በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በበቂ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችል አዲስ የውሃና ሳኒቴሽን አስተዳደር ሞዴል ለውይይት ቀርቧል።
በውይይቱ የፌዴራልና የክልል ውሃና ኢነርጂ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የውሃ አገልግሎት ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
መንግሥት በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 100 በመቶ የኢትዮጵያን ህዝብ በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ መግለፃቸውን ተሰምቷል።
መንግሥት ከልማት አጋሮችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በገጠርና በከተማ ከ230 ሺህ በላይ የውሃ ተቋማትን በመገንባት ከ82 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተቀናጀ ስትራቴጂና የተጠናከረ የትግበራ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ስሜ እንደተናገሩት በውሃ ፕሮጀክቶች ዕቅድ፣ ግንባታና አስተዳደር ሂደት ፣ ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት፣ የኃይልና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እያጋጠሙ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የውሃ ተቋማት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ አማራጭ የኃይል ምንጮችን በተለይም በገጠሩ ክፍል ላይ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ለዚህም የተዘጋጀው የአስተዳደር ሞዴል የውሃ ተቋማትን በወቅቱ የመጠገን አቅምን ለማሳደግ፣ የውሃ ጥራትን በተከታታይ ለመከታተል ያስችላል ነው ያሉት።
የአገልግሎት ተጠያቂነትን በማጠናከር የማህበረሰብና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎን ለማሳደግ እንደሚረዳ የገለፁት አቶ ጌትነት የውሃ አገልግሎት ተቋማትን በፋይናንስና በተቋማዊ አቅም ጭምር ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
ብስራት ሬድዮ
