ነው እንዴ?” በማለት እኔንና ጠናን ለመምከር ሲሞክር፣ “እኛኮ የተጣላነው ላንተ ብለን ነው፡፡” ብንለው “እንዲያው እኮ ነው የምትደክሙት፣ እርሷ እምቢ ካለችው ህግ ባለበት ሀገር ምን ያደርጋታል?” አለና እርፍ፡፡ ታዩም ባለመናደዱ ይበልጥ ተናደደች፡፡ እንግዲህ አስፋው እንደዚህ ነው፡፡ አይበርደው አይሞቀው፣ ንዴቱንና ቁጭቱን በሆዱ አፍኖ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትዕግሥት ያልፍ ነበር፡፡

እውነቱን ኖሯል፤ ትዳር ተጀመረ፤ በልጆችም ተባረኩ፡፡ አስፋው በማረፊያው ሰዓት ግን ታመመ፤ የልጆቹን ፍሬ በሚያይበት ጊዜ ደከመ፤ ትንፋሹን የሚሰርቅ መጥፎ ደዌ ተፈታተነው፡፡ እትዬ ወደሬን ያስታመመ፣ እናታችንን እንደ ልጅ ታቅፎ የተንከባከበው አስፍሽ ታመመ፡፡

ለሌላው ያልነገረው፣ ከፈጣሪውና ከልቡ ጋር ብቻ የተማከረው ጉዳይ ይኖር ይሆን? በአንድ ቤት፣ በአንድ ግቢ ውስጥ ተወስኖ፣ አራት ግድግዳዎችና አንድ ጣራ እየተመለከተ፣ ቀንና ሌሊቱን የገፋባቸው ለሦስት ዓመታት ምንኛ ረዝመውበት ይሆን? እንደዚያ ጠንካራ የነበረ ተራራ እየሮጠ የሚወጣ እንደ ሰንጋ ፈረስ ሜዳ የማይበቃው ጀግና እግሩ ከሩጫ ተከልክሎና በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ እየተገፋ፣ ትንፋሹ እየተፈታተነው መታመም ምንኛ አስጨናቂ ነው?አስፋው እንዲህ ሆኖ ቤት ዋለ ቢሉት ከቶ ማን ያምናል? እርሱ ግን ሁሉንም ችሎ፣ ቤተሰቡንና ወዳጅ ዘመዱን እንዳያሳስብ ተጨንቆ “ይመስገነው! ደህና ነኝ!” እንዳለ ነው የፈተናውን ጊዜ ያለፈው፡፡ ሌላ ሰው ቢሆን ያብዳል፤ የባለቤቱ ጥንካሬና የልጆቹ ርብርብና እንክብካቤ የተለየ ነው፡፡

ታዩዬ እኮ ብረት ናት፡፡ የጥንካሬናየቆራጥነት ምሳሌ! አንድ ቀን ከአጠገቡ ሳይለዩ፣ እንደ ህፃን አገላብጠውና አጥበው፣ አሽሞንሙነው፣ ሳይሰለቹ በፍቅርና በአክብሮት ያስታመሙት ሁሉ ክብር ይገባቸዋል፡፡ እርሱ ዝምታውን፣ ትህትናውን፣ ክብሩንና እርጋታውን ሳይነጠቅ ወደ ፈጣሪው ሄዷል፡፡ ትቶብን የሄደውን ሃላፊነት ለመወጣትና የአደራውን ሸክም ክብደት ለመለካት አይሞከርም፡፡ በፍቅርና በትህትና የተገነባ ስብዕናን ይጠይቃል፡፡ የአስፍሽና የታዩዬን ዓይነት የቃል ኪዳን ቁርኝትንና መባረክን ይጠይቃል፡፡

እኔ በዚህ ሁሉ ዘመኔ፣ ፈጣሪውን ሳያማርርና አስታማሚውንም ሳያስቸግር ስቃዩን ውጦ ያለፈ አስፋውን የመሰለ ጀግና አላየሁም፡፡ አንድ አስፋው እንጂ ሌላ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡ ሌላም ሰው አስፋው የተሸከመውን መከራ ከቶ አይችለውም፡፡ እግዚአብሔር ፍቅርና ማስተዋሉን ይስጠን!

የአስፋው ሞት ልጅነቴን ሰርቆብኛል፤ የብቸኝነት ጥላና የባዶነት ስሜት ወርሶኛል፤ የሞትን ቅርበት፣ ድንገተኝነትና እንግዳነት አሳይቶኛል፡፡ እውነት ሞት ሌባ ነው፤ አድብቶ የሚያጠቃ! ከመድኃኔ ዓለም በስተቀር የማያሸንፈው ጠበቃ፡፡

ለቤተሰቡ፣ ለሀገሩ፣ ለወገኖቹና ለዘመድ ወዳጆቹ ጠበቃና ጥላ የነበረውን ወንድሜን ምነው ጤናውን መልሶለት ትንሽ እድሜ ቢሰጠው ብዬ በሰውኛ አስባለሁ፡፡ ፈጣሪ የሚወዳቸውን መርጦ ይወስዳል፤ አስፋውም ወደ ፈጣሪው እቅፍ እንደሄደ አምናለሁ፡፡

የእርሱ አብነት የአደራ መንፈስ ሆኖ ሁላችንም በትዕግሥትና በፍቅር፣ በመከባበርና በርህራሄ ቀሪውን የህይወት ዘመናችንን ለመግፋትና ለንስሐ ሞት ያብቃን፡፡ አሜን!!!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...

ፍልውሃ እና ሶደሬ!

ከሐዉለት አህመድ በቀደም ከብዙ ዓመታት በኋላ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ሔጄ...