በከተማዋ የኮሪደር ልማት ባለባቸው አካባቢዎች የንግድ ተቋማት እስከ ምሽቱ4 ሠአት ድረስ እንዲሠሩ የሚያዝ ህግ መውጣቱ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ መዲናዋ ላይ የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ለውጥን በሚመለከት አራዳ ኤፍ ኤም ውሳኔውን ያሳለፈውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ጠይቋል።
ቢሮው በምላሹ አሁን ላይ የንግድ እንቅስቃሴው እስከተጠቀሰው ሠአት ድረስ ወጥና ዘላቂ እንዲሆን ማስቻል ቅድሚያ የተሰጠውጉዳይ እንደሆነ ጠቅሶ፥ ምን ያህል ለኢኮኖሚው አስተዋፅዖ አለው የሚለው ደግሞ ጥናት ይደረግበታል ብሏል።
ጥናቱ የሚጀመረው የከተማዋ ነዋሪ በምሽት ሸመታ ለማካሄድ የመውጣት ልማድ እያዳበረ መሄዱ ከተስተዋለ በኋላ መሆኑም ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍሰሃ ጥበቡ ፥ ዜጎች ሥራን ባህል እንዲያደርጉና ተጨባጭ በገንዘብ የተለካ ምጣኔሃብታዊ ለውጥ እንዲኖር የንግድ ማህበረሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው ሲሉ ለጣቢያችን አስረድተዋል።
ከትራንስፖርት አንፃር እንዲሁም ከመሸ በኋላ የደህንነት ችግር አለባቸው የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልፀዋል።
