የኢትዮጵያ ቅርሶችን ከሕገወጥ ዝውውር ለመጠበቅ ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት ሊዘረጋ ነው

Date:

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሀገሪቱን ታሪካዊ፣ ባህላዊና አርኪኦሎጂያዊ ቅርሶች ለመጠበቅና ከሕገወጥ ዝውውር ለመታደግ ዲጂታል የቅርስ ምዝገባ ሥርዓት ለመዘርጋት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ በአዳማ ከተማ የሕገወጥ የቅርስ ዝውውርን መከላከል አስመልክቶ በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ እንዳሉት፣ በአፍሪካ የቅርስ ሀብቶችን በተገቢው ሁኔታ መጠበቅና መከታተል እየተወሳሰበ መጥቷል።

በተለይም የፖለቲካ ቀውሶችና ግጭቶች ለቅርሶች ሕገወጥ ዝውውር መባባስ ከሚያበረክቱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነትም በርካታ ቅርሶች ከተጠበቁበት ቦታ መወሰዳቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንዳሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዘመናት ጀምሮ ከሀገር የተወሰዱ ቅርሶቿን ለማስመለስ ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ ስምምነቶችንና ሀገራዊ ሕጎችን መሠረት በማድረግ እየሠራች መሆኗንም ጠቁመዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመሥራትም በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ቅርሶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች በኢንተርኔትና በማኅበራዊ ሚዲያ ለጨረታና ለሽያጭ መቅረባቸው አዲስ ፈተና መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰር አበባው፣ ይህንን ለመከላከል የተለያዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ቅርሶችን በማስመለስና ሕገወጥ ዝውውራቸውን በመከላከል ረገድ አመርቂ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ የሚዘጋጀው ስትራቴጂም በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ትኩረት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

የቅርስ ጥበቃ የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የመንግሥትን፣ የማኅበረሰቡን፣ የምርምር ተቋማትንና ዓለም አቀፍ አጋሮችን የጋራ ትብብር የሚጠይቅ ብሔራዊ ኃላፊነት መሆኑም ተገልጿል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተሰረቀ ዕቃ በቅናሽ ዋጋ መግዛት ወይም ይዞ መገኘት እስከ 3 ዓመት እስራት ያስቀጣል

በርካሽ ዋጋ የተሰረቁ ስልኮችን፣ ላፕቶፖችንና ሌሎች ዕቃዎችን መግዛት፣ የተሰረቀ...

በኢትዮጵያ በዓመት ከ18ሺህ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ይጠቃሉ ተባለ

ጤና ሚኒስቴር  ከለሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የጡት ካንሰር...

35ኛው ዓለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን ተከበረ

በዝግጅቱ ላይ የስኳር ህመምን ለመከላከል ቅድመ ምርመራን፣ ጤናማ አመጋገብንና...

በኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማእከል

መገናኛ ብዙሃን ሕጋዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ...