‹‹ትርኳሽ›› ፤ ከመንፈስ ግዞት ወደ ነፍስ አርነት የተደረገ ያልተሳካ ተጋድሎ!

Date:

ሔኖክ ገለታው

ግዮን መጽሔት :- አንዳንድ መጻሕፍት ወደ አእምሯችን ጎራ የሚሉት ለጥቂት ሰዓታት አዝናንተው፣ የዕለት ኑሯችንን ድካም አዘናግተው ለመሔድ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ጥቂት መጻሕፍት ግን እንደ ረመጥ ናቸው፤ ገና የመጀመሪያውን ገጽ ስንገልጥ በነፍሳችን ውስጥ የሕይወትን ጧፍ ይለኩሳሉ፣ ከዚያም እያበሩ ይነዳሉ፣ ታሪካቸው አልቆ ከተከደኑ በኋላ እንኳ በሕሊናችን ውስጥ እየንተንበለበሉ ማጤሳቸውን አያቆሙም፡፡ የደራሲ ሰይድ ሙህዬ አህመድ ‹‹ትርኳሽ›› የተሰኘው ረጅም ልቦለድ፣ በዚህ በሁለተኛው ምድብ ሥር የሚቀመጥ፣ ለአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ የተበረከተ የከበረና ድንቅ የብዕር ችሮታ ነው፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም በሥነ-ጽሑፍ ዓለም ውስጥ ስለነበረው የሕትመት አሻራ መረጃው ባይኖረኝም፣ በዚህ ሥራው ግን ገና በጠዋቱ የብስለትና የጥልቀት ማማ ላይ ወጥቶ፣ የነፍስን ረቂቅ ስንክሳሮች የመፈተሽ አስደናቂ ዐቅም እንዳለው በተግባር አስመስክሯል፡፡

​ይህ መጽሐፍ በተራ ተዝናኖት ወይም በውጫዊ ኹነቶች ድርደራ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ጥበባዊ ሥራ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ከሰዋዊ ማንነታችን ጋር ተለብጦ፣ በሕማማችንና በውስጣዊ ስብራታችን እውነት ላይ በጥብቅ ያጠነጠነ፣ የሰው ልጅን ሥነ-ሕላዌያዊ (existential) ቀውስና ትርጉም ፍለጋ በትልቅ መነጽር የሚመረምር የሕይወት መስታወት ነው፡፡ ታሪኩ በገጠር ቀያትና በማኅበረሰባዊ ውቅሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ገጸ-ባሕሪያት ሰብአዊ ትግል ሲተርክ፣ በተለያዩ ጊዜያትና ሥፍራዎች የሚንከራተቱት ነፍሳት የእኛኑ የጋራ ሥነ-ልቦናዊ ግዞትና ትግል የተሸከሙ የውስጣችን ነጸብራቆች ኾነው ይገለጣሉ፡፡ ደራሲውም በእነዚህ መቼቶች ውስጥ ያለውን የኖረና የነበረ የአኗኗር ልማድ፣ ወግና ባሕል እንዲሁም በኋላቀር አስተሳሰብ የሚነዱ ግትር ማኅበረሰባዊ መዋቅሮችን በጥልቀት ፈትሾአቸዋል፡፡

በዐጭሩ ‹‹ትርኳሽ›› የሰው ልጅ ወደፊት በተሻለ የሕይወት ጎዳና ላይ በነፃነት እንዳይራመድ የትኞቹ ውስጣዊና ውጫዊ ሰንሰለቶች መሠናክል እንደኾኑበት አፍታቶ የሚመሰክር፣ የነጻነትንና የፍቅርን ዋጋ በኢ-መደበኛ የአጻጻፍ ስልት የተተነተነበት ድንቅ ሥራ ነው፡፡ መጽሐፉን ስናነብ በገጸ-ባሕሪያት አቀራረጹ ረቂቅነት፣ በውብ አተራረኩ እና በምሥል ከሳች ሥልቱ እየተመሰጥን፣ የቋንቋን መግነጢሳዊ ኃይልና የቃላት ድርደራን ጥበብ በተለየ ስሜት ለመጋራት እንገደዳለን፡፡ ይህ አጭር ምልከታ፣ ‹‹ትርኳሽ›› ምን ያህል በጭቆና፣ በአጉል እምነትና በሥልጣን አዙሪት መካከል የሚደረገውን የከረመ (መልሶ መላልሶ የሚዘይረንን) ሰብአዊ ትግል እንድታዘብ ምክንያት በኾኑኝ ውሱን ነጥቦች ዙርያ የሚሽከረከር ነው፡፡ እነኾ፡-

ውሱን ሁሉን ዐወቅ እና የአንደኛ መደብ አተራረክ ስኬት

ደራሲ ሰይድ ሙህዬ አህመድ ታሪኩን ለመግለጽ የተጠቀመበት የአንደኛ መደብ አተራረክ ስልት፣ ተራ ጥበባዊ ምርጫ ሳይኾን፣ የሰው ልጅን የእውቀት ወሰንና ውስንነት የሚያሳይ ፍልስፍናዊ መንገድ ነው፡፡ ታሪኩ በአግማሴ አንደበትና አመለካከት ብቻ እንዲፈስ መደረጉ፣ አንባቢው በዕውቀት ረገድ ከገጸ-ባሕሪው ጋር አብሮ እንዲታወር ያደርገዋል፡፡ አግማሴ ያላየውንና ያልደረሰበትን እውነታ አንባቢውም ማወቅ አይችልም፡፡ ይህ ዓይነቱ አቀራረብ በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የሚፈጠረውን የጉጉትና የልብ አንጠልጣይነት ምንጭ ከራሳችን የመረጃ ‹‹ጨዋነት›› ጋር እንዲቆራኝ ያደርገዋል፡፡

ይህ የእውቀታዊ ወሰን ስኬት ሌላውና እጅግ ረቂቁ ገጽታ፣ በአግማሴ የግል ገጠመኝና የኑዛዜ ቃና ውስጥ አንባቢው የገዛ ራሱን የተሸሸገ ማንነት እንዲያይ በር መክፈቱ ነው፡፡ አግማሴ በታዳጊነት ዘመኑ ያሳለፋቸውን፣ ከሌሎች ሰዎች ደብቆ በውስጡ ያመቃቸውን ስሜቶችና ምስጢሮች በግልጽ ሲዘረግፍ (ለአብነትም እትዬ ዘርፍነሽ ቤት በነበረው አንድ አዳር በአግማሴና በአገርነሽ መካከል የነበረውን የአልጋ ላይ ውርክብ ያስታውሷል)፣ አንባቢውም ሳያውቀው ወደ ራሱ የኋላ ታሪክ ይመለሳል፡፡ ይህ የአተራረክ ስልት አንባቢው የራሱን ያረጀና የተረሳ ቁስል ‹‹ደስ ብሎት እያከከ››፣ በልጅነቱ የደበቃቸውን ፍርሐቶች፣ የፍቅር ትኩሳቶችና ያመለጡትን ውድ ዕድሎች በትዝታ መነጽር እያስታወሰ ከገጸ-ባሕሪው ጎን አብሮ እንዲሰቃይና እንዲደሰት ያደርገዋል፡፡ ተራኪው የሚናገረው ‹‹እኔ›› እያለ ቢኾንም፣ በንባብ ሂደት ውስጥ ያ ‹‹እኔ›› ተቀይሮ የአንባቢው የገዛ ሕሊና ድምፅ ይኾናል፡፡

የዚህ ‹‹ውሱን ሁሉን ዐወቅ›› ስኬት ሌላው ገጽታ፣ የሰው ልጅ ሁልጊዜም በራሱ የግል ግንዛቤ (subjectivity) እስር ቤት ውስጥ እንደሚኖር ማሳየቱ ነው፡፡ አግማሴ ስለ ትውልድ መንደሩ እንቺ ቁራሽ፣ ስለ ፍቅረኛው ስለ ፊላዬ፣ ስድብና ዱላን ‹‹ስፔሻላይዝ›› ስላደረጉት መምህራኖቹ፣ ስለ ወረዳው ሹማምንትና ነገረ ሥልጣን፣ በዐደባባይ የጎደፈ የመሰላቸውን ስምና ክብር ለመመለስ ሲሉ ልጃቸውን የማስተሰርያ በግ ለማድረግ እስከማይሳሱት ወላጆች ‹‹ጭካኔ››፣ ወዘተርፈ… የሚነግረን እውነት፣ ፍጹም እውነታ ሳይኾን እሱ በራሱ መነጽር የተረዳውን ያህል ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ አንባቢው ታሪኩን እያነበበ ሳይኾን፣ የአንድን ሰው ውስጣዊ ዓለምና ጥልቅ ስሜት አብሮ እየኖረና እየተጋራ እንዲጓዝ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪኩን ከውጫዊ ክስተቶች ተረክ ወደ ውስጣዊ የሥነ-ልቦና እውነት ያሸጋግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ ይህ የአተራረክ ስልት አንባቢው በገጸ-ባሕሪው ላይ ያለውን እምነትና ጥርጣሬ በየጊዜው እንዲመረምር ምክንያት ይኾነዋል፡፡ አግማሴ ፍቅሩንና የፍቅሩን ጦስ ሒደት ሲተርክልን፣ በዕድሜው ታዳጊነትና በራሱ ስሜት ተጽዕኖ ሥር ኾኖ (ዕድሜው ከ15 ዓመት ከፍ እንደማይል መገመት አይከብድም) የሚያጋነናቸው ወይም የሚሸሽጋቸው እውነታዎች መኖራቸውን እንድንጠረጥር እንገደዳለን፡፡ በዐጭሩ የትርኳሽ የአተራረክ መዋቅር፣ የሰው ልጅ እውነትን ፍለጋ የሚያደርገውን ጉዞ እጅግ አድካሚና ውስብስብ በማድረግ ለአማርኛችን ሥነ-ጽሑፍ ተጨማሪ በጎ የነገራ ጥበብ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

የባሕል ግዞት፣ ቤተሰባዊ አምባገነንነትና የሕልውና ትግል

‹‹ትርኳሽ›› በወረኢሉ ወረዳ ውስጥ፣ ከ‹‹እንቺ ቁራሽ›› እስከ ‹‹ኪቲላ›› መንደር፣ ከ‹‹ሰኞ አራግፊኝ›› እስከ ‹‹ወይን-አምባ›› ገበያ መካከል በፍቅር እሳት የሚለበለቡትን የሁለት ታዳጊዎችን ስቃይ ሲተርክ፣ ከጀርባው ግን ከባድ የሥነ-ሕላዌ ቀውስ (existential crisis) ያሳየናል፡፡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪው አግማሴና የሰባተኛ ክፍል ተማሪዋ ፊላዬ በፍቅራቸው ምክንያት የሚጋፈጡት እንቅፋት፣ በጥቃቅን የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በባሕላዊና በማኅበራዊ ጠፍናጊ ሥርዓቶች ውስጥ የሚያደርጉትን የሕልውና ፍለጋ ‹‹ጦርነት›› የሚወክል ነው፡፡ ፍቅራቸው ተራ የስሜት መነካካት ሳይኾን፣ በዚያ ጨቋኝና የተዘጋ ማኅበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ነጻነትና ትርጉም ለማረጋገጥ የተከተሉት ብቸኛ አማራጭ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

በአካባቢው የነበረው ወላጅና ልጅን የሚያስተሳስረው ቤተሰባዊ ሥርዓት፣ ግልጽነትና ፍቅር የጎደለው፣ ይልቁንም የአባቶችን ፍጹም አምባገነንነትና የበላይነት የሚያነግስ ነው፡፡ ወላጆች የልጆችን ስሜትና የፍቅር ምርጫ ለመረዳት ያላቸው ግትርነት፣ ግለሰባዊ ነጻነትንና ሰብአዊ መብትን ጭፍልቅ አድርጎ የሚይዝ የማኅበረሰቡ ያልተጻፈ ሕግ ነው፡፡ ታዳጊዎቹ በዚህ ጨቋኝ አመለካከት ግፊት በሚተገበሩ ሕግጋት እግር ተወርች ታስረው መላወስ ሲያቅታቸው፣ ፍቅራቸው የፍቅር ታሪክ ብቻ መኾኑ ቀርቶ በዚያ ድፍን ዓለም ውስጥ የራሳቸውን ሕልውናና ነጻነት ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ብቸኛ የተቃውሞ መሣሪያ ይኾናል፡፡

ይህ ተቃውሟቸው ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ‹‹ታቡ›› የኾኑና በምስጢርና በሀፍረት መሸፈን ያለባቸውን ማኅበራዊ ግብዝነቶች ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ታዳጊዎቹ በፍቅራቸው ውስጥ የሚከፍሉት ዋጋና የሚያሳዩት የጸና ቁርጠኝነት፣ የሰው ልጅ ለልቡ የሞላበትን እውነት ለማሳካት በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ፣ ባሕላዊ ግዞቶች የቱን ያህል ወደፊት እንዳይራመድ የሚገድቡ የሕይወት እንቅፋቶች እንደኾኑ በግልጽ ይመሰክራል፡፡

ይህ የማኅበረሰባዊ ሰንሰለት ግዞትና የሥነ-ልቦና ስብራት ደግሞ በታዳጊዎቹ ላይ ብቻ ሳይኾን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ‹‹ራሳቸውን የቻሉና የነቁ›› በሚመስሉ ትላልቅ ገጸ-ባሕሪያት ላይም  የሚንጸባረቅ እውነት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚኾነው የአግማሴ አባት የአቶ መከተ ስብዕና ነው፡፡ አቶ መከተ በእንቺ ቁራሽ መንደር ካሉ ሰዎች ለየት ያለ፣ ለስሙና ለክብሩ የሚጨነቅ፣ ማኅበረሰቡ ለሚያደርጋቸው አሉባልታና ሐሜቶች ጆሮ ዳባ የሚልና በራሱ አቋም የቆመ ጠንካራ ሰው ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህ በራሱ የቆመ የሚመስለው ሰው፣ በመጨረሻ በልጁ በአግማሴ ምክንያት ‹‹ስሜ ጠፋ፣ ክብሬ ጎደፈ›› ብሎ ሲያስብ፣ ያንን የጠፋ ስሙን ለማካካስና በማኅበረሰቡ ፊት የተበላሸውን ምስሉን ለመጠገን ሲል የጭካኔ ዱላውን ያነሳል፡፡ ከባለቤቱም ኾነ ከሚወዳት ታላቅ እህቱ የሚቀርብለትን የተማጽኖ እና የይቅርታ ድምፅ ሳይቀር አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ ልጁን ያለ ራኅራኄ ሲቀጠቅጥ ሲታይ፣ ይኸው ሰው በማኅበረሰቡ እይታ ውስጥ የቱን ያህል ታስሮ የሚኖር፣ ‹‹ነጻ ወጥቶ ፈጽሞ ነጻ ያልወጣ›› የሥነ-ልቦና እስረኛ መኾኑን በግልጽ ያሳየናል፡፡ ይህ ሁኔታ ግለሰባዊነት (individuality) ለማኅበረሰባዊ ግምት (social approval) መሥዋዕት የሚኾንበትን አሰቃቂ የክብር ባርነት ያጋልጣል፡፡

​በዚህ ሁሉ አምባገነንነትና የባሕል ሰንሰለት መካከል፣ የአግማሴ እናት የምትጫወተው ሚናም የታሪኩን ውስጣዊ ግጭት ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ እናትየው የልጇ ምስጢር ከታች፣ ገመናውን ደባቂ እና በውስጧ የምታዝንለት (የጭቆናው ተባባሪ ያልኾነች) የፍቅር መጠለያ ብትኾንም፤ የአባቱ አምባገነንነት ግን በእርሷም ኾነ በልጇ ላይ የፈጠረው ፍርሐት ነጻ እንዳይወጡ ከባድ ሰንሰለት ኾኖባቸዋል፡፡ እናት የልጇን ገመና ለመሸፈን የምታደርገው ድብቅ ተጋድሎና አባት በማኅበረሰቡ ፊት ያለውን ክብር ለማዳን የሚፈጽመው ይፋዊ ጭቆና፣ በአግማሴ ዙሪያ የተሰለፉ ሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ናቸው፡፡ እነኚህ ‹‹ገመናንና ምስጢርን በውስጥ የማቀብ ሥነ-ልቦና›› እና ‹‹ግትር አምባገነንነት›› በአንድ ጣራ ሥር የሚጋጩበት ይህ መዋቅር፣ እናትየውን የጭቆናው ሰለባ ብቻ ሳይኾን፣ ፍርሐት የሰንሰለቱ አንድ አካል እንዲኾን ያደረጋት ‹‹ድብቅ ታሳሪ›› ያደርጋታል፡፡ ይህ በቤተሰብ መዋቅር ውስጥ የሚታየው አምባገነንነትና ፍርሐት፣ ግለሰቦች ከራሳቸው ደማዊ ማንነት ሳይቀር ነጻነትን መቀዳጀት አቅቷቸው፣ በባሕልና በስም ማጥፋት ሰንሰለት ተቆልፈው የሚማቅቁበትን መጥፎ ሰብአዊ ገጽታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡

የቅዠት ሥነ–ልቦና፣ ባሕላዊ አጉል እምነቶችና የሳይንስ ቅራኔ

በታሪኩ ሂደት ውስጥ በዋናዎቹና ስሱ ገጸ-ባሕርያቱ ላይ የሚከሰተው ከባድ እና ቀላል የጤናና የሥነ ልቦና መታወክ (የፊላዬ ሕመም፣ የአባቷ የአቶ አሰፋ ደዌ፣ የአግማሴ ሐሳብና ናፍቆት የወለደው መክሳትና መጠውለግ፣ የአባቱ የአቶ መከተ አንገት መቆልመም፣ የጂን ሰብሳቢው ሚስት ሕይወት በአሳዛኝ መልኩ ማለፍ፣ የአግማሴ አክስት ፍርሓትና እርግማን፣…) በሳይንሳዊ እውነትና በማኅበረሰባዊ አጉል እምነት መካከል ያለውን ጥልቅ ገደል የሚያሳይ ፍልስፍናዊ ትንታኔን ይይዛል፡፡ ማኅበረሰቡ ለሕመም መንስኤ ብሎ የሚያስበው ሳይንሳዊውን መንገድ ሳይኾን ባሕላዊውን፣ የአጋንንት፣ የዛርና የውቃቢ እምነትን ነው፡፡ ለሕክምናውም ዘመናዊ መድኃኒትንና ኾስፒታልን ከመፈለግ ይልቅ፣ ወደ ጅኒ ሳቢዎች፣ ባሕላዊ አዋቂዎችና ወደ ድግምት ሥርዓቶች መሮጥን ይመርጣል፡፡

ይህ ባሕላዊ ሥርዓት (ritual) በማኅበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት የኖረና ከሳይንሳዊው እውቀት የላቀ ‹‹የስሜት ዋስትና›› የሚሰጥ መጠለያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ነገር ግን ይህ መጠለያ ራሱ በመጨረሻ የባለታሪኮችን ሕይወት የሚቀማ (በእኔ ዕምነት ፊላዬ የዚህ ሰለባ ናት)፣ ሰብአዊነትን የሚያሳጣና ዕጣ ፈንታቸውን የሚያጨልም የድንቁርና መጋረጃ ኾኖ ይገለጻል፡፡ ማኅበረሰቡ ከእውቀት ይልቅ ለአጉል ትውፊቶች ባለው ታማኝነት ሳቢያ፣ የንጹሐንን ሕይወት በከንቱ አሰቃይቶ ለሕልፈት ሲዳርግ ደራሲው አሳይቶናል፡፡

ደራሲው ይህንን የባሕልና የሳይንስ ቅራኔ በጥልቀት በመመርመር፣ የሰው ልጅ ለአካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ሕመሞች የሚሰጠውን ትርጓሜ ስሁትነት ይመረምራል፡፡ በሳይንሳዊ የሕክምና ዘዴዎች በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎች (ፊላዬ የሕክምና መድኃኒት መዋጥ ጀምራ እንድታቆም መደረጓን ያስታውሷል)፣ በእነዚህ ያልተገቡ አጉል ባሕሎችና ድንቁርና ሳቢያ እንዴት የሰዎችን ሕይወት እንደሚበሉና የትውልድን ዕድሜ እንደሚያሳጥሩ መጽሐፉ የመሰከረበት መንገድ የረቀቀና ልብ የሚነካ ነው፡፡ ይህ ክፍል፣ ማኅበረሰቡ ከሳይንሳዊ ግኝቶች ይልቅ በሥነ-ልቦናዊ የፍርሐት ሰንሰለት ውስጥ ተቆልፎ የሚኖርበትን እውነታ በሚገባ ያጋለጠ ነው፡፡

የታሪክና የሥልጣን አዙሪት በሽግግር ወቅት

ታሪኩ የሚያጠነጥንበት ዘመን (ከ1986 እስከ 1987 ዓ.ም) በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ የደርግ ውድቀትንና የኢሕአዴግን የሽግግር ወቅት የሚያሳይ ምዕራፍ ነው፡፡ ደራሲው ይህንን የሽግግር ወቅት ፖለቲካዊ ትዝብት በስሱና በጥበብ ሲያዋሕደው፣ የኢትዮጵያን ዝንተ-ዓለማዊ የሚመስል የታሪክ በሽታና የሥልጣን አዙሪት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ በአካባቢው ቀበሌና ወረዳ የነበሩ ባለሥልጣናት ‹‹ዘመን የማይለወጥ›› መስሏቸው በድሃው ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ግፍና ጭቆና በመጨረሻ ለውድቀታቸው ምክንያት ሲኾን እንመለከታለን፡፡

የሚያሳዝነው ግን፣ የቀደሙት ወድቀው አዲሶች ወደ ሥልጣን ሲመጡ ካለፈው ስህተት ከመማር ይልቅ፣ ያንኑ አሮጌ የአፈና መንገድና ተመሳሳይ በደል መልሰው ይተገብሩታል፡፡ ይህ ሁኔታ፣ ግሪካውያን በሲሲፎስ አፈ-ታሪክ ውስጥ እንደሚገልጹት፣ አንድን ከባድ ድንጋይ ወደ ተራራ ጫፍ ለመግፋት ደጋግሞ የመውደቅና የመነሳት ዘላለማዊ አዙሪት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ መቼም ቢኾን እውነተኛ ነጻነትና የሥነ-ልቦና ሰላም እንዳያገኝ ያደረገውን ይህንን የሥልጣን አዙሪት ደራሲው በመጠኑም ቢኾን ጠቁሞ ያልፋል፡፡

ይህ የታሪክ እውነታ፣ ፖለቲካዊ ለውጦች የሰዎችን ውስጣዊ ስብዕናና ሥነ-ምግባር ካልቀየሩ በስተቀር፣ የባለሥልጣናት ስም መቀያየር ብቻውን ማኅበራዊ ነጻነትን ሊያመጣ እንደማይችል ያስገነዝባል፡፡ ደራሲው በገጸ-ባሕሪያቱ የዕለት ተዕለት ውሳኔዎችና በባለሥልጣናቱ መስተጋብር ውስጥ፣ የሽግግር ወቅት ኹከትና ግርግር በግለሰቦች ሕይወት ላይ የሚፈጥረውን የማይቀረውን ተፅዕኖም (የአቶ መከተ እና የፖሊሱን ጉዳይ ያስታውሷል) በጥበብ አሳይቷል፡፡ ይህ የአዙሪት ዕጣ-ፈንታ ማኅበረሰቡ ራሱን ከድህነትና ከጭቆና አውጥቶ ወደ ብርሃን እንዳይጓዝ ያገደው ሰንሰለት ኾኖ እናየዋለን፡፡

የቋንቋ ሀብት፣ አካባቢያዊ ዘዬና የቃላት መግነጢሳዊ ለዛ

የ‹‹ትርኳሽ›› መጽሐፍ ሌላው እጅግ የላቀና አስደናቂ ገጽታው፣ ደራሲው ሰይድ ሙህዬ የተጠቀመበት ጥልቅ የቃላት ሀብትና አካባቢያዊ ዘዬ ነው፡፡ ደራሲው የወረኢሉን ዙርያ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት የአነጋገር ሥልትና ቃላት በታሪኩ ውስጥ በውበት በመሸመን፣ ለአንባቢው የብዕር ገበታን አቅርቧል፡፡ እነዚህ ቃላት ተራ የቋንቋ ጌጦች ሳይኾኑ፣ የታሪኩን መቼትና የአካባቢውን ሰው ተፈጥሯዊ ማንነት በዓይነ-ሕሊናችን እንድንሥል የሚያደርጉ ድልድዮች ናቸው፡፡

ለመላው የአማርኛ አንባቢ አዲስ ሊኾኑ የሚችሉ [በመጽሐፉ የምናገኛቸው] ቃላት ታሪኩን ይበልጥ ሕያው አድርገውታል፡፡ ደራሲው እነዚህን ቃላት ከመጠቀም ባለፈ፣ በዐውድ ውስጥ ያስገባበት መንገድ አንባቢው መልዕክቱንና የአካባቢውን የአኗኗር ዘይቤ በቀላሉ እንዲረዳና ቋንቋውንም እንዲያውቅ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ጥበብ፣ ደራሲው በቃላት አማካኝነት የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር እና ማኅበራዊ ሥነ-ልቦና አዋሕዶ የሳለበትን የላቀ ክህሎት ያሳያል፡፡

ይህ ዓይነቱ የቃላት አጠቃቀም፣ ደራሲው ለአካባቢው ባሕላዊና ቋንቋዊ ቅርስ ያለውን ጥልቅ ክብር የሚያሳይ ከመኾኑም በላይ፣ መጽሐፉን ከፍ ያለ ሥነ-ጽሑፋዊ ዋጋ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ ቋንቋው ግልጽ፣ ውብ፣ እና የስሜት ሕዋሳትን ሁሉ የሚማርክ በመኾኑ፣ የደቡብ ወሎን ቀዝቃዛ አየር፣ የገበያ ውርክብና የገጸ-ባሕሪያቱን ውስጣዊ ጭንቀት እንድንጋራ ያደርገናል፡፡ ቃላቶቹ የሰዎችን ሕይወት፣ ሐዘን፣ ደስታና ስቃይ በራሱ በአገሬው አንደበት እንዲሰማ የሚያደርጉ የስሜት ሕዋሳት ኾነው ቀርበዋል፡፡

የስሜት ቁንጠጣ እና የመደምደሚያው ፍልስፍናዊ እውነታ

የ‹‹ትርኳሽ›› መጽሐፍ አተራረክና ፍሰት አንባቢን በከፍተኛ ጉጉት ሰቅዞ በመያዝ ከአንዱ ገጽ ወደ ሌላው ገጽ እያጣደፈ የሚነዳ ቢኾንም፣ የታሪኩ መደምደሚያ ግን አንባቢን ለየት ባለ የሕሊና እና የፍልስፍና አደባባይ ላይ የሚያቆም ነው፡፡ ደራሲው ታሪኩን የቋጨበት መንገድ፣ ተራ የልቦለድ ታሪኮች እንደሚያደርጉት አንባቢው (ቢያንስ ብዙኃኑ) የሚፈልገውንና የሚመኘውን ዓይነት ቀጥተኛ ፍጻሜ የሚለግስ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ አጨራረስ በሥነ-ጽሑፍ ኂስ መነጽር ሲታይ፣ ደራሲው ለአንባቢው ዝግጁ የኾነ ስሜታዊ እርካታን ከማቅረብ ይልቅ፣ በገጸ-ባሕሪያቱ ዕጣ-ፈንታ አማካኝነት ዘላቂ ማኅበራዊና ሰብአዊ እውነታዎችን እንድንመረምር የከፈተው የውይይት በር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ይህንን ፍጻሜ ማራኪና አስደሳች አድርጎ መቀበል ወይም በተቃራኒው በቁጭትና በሐሳብ መሞላት፣ ሙሉ በሙሉ ለአንባቢያኑ የግል የሕይወት ተሞክሮ፣ ምርጫና የንባብ መነጽር የተተወ ጉዳይ ነው፡፡ ታሪኩ ንጹሕና የላቀ የልጅነት ፍቅርን ውበት እያሳየን መጥቶ፣ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በሚያሳየው የተጠበቀም/ያልተጠበቀም ሁኔታ መደምደሙ፣ ለአንዳንዶች የሕይወትን አይገመቴና ድንገተኛ ተፈጥሮ የሚያሳይ እውነተኛ መስታወት ኾኖ ሊገለጥላቸው ይችላል፡፡ ለሌሎች ደግሞ፣ የገጸ-ባሕሪያቱ የሕልውና ትግልና ያሳለፉት መከራ በራሱ ትልቅ ስኬት በመኾኑ፣ ፍጻሜው ምንም ይሁን ምን የባለታሪኮቹ የጽናት ጉዞ ራሱን የቻለ ትልቅ ድልና ውበት ኾኖ ሊታያቸው ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን፣ የታሪኩ መቋጫ በመጽሐፉ ውስጥ የተነሱትን ፍልስፍናዊ እውነታዎች ይበልጥ የሚያጠነክርና የነፍስን ነጻነት የሚያረጋግጥ አዎንታዊ እሴት አለው፡፡ ደራሲው ታሪኩን በዚህ መልኩ መቋጨቱ፣ በአንድ በኩል በማኅበረሰባዊ ግዞትና በአጉል እምነቶች የተተበተበው ዓለም ያመጣውንና የመጣበትን ከባድና ፈታኝ ውጤቶች ለማሰብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግለሰቦች ይሳካም/ይክሸፍ እስከ መጨረሻው እስትንፋሳቸው ምን ያህል የራሳቸውን ምርጫና ማንነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ትግል (የአግማሴን የመጨረሻዎቹን ሳምንታት ሁለት ግዙፍ ውሣኔዎች) ክብር ሳያጎድፍ ያሳየናል፡፡ ፍጻሜው ለአንባቢው የሚሰጠው ስሜታዊ ቁንጠጣ፣ ታሪኩን አንብበን ከጨረስን በኋላም እንኳ ስለ ነጻነት፣ ስለ ፍቅርና ስለ ሰብዓዊ ዕጣ-ፈንታ በውስጣችን እንድንጠይቅ፣ እንድንከራከርና ከራሳችን ጋር እንድንወያይ የሚያደርግ ድንቅ የልቦለድ ሥራ ነው፡፡

በተገኘበት መነበቡ ይቀጥል!

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 235 ነሐሴ  2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የመልካም አዲስ ዓመት መግለጫ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ታደሰ ብሩ (ዶ/ር)

  ግዮን መጽሔት :-   ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ እንኳን ለ2019 ዓ.ም....

‹‹የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ሕዝቧ ነው›› ዶ/ር ንጉሡ ለገሠ

ግዮን መጽሔት :-  አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ...

የኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት ነፀብራቅ ...

  ግዮን መጽሔት :-   አዲስ ዓመት ሲቃረብ ስለ አዲስ...