በግዢ ሂደት ውስጥ በተደረጉ ማሻሻያዎችና የላቦራቶሪ ማረጋገጫዎች የከፋ የጥራት ችግር ያለባቸው መድኃኒቶች ከገበያ እንዲወገዱ መደረጉን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት መድኃኒት መቆጣጠሪያ መሪ አስፈፃሚና የእንስሳት መቆጣጠሪያ ዘርፍ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ከበደ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ 20 ሚሊዮን ብር የወጣበት የእንስሳት መድኃኒት የጥራት ችግር ስለነበረበት ወደ መጣበት ሀገር እንዲመለስ መደረጉን ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል። በዚሁ እርምጃ በሩብ ዓመቱ ውስጥ 114 መድኃኒቶችና ክትባቶች ተመርምረው፣ ከእነሱም መካከል 1 መድኃኒትና 3 ክትባቶች ከደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ መደረጉን ተናግረዋል።
የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻልና ጥራቱን ለማረጋገጥ ከአምራች እስከ ወደብ ቅኝት በማድረግ እና በላቦራቶሪ በማረጋገጥ፣ ጥራታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች ብቻ ወደ ገበያ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የጥራት ፍተሻውን በዲጂታል መልክ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ሥራዎች በኤሌክትሮኒክ አገልግሎትና በአንድ መስኮት አገልግሎት እየተሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የደህንነትና የጥራት ችግር ያለባቸውን መድኃኒቶች ሪፖርት የማድረግና የማስተካከል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዶክተር ሰለሞን ገልጸው፤ ከደህንነት ጋር ተያይዞ በግዢ ሂደትና በመድኃኒት ጥራት ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
