የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስላማዊቷ ሪፐብሊክ ላይ የቀረውን ሁሉ “እናጠፋዋለን” በማለት ከዛቱ በኋላ ቴህራን ለዋሺንግተን ኒውክሌርን በሚመለከት የስምምነት ሀሳብ መላኳ ተገለጸ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ምክረ ሃሳቡ በኳታር በኩል ለዋሽንግተን የተላለፈ ሲሆን፣ አሜሪካ የቴህራንን ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላች በኋላ ብቻ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ዋሽንግተን ሀሳቡን እየገመገመች እንደሆነ ለሮይተርስ የተናገሩ ቢሆንም፣ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።
የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊ ሞህሴን ሬዛኢ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ “ዲፕሎማሲን በሚመለከት ለአሜሪካ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አሳውቀናል።
እነዚህን ሰባቱን መስፈርቶች ተግባራዊ እስካላደረጉ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን አንከፍትም፣ እንዲሁም ወደ ድርድር አንገባም” ብለው ነበር።
የኢራን ቅድመ ሁኔታዎች እስካሁን ድረስ በይፋ ባይገለጹም፣ በካህሌጅ ታይምስ በመባል የሚታወቀው መገናኛ ብዙኃን ባወጣው ዘገባ መሠረት ቴህራን ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሊባኖስን ጨምሮ በክልሉ ያሉ ግጭቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ፣ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የባሕር ኃይል እገዳ እንድታነሳ፤ በኢራን ላይ የተጣሉ የአሜሪካ ማዕቀቦች እንዲነሱ፤ የኢራን በውጭ የታገዱ ንብረቶችና ገንዘቦች እንዲለቀቁ፤ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጦር እነድትቀንስ፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ እንዲከፈል፣ በኢራን ግዛት ላይ የሚፈጸሙ የአሜሪካ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚሉ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ ዋሽንግተን ማንኛውም የመጀመሪያ ዙር ድርድር የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ጉዳይ ማካተት እንዳለበት ገልጻለች። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ማንኛውም ስምምነት ላይ ለመደረስ የኒውክሌር ጉዳይ አንዱ ዋና የውይይት አጀንዳ እንደሚሆን ያመለክታል።
ይህ የኒውክሌር ስምምነት ሀሳብ የቀረበው፣ በአሜሪካና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫዎች በኋላ እንደገና ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በተጠናከረበት እና አደራዳሪዎች ግጭቱን ለማስቆም ጥረታቸውን ባጠናከሩበት ወቅትነው።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫው በኋላ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንደገና ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ያላስተባበሉ ሲሆን በሌላ በኩል ኢራንም ጦርነቱ እንደገና ከተቀሰቀሰ ጠንካራ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት ማቀዷ ተነግሯል።
አሜሪካና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ በኢራን ላይ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ፣ ኢራን በበኩሏ በእስራኤል እና የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚያስተናግዱ የባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
ግጭቱ ወደ ሊባኖስ ተስፋፍቶ በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል። በቅርቡ ደግሞ ቀውሱ ወደ የመን ተሻግሮ ከኢራን ጋርየሚቀራረቡት የሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በሚገኙ የኃይል ማመንጫ ተቋማት፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተዘግቧል።
