መገናኛ ብዙሃን ሕጋዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ በዕውቀት እና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
ስለሆነም በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 6(11) መሰረት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ራሱን የቻለ የሚዲያ ስልጠና ማዕከል በማቋቋም የጋዜጠኞችን አቅም እንዲገነባ በተሰጠው ሃላፊነት መሠረት በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል በማቋቋም በቅርቡ ተመርቆ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጁ ሆኗል።፡
በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍም ይሁን በአገራችን ያለው የሚዲያ አወድ ተቀይሯል፡፡ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ በርካታ ዕድሎች እና በረከቶች የተፈጠሩትን ያህል፤ በርከት ያለው ሃይል ደግሞ የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ-ምግባር እና የክህሎት ሥልጠና ሳይኖረው የይዘት አምራችና አሠራጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህም መሰረት በዘርፉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ዘንድ በሚገባ የሚታወቁትንና የሚተገበሩት የሚዲያ ሥነ-ምግባር መርሆች በስፋት እንዲጣሱ አሉታዊ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡
ይህም የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭት እንዲስፋፋ ምክንያት በመሆኑ፤ በሕዝብና በሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚጋርጠው ጉዳትና አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለሙያዎች ከመቸውም ጊዜ በላይ የሕዝብን እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ሚና እና ተልዕኮዋቸውን በጥራት ይወጡ ዘንድ የባለሙያዎችን የሙያ እና የሥነ-ምግባር ደረጃ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መገናኛ በሰዙሃን ባለስልጣን ባአስቻይ፣ በውይይትና ምክክር ላይ የተመሰረተ፣ ሕዝብን ያሳተፈና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የቁጥጥር እና ድጋፍ ሥርአት በመዘርጋት ዘርፉን ለመደገፍ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን፤ ክፍተቶች ሲገኙም ለመተራረም የሚያስችል በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጋራ ውይይት በማካሄድ እና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በአካል ጉብኝት በማድረግ እና ግብረ መልስ በመስጠት የማረም እና የማስተካከል ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር የማዕከሉ መቋቋም ዋና ዓላማ በሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ባሙያዎች የሚስተዋለውን የዘርፍ ጋዜጠኝነት ክፍተት መሙላት እና ጋዜጠኞች በተለያዩ የትኩረት መስኮች ጥልቅ ዕውቀት እና የትንታኔ አቅም እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። ሥልጠናው የዘርፍ ጋዜጠኝነትን (Specialization Journalism) ማዕከል ያደረገ ተግባር ተኮር መርሃ-ግብር ነው፡፡
በዚህም መሰረት በሙያው ላይ ከፍተኛ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ምሁራን አማካኝነት ደረጃውን የጠበቀ የተግባር ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ተጋባዥ እንግዶች አማካኝነትም ሠለጣኞች ሰፊ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ይደረጋል። ይህም በንድፈ-ሐሳብና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የክህሎት ክፍተትን ለመሙላት ያስችላል።
የማዕከሉ የሥልጠና ሂደት በከፍተኛ ጥንቃቄና በጥናት በተቃኘ ካሪኩለም የሚመራ ሲሆን፣ የተዘጋጁት ሞጁሎችም በሦስት ዋና ዋና የዕድገት እርከኖች የተዋቀሩ ናቸው። በዚህም መሰረት ሥልጠናው መገናኛ ብዙሃን በመንግሥታዊ አስተዳደር እና በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ሠፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ፣ ንድፈ-ሐሳብን ከተግባር ጋር በማቀናጀት የሚያቀርብ ሲሆን፤ የዲጂታል ሚዲያና ሰው ሰራሽ አስተውሎትም ሙያዊ ሥነ ምግባር መርህን በጠበቀ መልኩ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መረጃን በጥልቀት የመተንተን ክህሎትን እና የዘርፍ ጋዜጠኝነትን የሚያስጨብጡ፤ በሀገራችን ዲፕሎማሲ፣ ጂኦ ፖለቲካ እና መሰል ዋና ዋና ትኩረት የተሰጣቸው ርእሰ ጉዳዮች በሥልጠናው ተካተዋል፡፡
በመሆኑም የማዕከሉ ዕውን መሆን፤ ሙያዊ ብቃትን የተላበሰ፣ በጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር የዳበረ፣ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና ታአማኒ መረጃ ለሕዝብ በማድረስ እና የሕዝብ አመለካከት በመቅረፅ፤ ለሀገራችን የመረጃ ልውውጥ ሥርአት ሁነኛ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አዲስ ምዕራፍ ከፋች ሆኗል፡፡
