የኤም ፖክስ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የሚወጡ መግለጫዎችም ሆነ መረጃዎች መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በምልክት ቋንቋ ተደራሽ እየተደረገ አለመሆኑን መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ገልጿል።
ማህበሩ በመንግስት በኩል ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፆ፥ መገናኛ ብዙሃንም ኃላፊነት አለባቸዉ ብሏል።
ምን አይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ከሚለው ጀምሮ በበሽታው ቢያዙ ምን ማድረግ አለባቸው እስከሚለው ድረስ የሚመለከተው አካል ወደ ማህበሩ ቀረብ ብሎ የግንዛቤ ሥራዎች መስራት እንደሚጠበቅበትም አክሏል።
በተለይም በጤና ተቋማት የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች አለመኖር መስማት የተሳናቸው ከፍተኛ የሆነ የተግባቦት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ገዳሙ ሁንዴቻ ተናግረዋል።
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ ጊዜ ከሚከሰቱ ወረርሽኞችም ሆነ ሌሎች ችግሮች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መረጃ ተደራሽነት ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።
አያይዘውም የኤም ፖክስ በሽታ ቢስፋፋ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ተጠቂ የመሆን እድላቸው የሰፋ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል።
