ይድረስ ካገሬ ኢትዮጵያ የፌደራልና ክልሎች ባለስልጣናት!

Date:

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአንድ ወቅት ሚዲያ ላይ የተናገሩትና እንደ ዋዛ ያለፍነው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ እናም እንደገና ማሳታወስ ፈለኩ፡፡

“አንድ ጊዜ ደርግ ጽ/ቤት ተጠርቼ ከመንግሥቱ ኃ/ማርያም ጽ/ቤት ገባሁ፡፡ እኔም እንዲህ አልኩት፡-     

      ‘ሊቀመንበር መንግሥቱ ያንተና የመንግሥታችሁ ሥራና ታሪክ ዛሬ በአዲስ ዘመንና በሠርቶ አደር ጋዜጣ ላይ እንደሚፃፈው ላይሆን ይችላል፡፡ እውነተኛና ሀቀኛ ታሪካችሁና ተግባራችሁ የሚፃፈው በሚመጣው ዘመንና ትውልድ ነው!’  አልኩት” ብለው እንደተናገሩ ያስታውሳሉ፡፡ 

የፕሮፌሰር ምክረ ሀሳብ በወቅቱ ሰሚ ባያገኝም ኋላ ላይ እውነት ሆኖ ታዝበናል፡፡ በአዲስ ዘመንና በሠርቶ አደር ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ‹ቆራጡ አብዮታዊ መሪ፤ መንግሥታቸውን ደግሞ ተራማጅ፣ ለጭቁኖች የቆመ፣ ሶሻሊስት› ብለው ቢያንቆለጳጵሱትም ሥርዓቱ ሲወድቅ ኮሎኔል መንግሥቱን ‹ጨካኝ› መንግሥታቸውም ‹ሰው በላ፣ ፀረ ደሞክራሲ› ተባለ፡፡ ኢህአዴግም እንደዚያው ሆነ፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ፣ እፎይታ መፅሔት፣ ዋልታና ፋና እንደዘገቡት ሳይሆን ‹ዘረኛና ከፋፋይ› ዘመኑም ‹የ27 ዓመት ጨለማ ዘመን› ተብሎ ተበየነ፡፡

 

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ታሪክም አሁን ላይ ፋናና ኢቢሲ  እንደሚዘግቡት ላይሆን ይችላል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሥርዓቱ አፈቀላጤዎችና ራሳቸውን ‹አክቲቪስት› ብለው የሚጠሩት እንደሚፅፉትና እንደሚያደንቁት ላይሆን ይችላል፡፡ እውነተኛው የመንግሥት ታሪክ የሚፃፈው ለተረኛዉ ሲያስረክብና ኃይልና ስልጣን ከእነርሱ ስትርቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሲሆኑ ዘግይቶ ነው፡፡ 

ታሪክ የፍትህ ሚዛን ላይ ሲያስቀምጥህ እርቃንህን ነው፡፡ በብዙ አጀብና የፀጥታ መዋቅር የጠበከው ምሥጢር በአደባባይ ይዘከዘካል፡፡ ምሥክር ይሆኑ ዘንድ በየጫካው በግፍ የተገደሉ የሙታን ድምፅ ግዘፍ ነስቶ ይመጣል፤ እስረኞች እስከ ቂማቸው ይፈታሉ፤ የተሰደዱና የተፈናቀሉ እስከቁጣቸው ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዘመን ከድቶት ብቻውንና እርቃኑን ለሚቆመው መንግሥታዊ ተግባርህ ተፋራጅ ይሆናሉ፡፡ ኘሮፌሰር መስፍን በመፅሐፋቸው እንደገለፁት ‹አድፋጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ› ከየጎሬው ወጥቶ ‹ሌባ ሌባ› ይልኻል፤ እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ ሊወግርህ ይከብኻል፡፡ እናም በወጣትነትህና በጎልማሳነትህ ከነሙሉ ኃይልህና ክብርህ ጋር የሠራኸው ግፍ በኋላ ዘመንህ በሌለህ ጉልበት እንደ መርግ ላይህ ላይ ይጫንብሃል፡፡ ዳፋው ካንተ አልፎ ለልጅ ልጆችህና ለቤተሰቦችህም ይተርፋል፡፡ ታሪክ ለፍርድ ሲያቆምህ ማንገራገር፣ ማስተባበል፣ ማስተካከልም እንዳትችል በአበቃ ጊዜህ ላይ ይሆናል፡፡

 

እናም የሀገሬ ባለስልጣናት ወንድሞቼና እህቶቼ ዛሬ በሚቀርብላችሁ ውዳሴና የተጋነነ ክዋኔ ሪፖርት እንዳትታለሉ፡፡ ይልቁንም ከሚተቿችሁና ከሚነቅፏችሁ ይልቅ አብዝተው ከሚያወድሷችሁና ከሚያሸበሽቡላችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ግፍን ፍሩ፤ የሕዝብን ብሶትናምሬት አዳምጡ፤ የሆነ ቦታ በሆነ ተግባር ቢሳካላችሁ እንኳን ትሩፋቱ ለሁሉም ሕዝብ ስለማይደርስ ተስፋ ለጣው ህብረተሰብ ሞራል ተጨነቁ፡፡ አቅመ ቢስ ዜጎችን ከጥቃት ተከላከሉ፡፡ የዜጎችን ሞት እንደተራ ክስተት አትቀበሉ፡፡ ምናልባት በመረጃ ክፍተትና ባቅም ማነስ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲደርስ እንደ ሰው ወጥታችሁ ኃዘናችሁን  ግለጡ ቢቻል በአካል ተገኝታችሁ የተጎጂ ቤተሰቦችን አፅናኑ፤ እንደ መንግሥት ቁጭታችሁን  በግልፅ ቋንቋ ግለፁ  እንጅ የቃላት ቁማር አትጫወቱ፡፡ 

ያከናወናችሁትን ስኬት በልኩ ግልጹ፤ ችግራችሁንም በግልፅ ለህዝብ አስታውቁ፤ ድክመታችሁን አምርራችሁ ፈትሹ፡፡ በህዝብ ላይ ለደረሰ ጥፋት እስከመጨረሻው መርምራችሁ ተጠያቂዎችን ለይታችሁ ለህግ አቅርቡ እንጅ በደፈናው አትፈረጁ ወይም አታድበስብሱ፡፡ በሲቪሊያን ላይ ማንነትን መሠረት አድርጎ በተደጋጋሚ የሚደርስን ጥቃት ማስቆም ካልቻለ ወይም ተጠያቂዎችን ለይቶ ለፍርድ ካለቀረበ የተጠያቂነቱ  ሸክሙ ከመንግሥት ላይ መውደቁ ግድ ነው፡፡ ስለሆነም የህግ ተጠያቂዎችንና ወንጀለኞችን ዛሬ ለይታችሁ ካለቀረባችሁ ነገ የጋራ ወንጀላችሁ ሆኖ መምጣቱን አትዘንጉ፡፡ 

ይህን ምክረ ሀሳብ የማቀርበው ለሀገሬ ኢትዮጵያ ካለኝ ፍቅር የተነሳ በተሰጣችሁ ዕድል አንዳች የሚጠቅም አስተዋፅኦ አድርጋችሁ እንድታልፉ ካለኝ በጎ ስሜት ነው፡፡ አብዛኞቻችሁ የዕድሜ እኩዮቼና የዘመን ተጋሪዎቼ በመሆናችሁ ቀሪ ዘመናችሁ መልካም እንዲሆን ማንም ከማያመልጠው የታሪክ ፍርድ ትድኑ ዘንድ ከመጨነቅ የተነሳ የታሪክ መስታዎትን እንድታዩ ለማስታወስ ነው፡፡ 

በተለይም በዚች ታሪካዊ ሀገር አንድ ልምምድ እውን ሆኖ ማየት ስለምፈልግ ነው፡፡ እሱም የመንግሥት ሹመኞች የሥራ ዘመናችው ሲያልቅ፤ መንግሥታቸውም ሲቀየር በሠላምና በአክብሮት በህብረተሰቡ መካከል ሲኖሩ ማየት ነው፡፡ የቀድሞ ባለሥልጣኖች በየዕድርና ሠርግ ቤቱ፣ በየቤተ እምነቱና  በየመናኸሪያው ስናገኛቸው ‘ስለሰጡን አገልግሎት እናመሰግናለን /Thank you for your service’  ሲባሉ ማየት ስለምናፍቅ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ አምላክ ዓይነ ልቡናችሁን ያብራላችሁ፤ ቀናውን ያሳስባችሁ!

 ከአለማየሁ ዋሴ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ከ 23ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ ጋር ያደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለ2027 የአፍሪካ ዋንጫ...

ማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኙን ማይክል ካሪክን አሰናበተ

የእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ ክለብ ዋና አሰልጣኙን ማይክል ካሪክን ከኃላፊነታቸው...

ኢትዮጵያ በCOP31 የደን ጥበቃና የአየር ንብረት ተግባር ላይ ጥሪ አቀረበች

ኢትዮጵያ በቱርክዬ አንታሊያ በተካሄደው የCOP31 መሪዎች ዝግጅት፣ “ደኖችና የአየር...

1.5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ፕሮጀክት ወደ ተግባር መሸጋገሩ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን...