በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ 3 የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ከ24 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች የካምፖቹ የአገልግሎት ጊዜ በማብቃቱ መቸገራቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ካለፉት 5 ዓመታት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ቻይና፣ ባቄሎ እና ወይንሸት የሚል መጠሪያ ባላቸው መጠለያ ካምፖች ውስጥ ከ3 ዓመት በላይ እንደቆዩ የተናገሩት ነዋሪዎቹ፤ ከሸራ እና ከፕላስቲክ የተሰሩት የካምፖቹ መጠለያዎች በተፈራረቀባቸው ጸሐይ እና ዝናብ ምክንያት የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማብቃቱ ለመኖር በማይመች ሁኔታ ውስጥ ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል።
የካምፑ አስተባባሪ “በቻይና እና ወይንሸት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙት ከ3 ዓመት በላይ በቦኬሎ የሚገኙት ደግሞ ከ2 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም፤ “መጠለያ ካምፖቹን ለማሻሻል የተደረገው ጥረት አነስተኛ ነው፣ አደጋ ላይ ያሉት ተፈናቃይ ዜጎች ተዘንግተዋል እንዲሁም፤ መጪው ክረምት እንደመሆኑ የፌደራል መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በካምፖቹ ተፈናቅለው ከሚገኙት ዜጎች መካከል 5 ሺሕ የሚሆኑ ሴቶች ከምግብ አቅርቦት አናሳ መሆን፣ በቂ የውሃ አቅርቦት አለመኖር እንዲሁም፤ የመጸዳጃ ቦታዎች አለመመቻቸት ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን በመግለጽ ለሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅሬታ ስለማቅረባቸው አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
