የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 6 አስርት አመታት የቆየበትን ዋና መስሪያ ቤት ሊለቅ ነው፡፡ እንደአየር መንገዱ መግለጫ ወደአዲሱ ዋና መስሪያ ቤቱ በመጪው ነሀሴ ወር የሚገባ ይሆናል፡፡ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው ሲናገሩ ‹‹አየር መንገዱ ዋና መስሪያ ቤቱ በተገነባበት ወቅት ከነበረው አቅም አሁን በ20 እጥፍ አድጓል፡፡
ስለዚህም አሁን ያለበት ህንፃ ለእንቅስቃሴ ፈታኝ ሆኖብናል›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹አዲሱ ዋና መስሪያ ቤት የአየር መንገዱን የወደፊት እድገት ከግምት ውስጥ ባስገባና ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ ዲዛይን የተደረገ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይነት ሰማይ ጠቀስ ህንፃ አይደለም፡፡ ቢሆንም የአየር መንገዱን ፍላጎት የሚያሟላ ነው›› በማለት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ዋና መስሪያ ቤት ከድሮው አጠገብ የሚገኝ ሲሆን የተሰራውም በቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው፡፡
በ33500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው አዲሱ ህንፃ ስድስት እርስ በእርሳቸው የተያያዙ ህንፃዎችን ያካተተ ከመሆኑም በላይ ዋናው ህንፃ 45 ሜትር ቁመት ያለው ነው፡፡ አጠቃላይ ግንባታው 80 ሚሊዮን ዶላር እንደፈጀም ተዘግቧል፡፡
