(በእውቀቱ ስዩም)
ጀርመን በገባሁ በሁለተኛ ቀኑ ማካፋት ጀመረ፤ ዝናብ ያረጠበው አፈር ሽታ ናፈቀኝ ፤ እዚህ ደግሞ መሬቱ እንዳለ በኮብል ተሸፍኗል፤ ደግነቱ ከኢትዮጵያ ስወጣ አፈር በያይነቱ ቆጣጥሬ ነው የወጣሁት፤ ቀይ አፈር – ደባይ አፈር – የመቃብር አፈር- በርበሬ እንዲበረክት የሚያረግ አፈር- ሙሉቀን መለሰ ምነው ባደረገኝ ብሎ የተመኘው “የሚነፈራፈር አፈር”፤
ከሁሉም አፈር አይነት ቆነጣጥሬ፥ በጀርመን ዝናብ ለውሼ ማግ ሳደረገው እልል ያለ አጭሬ ግጥም መጣልኝ፥
“እንዴት ነሽ አገሬ
ከነገ አንጻር ሲታይ ደግ ቀን ነው ዛሬ
ስንት ገባ ይሆን የውጭ ምንዛሬ ?
ከጀርመን ከተማዎች ባንዱ እየተርመሰመስሁ ነበር ፤የሆነ መጸዳጃ ቤት ገብቼ ስሙኒ ከፍየ እጄን ታጠብሁ፤ አለንጋ ጣቶቼን ሳራግፍ ወለሉ ላይ ጥቂት ነጠብጣብ አረፉ፤ ወለል ጠራጊው ሽማግሌ ፈረንጅ ይሄን ሲያይ እንደማበድ አረገው፤
“ቫሩም?” ብሎ ቀወጠው፤ “ ጀርመንኛ ብዙ ባላውቅም፥ “ ምን ነካህ? እንዴት ልፋቴን መና ታደርገዋለህ?” ምናምን ማለት እንደሆነ ቀልቤ ነግሮኛል፤( እምገርመው ። ቀልቤ ከኔ የተሻለ ጀርመንኛ ያውቃል)
ጌታ ሆይ ! ብዙ ሺህ ማይል አቆራርጬ ፥ አውሮፓ ገብቼ ፥ ፈረንጅ የማናድድበት ሐይል የሰጠኸኝ እኔ ማን ነኝ? ብየ ተደነቅሁ፤
መልሼ ሳስበው ግን ተጸጸትሁ፤ ያንጠባጠብሁትን የውሀ ርጋፊ ላጸዳ መጥረጊያውን ብድግ ሳረግ ሰውየው እንደገና ተንደቀደቀ፤
ከውጭ የሚጠብቀኝን ዲያስፖራ ሰለሞን ሞገስን “ምንድነው የሚለው” ብየ ጠየቅሁት፤ ተረጎመልኝ፤
ጠራጊው ሽማግሌ እንዲህ ነው ያለኝ፤
“ውሀ ስታንጠባጥብ ታግሼሀለሁ፤ መጥረጊያየን ስትሰርቀኝ ግን እፋረድሀለሁ”
ሳያሳፍሰኝ አመለጥኩ፤
የሆነ ሰአት ብቻየን እየተራመድኩ አንድ ሀውልት አገኘሁ፤ ሀውልት ከማይሰምርበት አገር ስለመጣሁ ሀውልት ብርቄ ቢሆን አይገርምም ፤ ከሀውልቱ ስር ፎቶ ለመነሳት ፈለግሁ፤ አንድ ፈረንጅ ባጠገቤ ሲያልፍ ተከትየ በጀርመንኛ አንሳኝ አልሁት፤ ዝም ብሎኝ ሄደ፤ በላቲን ሳይቀር ጠየቅሁት፤ ገላምጦኝ ርምጃውን አፋጠነ፤
አይ ፈረንጅ! ከላይ ሲታዩ የተማሩ ይመስላሉ! ፎቶ በሞባይል እንዴት እንደሚነሳ እንኳ አያውቁም ፤ “ብየ ራሴን ለማጥናናት ሞከርኩ፤
አማራጭ ሳጣ ፥ሰልፊ ፊቴ ላይ ደገንኩ፤ ካሜራው የኔን ፊት እየዘለለ ሀውልቱን መቅረጽ ጀመረ፤ አጥብቆ ሆድ ባሰኝ! ሆድ ለባሰው ሞባይል አታውሰው! ድንገት ስልኬ ከመዳፌ ላይ ሲንሸራተት ይታወቀኛል፤ ቷ! ስልኬ በግንባሩ ክንብል ካለበት አንስቼ ሳየው ስክሪኑ የሸረሪት ድር ሪልስቴት መስሏል፤
በመጨረሻ ወደ ማረፊያ ቤቴ ስመለስ ሁለት ደጋግ ያገሬ ልጆችን አገኘሁ፤
ትንሽ ሰላምታ ከተለዋወጥን በሁዋላ፤
“ የምትፈልገው ካለ ንገረን ?” አሉኝ ፤
“ ባስቸኳይ ወደ አገሬ መልሱኝ “
