ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ወልዳይ፣ የፓርቲው አባል አቶ አበበ አካሉ እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ ናቸው።
መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው መዝገብ ተጠርጣሪዎቹ «የፀጥታ አካላት ሕዝብን እየጨፈጨፉና ንብረት እያወደሙ ስለሆነ ወጣቱ ተደራጅቶ፣ ሰልጥኖና ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል» በማለት በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ሲያደራጁ እንደነበር የሚያስረዱ የቴክኒክ ማስረጃዎች ማገኘቱን አስረድቷል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ በመንቀሳቀስ አባላትን ሲመልመሉና ሲያደራጁ ነበር ብሏል።
ተጠርጣሪዎች ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የመንግሥት የፖለቲካ ፣ የወታደራዊና የፕሮፓጋንዳ ክንፍ በመፍጠር፣ የአፈጻጸም መርሃ-ግብር በማውጣትና መዋቅር በመዘርጋት ከአዲስ አበባ እስከ ክፍለ ከተሞች ባሉ የፀጥታ ተቋማት ላይ አደጋ ለማድረስ አቅደው በመንቀሳቀሳቸው ወንጀል መጠርጠራቸውን አስረድቷል።
ቀደም ሲል ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ የነበር ሲሆን ፖሊስ በተፈቀደለት የ10 ቀን ጊዜ ውስጥ ከ1 ሰው የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከተጠርጣሪዎቹ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንዲመረመሩና የቴክኒክ ማስረጃዎች እንዲሰጡት ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በደብዳቤ ጠይቆ ማስረጃዎችን ማምጣቱን አስታውቋል።
የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን ለማጣራትም ለባንኮች ደብዳቤ በመላክ የ5 ባንኮችን ምላሽ ማቅረቡን እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ በሚገኘው ሀደራ ብሔረሰብ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት የ17 ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን፣ 23 አባወራዎች መፈናቀላቸውን እና ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወድሞ መገኘቱን በማረጋገጥ በጉዳዩ ላይ የምርመራ ሥራ ማከናወኑን አብራርቷል።
ሆኖም የሌሎች ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን የምርመራ ውጤት ማጠናቀቅ እና የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መጠን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ይቀሩኛል ብሏል ፖሊስ።
ወንጀሉ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አካላት የተሳተፉበት ውስብስብ በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን ሊደልሉ፣ ሊያስፈራሩ እና የፍርድ ቤቱን ዋስትና አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ ያለው ፓሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ባቀረቡት መከራከሪያ፤ ፖሊስ ከጋሞና አርባ ምንጭ አካባቢ ማስረጃዎችን አሟልቶ ለማቅረብ በቂ ጊዜ የነበረው በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ አያስፈልገውም ብለዋል።
ባለፈው ቀጠሮ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ 300 ገጽ አካባቢ እንደሆነ ቢናገርም፣ በዛሬው ዕለት ግን መዝገቡ 50-60 ገጽ ብቻ ሆኖ መቅረቡ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ያገኘው አዲስ ማስረጃ አለመኖሩን ያሳያል ሲሉ ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለነገ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሸገር 102.1
