በዓለም አቀፍ ደረጃ ለፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተዋናዮችን እውቅና (Certification) የሚሰጠው ሲ.ኤፍ.ኤ (CFA) በኢትዮጵያ የፈተና ማዕከል መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።
ከዚህ ቀደም ይህንን ሰርተፊኬት ለማግኘት የሚሰጠውን ፈተና ናይሮቢ ወይም ሌሎች ቻርተሮች ወደ ሚገኙበት መሄድ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቻርተርን መቀላቀሏን ተከትሎ በአዲስ አበባ የመፈተኛ ማዕከል ይኖራል ተብሏል።
በምሥራቅ አፍሪካ ይሄን ሰርተፊኬት ያገኙ ባለሞያዎች ቁጥር ከ600 ቢልቅም በኢትዮጵያ ግን ሰርተፊኬቱን ያገኙት ባለሞያዎች ቁጥር 11 ብቻ ናቸው።
በዚህ መርሐግብር የተገኙት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልኩ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የክክሎትና እውቀት ክፍተት መኖሩን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በCFA እና መሰል ተቋማት የሚሰጡት ትምህርቶችና ሰርተፊኬቶች ክህሎት፤ እውቀት እና ዲሲፕሊን አብሮ የያዙ በመሆኑ ለገቢያው ጠቃሚ እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና ወጥ የሆነ የእውቀት ደረጃ እንዲኖር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በዘርፉ ያለው የሰው ኃይል እና እውቀት ክፍተት ምን ያህል ነው ? ምንስ እየተሰራ ነው? ስንል የጠየቅናቸው ዋና ዳይሬክተሯ ” ሰፊ ክፍተት አለ ” ሲሉ አመላክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በዝርዝር ምን አሉ ?
” የፋይናንስ እና አኮኖሚ ዘርፉን፤ ካፒታል ማርኬትን እንዲሁም በካፒታል ማርኬት ያሉ ህጎችና ደንቦችን ከመረዳት እና የሚፈጠሩ ችግሮችን በአግባቡ የማስተዳደር (Risk management) ላይ ሰፊ ክፍተት አለ።
አሁን ላይ ከfsd ጋር በመተባበር በዘርፉ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል አቅም (Human Capital Strategy ) እየሰራን እንገኛለን ወደ መጠናቀቁ ላይ ይገኛል። ይሄ ሲጠናቀቅ ያለው ክፍተት ምንድን ነው፤ የትኞቹ ተቋማት መካፈል አለባቸው የሚለውን ይመልሳል።
ከዚህ በተጨማሪ፤ ባለሥልጣኑ የካፒታል ማርኬት ስልጠና ተቋም እያቋቋመ ነው። አሁን ላይ ከፍ ያለ የስልጠና ማኑዋል በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን ይሄ ሲጠናቀቅ ፕሮግራሙን በይፋ አስተዋውቀን ወደ ስልጠና እንገባለ።
CFA ወደ ሀገር ውስጥ የማምጣቱም ሂደት የጥረቱ አካል ነው ” ሲሉ ገልጸዋል።
የዩኤን ዲ ፒ ፋይናንሻል ላብ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የዘርፉ ባለሞያዎች ስፖንሰር ሺፕ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ይህ ስኮላርሺፕ እነማንን ይመለከታል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ በዩ ኤን ዲፒ ፋይናንሻል ላብ ዳይሬክተር የሆኑትን ዳግማዊት ሽፈራውን ጠይቋል።
ዳይሬክተሯ በምላሻቸውም፥ ይህ ስኮላርሺፕ በዘርፉ ልምድ ላላቸው የሚሰጥ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ለምን ያህል ሰዎች እንዲሁም የብሩን መጠን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።
” በጣም ትጋት የሚፈልግ ነው ። ፈተናውን የማለፍ ምጣኔው 49 በመቶ ነው [Level 3] ለዚህ ደግሞ የውጤቱ መጠን ከፍ ያለ እንዲሆን ልምድ ላላቸው ሰዎች እድሉን እንሰጣለን “ ሲሉ ነው ያስረዱን።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልኩ ባንኮች፤ ኢንሹራንሶች፤ የመንግስት ተቋማት እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮች ለሰራተኞቻቸው ይህን መሰል ሥልጠና እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የCFA ሰርተፊኬት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ገቢያውን ለመቀላቀል የሚረዳ ነው ሲባል ኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬትን ማስተዋወቋን ተከትሎ ፍላጎቱ እንደሚጨምር ይታመናል።
ይንንን ሰርተፊኬሽን ለማግኘት ሦስት ደረጃዎች ሲኖሩት ለማጠናቀቅ ከ4100 ዶላር በላይ ይጠይቃል። ከዚህም በላይ 400 የጥናት ሰዓታት በየደረጃው ይፈልጋል ተብሎ ሲገለጽ ፈጣኑ የማጠናቀቂያ ጊዜ 2 ዓመት ነው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
