በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)
ከሴኔጋል ዳካር
ከዚህ በፊት ሶስት የፊፋ የወንዶች የአለም ዋንጫዎችን በደቡብ አፍሪካ፣በካታር እና በቅርቡ በአሜሪካ፣በካናዳና በሜክሲኮ፣ሁለት የፊፋ የሴቶች የአለም ዋንጫ በጀርመንና በካናዳ፣አራት የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በእንግሊዝ ለንደን፣በአሜሪካ ኦሪገን፣በሀንጋሪ ቡዳፔስት እና በቅርቡ በጃፓን ቶኪዮ በአጠቃላይ ዘጠኝ ፤በህይወት ዘመኔ ከፍ ብለው የሚነሱ የመክፈቻና የመዝጊያ ፕሮግራሞችን የማየት ዕድል ሙያዬ ያለስስት ስጥቶኛል፤
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ቀለም ደምቆ የታየበትና የእኔነት ስሜቱ ጎልቶ የተንፀባረቀበትን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር የተካሄደውን የወጣቶች ኦሎምፒክ የመክፈቻና የመዝጊያ ፕሮግራሞችን በማጣጣም ሌላ አዲስ የስኬት ምዕራፍ በወርቅ ቀለም የማፅፍበትን ደማቅ ታሪክ ዳካር ስላጎናፀፈችኝ በቃላትየማልገልፀው ልዩ ስሜት ተሠምቶኛል።
“በእነዚህ ሁሉ ስኬቶች ሳልኩራራ ኢትዮጵያ”የሚለውን ታላቅ ስም አንግቤ በታሪክ ላይ ታሪክ ማፃፌን አዳዲስ ታሪኮችን መራቤንም እቀጥላለሁ።
የዳካር ማስታወሻዬንና ትዝብቴን ይህቺን ፍፁም ጨዋ፣እንግዳ ተቀባይ፣ያለውን ተካፍሎ በመብላት የሚያምን፣ፍቅር የሆነ ህዝብ ያሏት መሠረተ ልማቶቿ ከግምቴ በታች የሆኑብኝን፣በሞተር ብስክሌት ተጨናንቃ መተንፈሻ ያጣችውን ዳካርን ዛሬ ተሠናብቼ የምወጣው በዳካር ያየሁትንና የታዘብኩትን በቀጣይ እንደማካፍላችሁ ቃል በመግባት ጭምር ነው።
✅መንደርደሪያ
ሁሌም እንደምለው አንዳንድ ጉዞዎች በርቀት አይለኩም፤ በሚተዉት ትዝታ፣በሚፈጥሩት ስሜትና በልብ ውስጥ ታትመው በሚቀሩት ታሪኮች ይመዘናሉ፤በሴኔጋል ዳካር ሠማይ ስር የነበረኝ የ14 ቀን ቆይታዬም ከእነዚህ የማይረሱ የሕይወት ገጠመኞች አንዱ ሆኖ በልቤ ውስጥ ለዘላለም ታትሞ ይኖራል።
እ.ኤ.አ ከጥቅምት 31 እስከ ህዳር 13 በሴኔጋል ዳካር የተካሄደው የዳካር 2026 የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የስፖርት ውድድር ብቻ አልነበረም፤ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሎምፒክ የስፖርት ዝግጅትን ወደ አፍሪካ ያመጣ፣ለአህጉሪቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነበር፤ዳካር አፍሪካ ታላላቅ የዓለም ስፖርታዊ ውድድሮችን በክብር ማስተናገድ እንደምትችል ለዓለም አሳይታለች።
ከመክፈቻው እስከ መዝጊያው፣ከዳያምኒያዲዮ እስከ ሳሊ፣ ከውድድር ሜዳዎች እስከ የአፍሪካ ባህል፣ሙዚቃና የወጣቶች የውድድር መንፈስ ዳካር የራሷን መልዕክት ለዓለም አስተላልፋለች፤ይህ ዝግጅት ስፖርት ከሜዳሊያና ከውጤት በላይ የሕዝቦች ወዳጅነት፣የባህል ልውውጥና የተስፋ ድልድይ መሆኑን አሳይቷል።
✅የአፍሪካ ድልና የኢትዮጵያ የወርቅ ታሪክ
በዳካር 2026 የአፍሪካ ሀገራት ያሳዩት ብቃት ሌላው የዝግጅቱ ትልቅ ድምቀት ነበር፤የአህጉሪቱ ተወካዮች በአጠቃላይ 74 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የአፍሪካን የወጣቶች ኦሎምፒክ ታሪክ አሻሽለዋል፤ለአስተናጋጇ ሴኔጋልም የ16 ዓመቷ ኤሊዛቤት ዲያታ በቢች ሬስሊንግ ያስመዘገበችው ወርቅ ታሪካዊ የኩራት ምንጭ ሆኗል።
ኢትዮጵያም በዚህ ታሪካዊ መድረክ የወርቅ ድሏን በታሪክ መዝገብ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርቅ ቀለም በማፃፍ የሀገሯን የውጤትና የታሪክ ክብር አስቀጥላለች፣አስጠብቃለች፤ይህ ስኬት የኦሎምፒክ ኮሚቴን ያልተኬደበት አዲስ መንገድ፣የአሠልጣኞች፣ የወጣት አትሌቶቻችንን ተሰጥኦ፣ጥረትና ተስፋን ያሳየም ነው።
✅የዳካር ትልቁ ውርስ
የዳካር ስኬት በሜዳሊያዎችና በሥነ-ሥርዓቶች ብቻ መመዘን የለበትም፤የተገነቡና የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች፣የወጣቶች ተሳትፎ፣የስፖርት ተቋማት አቅምና ከውድድሩ በኋላ የሚቀጥለው ዘላቂ ጥቅም የስኬቱ እውነተኛ መለኪያዎች ናቸው፤አፍሪካ የታላላቅ ውድድሮች ተመልካች ብቻ ሳትሆን አዘጋጅና ባለቤትም መሆን እንደምትችል ዳካር አሳይታለች።
✅14 ቀናት በዳካር ሰማይ ሥር፤የማይረሳ የሙያ ወዳጅነት
ከውድድሩ በተጨማሪ ለእኔ ዳካር 2026 ያበረከተችልኝ ትልቁ ስጦታ አምስት ከሚሆኑ የሙያ ጓደኞቼ(ጋዜጠኛ ፍቅር ይሌቃል፣ጋዜጠኛ ግርማቸው እንየው፣ጋዜጠኛ ይገደብ ዓባይ፣ጋዜጠኛ ሠለሞን በቀለና ጋዜጠኛ ወርቅነህ ጋሻው)ጋር ያሳለፍናቸው 14 ውብ ቀናት ናቸው፤ በዳካር ሰማይ ሥር የነበረን መተሳሰብ፣መረዳዳት፣መከባበርና አንዱ ለሌላው የነበረው ድጋፍ ከዚህ በፊት ካሳለፍኳቸው የቡድን ቆይታዎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ በልቤ ተቀርጾ ይኖራል፤ከእናንተ ከታናናሾቼ የተማርኩት አንድ ትልቅ ትምህርት አለ፤ዝቅ ማለት የታላቅነት ምልክት መሆኑን፣ለሰው ክብር መስጠት ዋጋው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነና የሙያ ወዳጅነት በመከባበር ሲገነባ ምን ያህል ውብ እንደሚሆን በተግባር አይቼበታለሁ።
ውድ የሙያ ጓደኞቼ፤ ከዳካር ስመለስ ከመጥፎ ትዝታ ይልቅ ሁሌም በፈገግታ የማስታውሰው መልካም ትዝታ ይዤ እንድመለስ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፤ከሁሉም በላይ በጋዜጠኝነት ሙያችን የኢትዮጵያ ታሪክ በዳካር ደምቆ ሲጻፍ በቦታው ተገኝተን ሕያው ምስክሮች መሆናችን ሳስብ የደስታዬን መጠን በእጅጉ ይጨምራል።
✅ለዚህ ታሪካዊ ዕድል ባለቤት ላደረገን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዩ ምስጋና!
በተለይም የጋዜጠኝነትን ሙያ ከፍ አድርገው የሙያችንን ክብር በተግባር ላሳዩን ለኢትዮጵያ ኦልምፒክ ኮሚቴ አባላት በአጠቃላይ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ለተከበሩ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ልዩ ምስጋናዬን የማቀርበው በልዩ የኩራት ስሜት ነው፤በዳካር የተመዘገበው የወጣቶች ኦሎምፒክ ስኬት ከውጤት በላይ ራዕይ፣አመራርና የሃሳብ ፈጠራ የሚጠይቅ መሆኑን በዚህ ጉዞ በቅርበት ተመልክቻለሁ፤የአስተሳሰብ ድንክ እንደሆኑት ሠዎች ትንሽዬ ሃሳብ የመብላትና የመጠጣት አሊያም የጥቅም ጉዳይ ሳይሆን ለጋዜጠኛውና ለሙያችን ለሰጡት ክብር፣ለፈጠሩት ዕድልና ለተመዘገበው አንፀባራቂ ውጤት በድጋሚ ባርኔጣዬን በአክብሮት ከፍ አደርጋለሁ።
✅ለሴኔጋሊያዊው ኦማር ብራዘር(Omar Sane) የሰውነት ጥግ!
በሴኔጋል የ14 ቀናት ቆይታችን ያማረ እንዲሆን፣ ባይተዋርነት እንዳይሰማን፣ የዳካርን ውበትና ምስጢር በሚገባ እንድናውቅ በትዕግሥት፣በቅንነትና ወንድማዊ ፍቅሩን ያለስስት የሠጠንን ሾፌራችንን Omar Sane አንተ ከሾፌርነት በላይ ለእኛ ጓደኛና መልካም መመኪያ ነበርክ፤በአንተ መልካምነት ውስጥ ሴኔጋልን አይተናታል፣አውቀናታል፤አንተ የሰውነት ጥግነትን በቃል ሳይሆን በተግባር ያሳየኸን ልዩ ሰው ነህ፤ለሁሉም ከልብ እናመሰግናለን!
✅Bye Bye Sénégal! – ደህና ሁኚ ሴኔጋል!
ሴኔጋል ሆይ! በልዩ ፍቅር፣ ሞቅ ባለ ልባዊ መስተንግዶ ሁለቱን እጆችሽን ዘርግተሽ ተቀብለሽኛል፤ወደ ሀገሬ ዛሬ የምመለሠው የሕዝብሽን ጨዋነት፣ከፊታቸው ለሠከንድ እንኳን የማይጠፋው ፈገግታቸውን፣በአትላንቲክ ውቅያኖስ የተከበበውን የዳካርን ውበትና The Lion of Teranga የቴራንጋን የእንግዳ አቀባበል በልቤ ይዤ ነው።
Teranga ማለት ከአንድ ቃል በላይ መሆኑን በወሬ ሳይሆን በተግባር አይቻለሁ፤የፍቅር፣የመስተንግዶና የሰው ልጅ ክብር መገለጫ ስለመሆኑ ህያው ምስክሩ እኔ ነኝ።
ደህና ሁኚ ሴኔጋል!አመሰግናለሁ ዳካር! ከአንቺ የወሰድኩት ትዝታ ከሻንጣዬ ይልቅ በልቤ ውስጥ በስፋት ተሞልቷል።
እንደገና እስክንገናኝ ድረስ፤ የቴራንጋ ፍቅር በልቤ ይኖራል!
Jërëjëf Sénégal ! Jërëjëf Dakar ! ❤️🇸🇳🇪🇹
በቀጣይ የዳካር የጉዞ ማስታወሻ ትዝብቴ ይቀጥላል፤በተለይ ከ16 ዓመታት በላይ ስላስቆጠረውና ትናንት ከሙያ ጓደኞቼ ጋር ስለጎበኘሁት የአፍሪካን ነፃነት፣የህዳሴ ጉዞ፣የተስፋ ብርሃን፣ የትውልድ ቀጣይነትና የአህጉሪቱን የወደፊት ህልም ለመወከል ስለተገነባውና ሶስት ቤተሠብን በትልቅ መልዕክትነት የሚያሳየውን የሴኔጋል ታላቁ የአፍሪካ ህዳሴ ሀውልትን፣በዳካር ጎዳናዎች ስለሚርመሠመሱት፣ግን ደግሞ የከተማው የትራንስፖርት እስትንፋስ(የልብ ምት)ስለሆኑት ምተር ሳይክሎች አጋራችኋለሁ፤ጠብቁኝ።
