” ከ40 በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ሠርቻለሁ “

Date:

” የሰው ልጅ ያለ ሕግ ሁልጊዜም ወንጀለኛ ነው የሚሆነው ” 

ኢንጂነር ጀበል ጀማል
(የ‹‹ጀ.ጀኮን ኮንስትራክሽን›› መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር)

ግዮን መጽሔት :-   ኢንጂ. ጀበል ጀማል በፈተናዎችና በተስፋ መቁረጥ መንገዶች ውስጥ አልፈው የዛሬውን ስኬታቸውን የገነቡበት የሕይወት ታሪክ እጅግ አስደናቂና ለብዙዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተናቸውን በእስር ቤት ውስጥ ተፈትነው ካለፉ በኋላ፣ በምሕንድስና ሙያ ተመርቀው ባለፉት 13 ዓመታት በኮንስትራክሽንና በሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ስማቸውን በጉልህና በክብር መጻፍ ችለዋል።

ዛሬ ላይ በ‹‹ጀ.ጀኮን ኮንስትራክሽን›› (JJCON Construction) አሻራቸውን በከተማዋ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ላይ ያሳረፉት ኢንጂ. ጀበል፤ የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን የዘርፉን ዕድገት፣ ጥራትና ታማኝነት ለመገንባት በግንባር ቀደምትነት እየሠሩ ይገኛሉ።

​ግዮን፦ ከእስር ቤት የወጣኸው መቼ ነበር?

​ጀበል፡- ከእስር የወጣሁት በ1998 ዓ.ም መስከረም መጨረሻ አካባቢ ነው። በዚያን ወቅት እኛ የነበርንበት ማረሚያ ቤት እየፈረሰ ነበር። እኔ ስወጣ እስር ቤቱ እየፈረሰ በመሆኑ፣ እስረኞቹ ወደ ዝዋይና ሸዋ ሮቢት ይጫኑ ነበር። ያ ወቅት እኔ የማትሪክ ውጤቴን የተቀበልኩበት ጊዜ ነበር። ከዚያም የትምህርት ዘመን የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ፣ ኮሌጅ ገብቼ ‹‹Building Construction›› መማር ጀመርኩ። የሁለት ዓመት ትምህርቴን አጠናቅቄ COC ከተፈተንኩ በኋላ፣ ወደ አምስት ኪሎ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ገብቼ በሲቪል ምሕንድስና (Engineering) ለአምስት ዓመታት ተማርኩ።

​በነገራችን ላይ እኔ ባልታሰር ኖሮ አልማርም ነበር፤ ምክንያቱም በወቅቱ ጥሩ ገንዘብ አገኝ ስለነበርና በእውቀትና በገንዘብ መካከል ያለውን ልዩነት ስላልተረዳሁት፣ በዚያው ሳልማር እቀጥል ነበር። ትምህርቱን ከተማርኩ በኋላ ግን ለሲሚንቶና ለግንባታ ልዩ ፍቅር አደረብኝ። ሲሚንቶን ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርብ ያየሁት የአፍሪካ ሕብረት ሕንፃ ሲገነባ ነው፤ ምክንያቱም እስር ቤት እያለሁም እየተማርኩ አብሬ እሠራ ነበር።

ግዮን፡- ለመሆኑ በኮንስትራክሽን (በግንባታ) ዘርፍ ለመማርና ለመሰማራት ፍቅሩና ፍላጎቱ ከየት መጣ?

​ጀበል፡- እስር ቤት እያለሁ በግንባታ ሥራዎች ላይ በፎርማንነት እሠራ ነበር። በወቅቱ እዚያው እስር ቤት ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንገነባ ነበር፤ ከእነዚህም አንዱ የትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ነበር። ጠዋትና ማታ እስረኞችን ቆጥሬ የማስረክበው እኔ ነበርኩ። ጠዋት ላይ ቆጠራዬን ከጨረስኩ በኋላ ግን በቀጥታ ወደ ግንባታው ቦታ አመራለሁ።

​በአጋጣሚ ሆኖ በትምህርት ቤቱ ፕሮጀክት ሥራ ዙሪያ የነበሩት ሰዎች በጣም ደጋፊና ጥሩ ሰዎች ነበሩ። ሰዎቹ ከውጭ የመጡ ባለሙያዎች ነበሩ። በነገራችን ላይ እኔ በሙያው ሳልመረቅና ትምህርቱን ሳልማር ነበር የሕንፃ ፕላን (ንድፍ) ማንበብ የጀመርኩት። ምንም ዓይነት መደበኛ ሥልጠና ሳልወስድ መሐንዲሶቹ እያሳዩኝ ፕላን አነብ ነበር። ከዚያ በኋላ በዘርፉ ያለውን ሥራ እያደነቅኩና እየወደድኩት መጣሁ።

​በዚህም የተነሳ ‹‹ለምን በዚሁ ዘርፍ ተምሬ ሙያተኛ አልሆንም?›› ብዬ ወሰንኩ። እንዳልኩትም ለአምስት ዓመታት በምሕንድስና ትምህርቴን ተከታትዬ ተመረቅኩ፤ በዘርፉም በተቀጣሪነት ለሦስት ዓመታት ያህል ሠራሁ። ቆይቶ ግን ‹‹የራሴን ድርጅት መመሥረት አለብኝ›› በሚል በ2005 ዓ.ም የሥራ ፈቃድ አወጣሁ። የመጀመሪያውን ሥራዬንም ሳር ቤት አካባቢ ‹‹G+2›› ሕንፃ አገኘሁ።

​የቤቱ ባለቤት እንግሊዝ ሀገር የተማረና እዚያው የሚኖር ሰው ነበር። ቤቱ አንድ ቤዝመንት ያለው ‹‹G+2›› ሕንፃ ነበር። በወቅቱ ስለ ኮንትራክት ዋጋ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ሰውየው ደግሞ እጅግ ጥብቅና ስለ ሥራው ሁኔታ ከበቂ በላይ እውቀት ያለው ነበር። ይመጣና አንዱን ቢም (Beam) ተመልክቶ ‹‹ይህ ጠማማ ነው፤ አይደለም?›› ይላል፤ ‹‹አይ! ትንሽ ዘንበል ብሏል›› ስንለው በፍጹም አይቀበለንም። ያንን ሥራ የጨረስኩት በከፍተኛ ጭንቀትና ጥንቃቄ ነው። ሰውየው በጣም አስጨንቆኝ የነበረ ቢሆንም፣ ቤቷ ግን እጅግ ውብ ሆና ነው የተሠራችው። በኋላም ባለቤቱ ለነጮች አከራያት። በዚያ የሥራ ሂደት ውስጥ በከፍተኛ ጭቅጭቅና ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ማለፌ ለቀጣዩ የሥራ ሕይወቴ ትልቅ ልምድና ትምህርት ሰጥቶኛል።

​ይህ ሰው ከሸዋ ዳቦ ባለቤቶች ጋር አስተዋወቀኝ። ከሸዋ ዳቦ ቤተሰቦች አንዱ አፍሪካ ሕብረት አካባቢ አንድ የፈረሰባቸው ቦታ ነበራቸው፤ በእሱ ምትክ ‹‹G+1›› ቦታ ተሰጥቷቸው ስለነበር ጥንቅቅ አድርጌ ሠራሁላቸው። ከዚያ ቀጥሎ ወሎ ሰፈር አካባቢ ከፈረንሳይ የመጣች አንዲት ሴት ‹‹G+7›› ሕንፃ ሰጠችኝ፤ እሱንም እጅግ ያማረ አድርጌ ሠራሁላት። አጠገቡ ከአሜሪካ የመጡት አቶ ብርሃኔ የሚባሉ ባለሀብት ‹‹ሌጋሲ አፓርትመንትን›› ሰጡኝ፤ ሦስት ቤዝመንት ያለው ‹‹G+18›› ሕንፃ በጥራት ሠራሁ። ቀጥሎም ሰሚት አካባቢ ‹‹ሰንራይዝ ሪል እስቴት›› የሚባል ሁለት ‹‹G+9›› እና ሁለት ‹‹G+6›› (በአጠቃላይ አራት ፎቆችን) ሠራሁ።

​ከዚያ በኋላ ደንበኞች እርስ በእርስ እየተጠራሩ በራሳቸው ጊዜ መምጣት ጀመሩ። ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃኝ በቁርጠኝነት፣ በድፍረትና በእውቀት መሥራቴ ነው። ሥራውን ሳይወዱ ‹‹ገንዘብ አገኛለሁ›› ብሎ ብቻ መሮጥ አይገባም። ለምሳሌ እኔ በሠራሁት የሥራ መጠን ልክ በእጄ ላይ የሚገኝ ገንዘብ የለም፤ ነገር ግን ሙያውን እጅግ ስለምወደው እሁድ ቀን እንኳ ሳይት (የሥራ ቦታ) እሄዳለሁ።

​እየቆየ ሲሄድ ትልልቅ ፋብሪካዎችንና ሕንፃዎችን መሥራት ጀመርኩ። ፋብሪካ ሲባል መጋዘን መገንባት ብቻ አይደለም፤ ፋብሪካ ውስጥ የሚተከለው ማሽን የቦልት ማሰሪያዎች ጭምር አንድ ሚሊሜትር ዝንፈት ሳይኖራቸው በትክክል እንዲገጠሙ አዘጋጅቶ መሥራት ማለት ነው። ማሽኑ ከውጭ በቀጥታ ሲመጣ ቦታው ላይ በትክክል መሰካት አለበት። በዚህ መንገድ ከአራት በላይ ትልልቅ ፋብሪካዎችን ገንብቻለሁ።

​ግዮን፡- በ2005 ዓ.ም የመጀመሪያውን የሥራ ፈቃድ ስታወጣ ደረጃው ስንት ነበር?

​ጀበል፡- ደረጃ ስምንት (GC-8) ነበር፤ የድርጅቴም ስም ‹‹ጀበል ጀማል ጄነራል ኮንትራክተር›› ይባል ነበር። ያኔ ከፍ ያለ ደረጃ የሚጠይቅ ሥራ ሲመጣ በጓደኞቼ ፈቃድ ተጠቅሜ እሠራ ነበር።

​ግዮን፡- ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የሪል እስቴት ሥራ ሳትጀምር በነበሩት 13 ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ሥራዎችን አከናውነሃል?

​ጀበል፡- የሕንፃ እድሳቶችንና የቪላ ቤቶችን ሳይጨምር፣ ከ40 በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ሠርቻለሁ። ለምሳሌ በፋብሪካ ደረጃ አዳማ የሚገኘውን የሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ፣ ኒው ፍላወር እስፖንጅ ፋብሪካን፣ የረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት ፋብሪካን፣ ሌጋሲ አፓርትመንትን፣ ብራ ታወርን፣ ሰንራይዝ ሪል እስቴትን፣ ሀያ ሁለት አካባቢ የሚገኘውን ‹‹G+8›› ታወርን፣ ጃክሮስ አቅራቢያ የሚገኘውን የደብል ኤስ ቢዝነስ ግሩፕ ሁለቱን ሕንፃዎችና ሌሎችንም መጥቀስ እችላለሁ።

​አንዳንዴ የሠራሁትን ሥራ መጠን ወደ ገንዘብ እቀይረውና ‹‹ገንዘቡ ወዴት ገባ?›› ብዬ እጠይቃለሁ። እኔ ግን ወደዚሁ ሥራ ስገባ ሙያውን ወድጄ በመምጣቴ ስለ ገንዘቡ ብዙም አልጨነቅም ነበር። ነገር ግን በርካታ ሥራዎች በሚኖሩበት ጊዜ ገንዘብን በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ገንዘብ ከአንዱ ፕሮጀክት ወደ ሌላው ስለሚወጣ፣ ሥራው ካለቀ በኋላ ባዶ እጅ የመቅረት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይሄ የሚሆነው ደግሞ የወጪና ገቢ ሂሳብ በአግባቡ ስለማይመዘገብና የአንዱ ፕሮጀክት ገንዘብ ለሌላው ስለሚውል ነው።

​እኔ የምመክረው እያንዳንዱ ፕሮጀክት የራሱ የተለየ የባንክ ሂሳብ (Account) ኖሮት፣ በራሱ ሂሳብ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ነው። ከእያንዳንዱ ፕሮጀክት የሚወጣው ወጪ፣ እንዲሁም ትርፍና ኪሳራው በግልጽ መታወቅ አለበት። ይህንን መሠረታዊ እውነት ለመረዳት እኔ አሥር ዓመታት ወስዶብኛል! የሠራሁላቸው ሰዎች ሁሉ ስለ ሥራዬ ጥራት ቢያመሰግኑኝም፣ የእኔን ትርፍና ኪሳራ ግን የሚያውቅልኝ አልነበረም። ለምሳሌ በቅርቡ ከአሥራ አንድ በላይ ፕሮጀክቶች ነበሩኝ፤ የአንዱን ዋጋ ለሌላው እያደረግን አደባልቀን ስለምንሠራ፣ ትርፍና ኪሳራው በወጉ ሳይለይ ነው ልናጠናቅቅ የቻልነው።

​ሌላው ትልቅ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ የታክስ (የግብር) ጉዳይ ነው። ታክስ ደግሞ ወጪው ተከናውኖ ሕጋዊ ደረሰኝ ካልተሰበሰበበት ዋጋ የለውም። ​እኔ በታክስ ጉዳይ ሁልጊዜ ተቀጪ ነበርኩ፤ በቅርቡም በዚህ ዙሪያ ከባድ ችግር ገጥሞኝ ነበር። ይሁን እንጂ በታክስ ጉዳይ የገጠመኝ ችግር መንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በገቢዎች ባለሥልጣን አማካኝነት የመጣ ችግር አይደለም። ችግሩ የገጠመኝ ከራሴ የሰነድና የሂሳብ አያያዝ ግድፈት በመነጨ ነው፤ በፍጹም ‹‹ገቢዎች እንዲህ አደረገኝ›› ብዬ መናገር አልችልም። የአብዛኞቻችን ችግር የራሳችን የአሠራር ድክመት ነው።

​የሂሳብ ሠራተኞቻችን (አካውንታንቶች) እንኳ ሳይቀሩ ባለቤቶችን በትክክል አይመሩም። ምክንያቱም የባለቤቱ የገንዘብ አወጣጥ ሥርዓት ምን እንደሚመስል በሚገባ መቆጣጠር ይችላሉ፤ በዚያ ዘርፍ ከባለሀብቱ ይልቅ የተሻለ እውቀት አላቸው። ‹‹ይህንን አድርግ፤ ያንን አታድርግ›› ማለት ይችላሉ። ነገር ግን ባለቤቱ ኢ-ሥርዓታዊ (ሕጋዊ ያልሆነ) ግዢ ሲፈጽም ዝም ይላሉ፤ ችግር ሲፈጠር ግን ተጠያቂው ባለሀብቱ እንደሆነ ያውቃሉ።

ግዮን፡- ለ13 ዓመታት ያህል በኮንስትራክሽን ዘርፍ ቆይተህ፣ አሁን ወደ ሪል ስቴት አልሚነት ለመሸጋገር ምን አነሳሳህ?

ጀበል፡- እኔ ባለፉት ዓመታት ከሠራኋቸው ግንባታዎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሪል ስቴት ዓይነት አፓርትመንቶች ናቸው። ቀደም ሲል በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት የሚያገኙትን ትርፍ እመለከት ነበር፡፡

​ያም ሆኖ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደዚህ ዘርፍ የገባሁበት ዋናው ምክንያት በከተማችን አዲስ አበባ የተከሰተውን ከፍተኛ የቤት እጥረት በመመልከቴ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የሥራውን 80 በመቶ ያህል በቅርበት ስለማውቅ ነው።

​በተለይም በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ አካላት ሥራውን በአግባቡና በባለሙያ ሳያከናውኑ፣ የሰውን ገንዘብ እየሰበሰቡ የመሬት ንግድ ላይ ብቻ ትኩረት ያደርጋሉ። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን መሬት መቸበችብ አይቻልም። በነገራችን ላይ ቤትን የሚያክል ትልቅ ሀብት ገንብቶ ለሰው ማስረከብ ቀላል ነገር አይደለም።

​በሌላ በኩል እኔን ወደዚህ የሥራ ዘርፍ ያሳበኝ ትልቁ ምክንያት የኮንስትራክሽን ሥራ እጅግ አድካሚና አሰልቺ ሲሆን፣ የሪል ስቴት ልማት ግን በአንጻሩ ቀላልና አትራፊ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ በሀገራችን ያሉ በርካታ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችና ኮንትራክተሮች ከፍተኛ ገንዘብ ያንቀሳቅሳሉ፤ ነገር ግን ሕይወታቸው አይቀየርም። ምናልባት ውድ መኪና ሊነዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን መኪናው የነሱ አይደለም። ምክንያቱም በርካታ ፕሮጀክቶችን ይይዛሉ፣ ሥራው እጅግ አድካሚ ነው፣ የሂሳብ መደባለቅ አለ፤ በመጨረሻም ሥራው ተጠናቆ ወጪና ገቢ ሲሰላ ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ።

​ለዚህ ውድቀት የሚዳርጋቸው ደግሞ ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት ገቢና ወጪን በሥርዓት አለመያዝ፣ እንዲሁም ከታክስና ከግብር ሥርዓቱ ጋር በሚገባ አለመተዋወቅ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባን የገነቧት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች ናቸው። እነዚህ ኮንትራክተሮች ታዲያ አሁን የት አሉ? በምንስ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የሀብት ሁኔታቸውስ ምን ይመስላል? ብለን ስንጠይቅ መልሱ የሚያስዝን ነው የሚሆነው።

​ኮንትራክተር ኪሱ ቀዳዳ ነው፤ በየቦታው ገንዘቡን እያፈሰሰ ነው የሚሄደው። ገንዘቡን ባፈሰሰበት ቦታ ሁሉ ደግሞ ሕጋዊ ደረሰኝ አይሰበስብም። በዚያ የተነሳ የመንግሥት የታክስ ባለዕዳ ይሆናል። ​አንድ ጊዜ ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስለ ገንዘብ አያያዝ ሲናገሩ ‹‹እኔ ሳንቲሞችን እጠብቃለሁ፤ ብሮች ደግሞ እርስ በእርሳቸው ይጠባበቃሉ›› ብለው ነበር። እውነት ነው፤ ምክንያቱም በትላልቅ ብሮች ላይ ዝም ተብሎ ቼክ አይፈረምም። ነገር ግን አነስተኛ ሳንቲሞችንና ብሮችን በየሰዓቱ ስንበትናቸው እንውላለን።

​ብዙ ኮንትራክተሮች ለኪሳራ የተዳረጉት ቅድመ ክፍያ (“Advance Payment”) በሚሰጣቸው ገንዘብ ምክንያት ነው። የቅድመ ክፍያ ገንዘብ ተቀብለው ዱባይ የሚሄዱና ውድ መኪናዎችን የሚገዙ በርካታ ኮንትራክተሮች ነበሩ፤ መጨረሻቸው ግን ኪሳራ ነበር።

​ግዮን፡- ወደ ሪል ስቴት ዘርፉ ስትመጣ ችግሮቹን በአግባቡ ለይተህ እንደመሆኑ መጠን፣ ከእኔ ምን ይጠበቃል ትላለህ?

​ጀበል፡- እኔ ወደዚህ ሥራ የገባሁት አስቸጋሪና መጥፎ በሚባል ወቅት ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት የተገነባ ቤት እንኳን በቀላሉ አይሸጥም፤ ከዚያም በላይ አሁን ባለው ሁኔታ የዓለም ኢኮኖሚ የደከመበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የሕዝቡም የመግዛት አቅም እጅግ ተዳክሟል። በአጠቃላይ በርካታ ተደራራቢ ፈተናዎች አሉ።

​ነገር ግን ሥራችንን በትክክልና በታማኝነት ከሠራን ነገ ሌላ አዎንታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ቀደም ስህተቶቼ ተምሬአለሁ። እኔ አሁን አፓርትመንት ስሸጥ ያገኘሁትን ገንዘብ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ አልፈልግም፤ መልሼ እዚያው ፕሮጀክቱ ላይ ማዋል ነው የምፈልገው። በወቅቱ ገንዘቡ ፕሮጀክት ላይ ካልዋለ፣ ብድርም ሳይከፈል ቀርቶ ከባድ ኪሳራ ያጋጥማል። በኪሳራ ምክንያት ደግሞ ቤተሰብ ይበተናል።

​አሁን በሪል ስቴት ዘርፍ ያሉ ችግሮች በጊዜ ሂደት ይፈታሉ ብዬ አስባለሁ። አሁን ላይ የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች) እንኳን ለሪል ስቴት አልሚዎች የብድር አቅርቦት አይሰጡም። መንግሥት ግን ይህንን ችግር ለመፍታት እያሰበበት ያለ ይመስለኛል።

​በሪል ስቴት ሥራ ላይ የግንባታ ግብዓትን በአግባቡ መጠቀም፣ ወጪና ገቢን በሥርዓት መመዝገብ ከተቻለ ዘርፉ በፍጹም አክሳሪ አይደለም። አሁን ዘርፉ በአዋጅና በሕግ የተደገፈ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ግን ግለሰቦች በዘፈቀደ ነበር የሚሠሩት፤ ለዚያም ነበር ገንዘብ ሰብስበው መሬት የሚቸበችቡት። አሁን ግን ጥብቅ ሕግ ወጥቷል።

​የሰው ልጅ ያለ ሕግ ሁልጊዜም ወንጀለኛ ነው የሚሆነው። ሌላው ቀርቶ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን እንኳን እኛን ለዚህ ስቃይ የዳረጉን ‹‹አድርጉ/አታድርጉ›› ተብለው የተሰጣቸውን ሕግ ተላልፈው ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ ሁልጊዜም የሕግ ገደብና ሥርዓት ያስፈልገዋል።

​–

ማስታወሻ፡- ውድ የግዮን አንባቢያን ከኢንጂ. ጀበል ጀማል ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ በቀጣዩ  ቆይታችንንና ከእርሳቸው ጋር አብረው የሠሩ ባልደረቦቻቸውንና የዘርፉ ተቋማት አመራሮች ምሥክርነትን አካተን የምንመለስ ይኾናል፡፡  

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 237 ጥቅምት  2019 ዓ.ም

 

 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ቢል ጌትስ ስለ AI አጠቃቀማችን ምን አሉ?

የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ሮቦቶች...

ዲቪ ሎተሪ 2027 ዳግም እንዳይከፈት በፍርድ ቤት ታገደ

የአሜሪካ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የዲቪ ሎተሪ 2027 ምዝገባ...

የማይደበዝዝ የታሪክ አሻራ፤

አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ በዓለም መድረክ ግዮን መጽሔት :-...

በብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ለስድስት ወር በደብረ ሊባኖስ ገዳም እንዲቆዩ ተወሰነ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ...