‹‹ሰው ሀገር የማየው መልካም ነገር ሁሉ ያስቀናኛል››

Date:

ወ/ሮ ሳራ ሐሰን
(የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ም/ፕሬዝዳንት)
ባሳለፍነው ዕትም ከሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ም/ፕሬዝዳንት ሳራ ሐሰን ጋር በግል ሕይወታቸው እና በሥራ እንቅስቃሴያቸው ዙርያ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገን የነበረ መኾኑ ይታወሳል፡፡ በመጨረሻውና በሁለተኛው ክፍል ደግሞ በሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው እና አበርክቶዎቻቸው ዙርያ የሠሩትንና መሥራት የሚሹዋቸውን ጉዳዮች የተመለከተ ቆይታ አድርገናል፡፡ እንኾ!


ግዮን፡- ብሪክስ በነበራችሁበት ሰዓት ስለነጋዴ ሴቶች የተነሳው ጉዳይ ምን ነበር?
ሳራ፡- እንደሀገር የኢትዮጵያ ሴቶች ከአሁን በኋላ መኾን ያለባቸውን ሀገራችን ብሪክሰን ከተቀላቀለች በኋላ ምን ልታገኝ ትችላለች፣ አሁንስ ባለን ልምድ ወደፊት ምን መሥራት አለብን የሚለው ላይ ብዙ ተወያይተናል፡፡ ስለዚህ የብሪክስ አባል ሀገራት ብዙ ለውጥ ያመጣሉ ብለን እናስባለን፡፡ አካሄዱ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም የብሪክስ አባል መኾኗ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ራሷን አባል አድርጋ ብሪክስ ውስጥ መገኘቷ በራሱ የሚያኮራ ነው፡፡


ግዮን፡- ኃላፊነቶችዎ በርካታ ከመኾናቸው አንፃር ለሌሎች ሴቶች ምን ይመክራሉ?
ሳራ፡- የሀገር ነገር ማስቀደም መልካም ነው፡፡ እኔ ሀገርና እናትን አበላልጨ ማየት አልችልም፡፡ እኛ ውጭ ሀገር የኖርን ሰዎች ሀገር ማለት ምን ማለት እንደኾነ በደንብ ይገባናል፡፡ በሰው ሀገር ላይ ምሉዕነት የለም፡፡ ሁሌ ባይተዋርና ጎደሎነት ነው ያለው፡፡ ሁሌ ከእነሱ የተረፈውን ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ በእርግጥ የፈረንጅ ሀገር የተመቻቸው ወገኖች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኔ አንድም ቀን ከሀገሬ ውጭ ያለው ሕይወት ተመችቶኝ አያውቅም፡፡ በጣም ሀገሬን ስለምወድ የሰው ሀገር አይመቸኝም፡፡


ወደ ጥያቄው ስመለስ ተደራራቢ ኃላፊነቶችን መሸከም በርካታ ጉዳቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ጉዳት ማኅበራዊ ሕይወትን ማበላሸቱ ነው፡፡ የግል ሕይወት በጣም ይጎዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰው ሞቶ መቅበር የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሰፋ አድረገን ስናየው ደግሞ ለሀገር ማገልገል ጥሩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ኃላፊነት ሲበዛ የተለየ ጫና አለው፡፡ ለምሳሌ እኔ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውስጥ አራት ዓመት በሥራ አስፈፃሚነት አገልግያለሁ፡፡ በቅርቡም ተመርጩ ከኮማንደር ስለሺ ስህን ጋር በሥራ አስፈጻሚነቱ እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡


ግዮን፡- እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚነትዎ አሁን ላይ በአትሌቶቻችን ላይ የሚታየውን ድክመት ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?
ሳራ፡- በአትሌቲክሱ ውስጥ የመሥራትና ድክመቶችን የመለወጥ ከፍተኛ ተነሳሽነት አለኝ፤ በተለይ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ሀገሩን የሚያስጠራ አትሌት ይወዳል፡፡ ለምሳሌ ሰዎች እኔን ‹‹አትሌቲክስ ምን ያደርግልሻል?›› ሲሉኝ ‹‹ውጪ ሀገር ሄደን አትሌቶቻችን አሸንፈው የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚሰማውን ስሜት ስለማታውቁት እንዲህ ነው ብዬ ለመግለጽ እቸገራለሁ›› ብየ እመልስላቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ያቺ ስሜት ለእኔ ከቃል በላይ ናት፡፡ በውጭውም ዓለም ብሔራዊ መዝሙራችን ተዘምሮ ባንዲራችን ተውለብልቦ ኢትዮጵያ ስትጠራ በጣም የተለየ ስሜት ስለሚሰማኝ ይህን ተቋም አገልግዬ መኖር ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የእኔ አስተዋፅኦ የኾነ ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡


እያንዳንዱ ቤት ሲሠራ በብዙ ድንጋዮች እንደኾነ ሁሉ እኔም ከጠጠሯ አንዷ ብኾን ብዬ አስባለሁ፡፡ በአትሌቲክሱ ዙሪያ ትልቅ ችግር የሆነብን የማዘውተሪያ ስፍራ ነው፡፡ አትሌቶቻችን የማዘውተሪያ ሥፍራ የላቸውም ፤ የሚሰለጥኑበት ቦታ አቅም መገንባት የማይችልና የማይመጥን ከኾነ በዓለም ፊት ተወዳደሪ መኾን አይቻልም፡፡ ሌላው ደግሞ በአመራር ደረጃ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ ችግሮቹን በሽምግልናም ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ እንደሚታወቀው አብሮ የሚሠራ ሰው ይጋጫል ፤ እኛም እያለን ችግሮቹ ቀጥለዋል፡፡ አሁን ግን እነዚያን ችግሮች ቀርፎ ለውጥ አመጣለሁ ከሚለው አካል ጋር ተቀላቅዬ እየሠራሁ ነው፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡


ግዮን፡- የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ቦታ ሳይኖር ድሎች መጥተው ነበር ፤ አሁን የማዘውተሪያ ቦታ ምክንያት የሚደረገው ለምንድነው?
ሳራ፡- የማዘውተሪያ ቦታው አንዱ ስታዲየማችን ነበር፡፡ አሁን ላይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራኩ ተበላሽቶ ከተዘጋ አምስተኛ ዓመቱን እየያዘ ነው፡፡ ይኼ በጣም ትልቅ ችግር ነው፡፡ ስለኾነም ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር አካላት ጋር በመነጋገር በቅርቡ አዲስ ማዘውተሪያ እንደሚሠራ ተነጋግረናል፡፡ ምክንያቱም ትራክ ላይ የሚሰለጥን አትሌትና አስፋልት ላይ የሚሰለጥን አትሌት የሚኖራቸው ውጤት አንድ አይደለም፡፡
ሌላው ደግሞ በተለይ ለማራቶን ለአዲስ አበባ ቅርብ በኾኑ ጫካዎች ውስጥ የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን እነዚህ ቦታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደልማት በመግባታቸው ሌላ ችግር ኾኗል፡፡ እኛም አብረን እየሄድን የሚሰለጥኑበትን ቦታ እናያለን፡፡ ‹‹በግል የሚወዳደሩ ሁሌ አሸናፊ ይኾናሉ›› የሚለው ጥያቄ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን አትሌቲክስ ማለት ለአትሌቱ የመኖር ጥያቄው ነው፡፡ በአሠልጣኞችና በማናጀሮቻቸው በኩል ከፍ ያለ ሥልጠና ወስደው ይሳተፉና ስኬታማ ኾነው፣ ነገር ግን ጫናው ሲበዛ ዋናው ውድድር ላይ አቅም ማጣት ይመጣል፡፡ ይኽም ኾኖ ውጤቶች አሽቆልቁለዋል፡፡ ይህ ችግር በመኖሩም አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ ችግሮቹን ገምግሞ ከቀውሱ ለመውጣት እየሠራ ነው፡፡


በአትሌቲክስ ዙሪያ ባለፉት አራት ዓመታት አረንጓዴ ጎርፍ ከሚባለው ቀጥሎ በርካታ ሜዳሊያዎችን አግኝተናል፡፡ ከምንግዜም በላይ በዚህ አራት ዓመት ውስጥ 18 ሜዳሊያዎችን አግኝተናል፡፡ ነገር ግን ወርደን የታየነው አሎምፒክ ላይ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለኦሎምፒክ ተወዳዳሪን ከመምረጥ ጋር ተያይዞ የመጡ ክፍተቶች አሉበት፡፡ የኦሎምፒክና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውሳኔዎች ልዩነትም የራሱን ችግር ፈጥሯል፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አትሌቱን በሥልጠና አብቅቶ ለአሎምፒክ ኮሚቴው ያቀርባል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ደግሞ በታቀደው ፕሮግራም መሠረት ተወዳዳሪዎችን ማሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ያ ኾኖ ባለመገኘቱ የታየው የውጤት ማሽቆልቆል ተከስቷል፡፡


ግዮን፡- ሴተኛ አዳሪዎችን የመሰብሰብና ሥራ የመስጠት ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የእርስዎ ሚና ምንድነው?
ሳራ፡- ‹‹የነገዋ›› የተባለው የሴቶች ተቋም በከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅጣጫ ጠቋሚነት የተገነባ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ እንደሀገር ብቻ ሳይኾን እንደ አህጉርም፣ እንደ ዓለምም የሚያኮራ ትልቅ ማዕከል ነው፤ ይኼ ማዕከል የተመሠረተ ዕለት እኔ በጣም ስሜታዊ ኾኜ በርካታ ነገሮችን ተናግሬያለሁ፡፡ ጥሩ ነገሮችን ሳይ ለሀገሬ እቀናለሁ፡፡ ሰው ሀገር የማየው መልካም ነገር ሁሉ ያስቀናኛል፡፡ የዚያን ቀንም ተቋሙ ተመሥርቶ በማየቴ እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ አጋጣሚ ኾኖም በዚህ ተቋም ውስጥ የቦርድ አባል ኾኖ የመሥራት ዕድል በማግኘቴ ተደስቻለሁ፡፡

በዚያ ተመርቀው ከወጡት ወጣቶች መካከል 16ቱን ወስጄ ሥራ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ የጋርመንት ኩባንያ አቋቁሜ ከተማ አስተዳደሩ በሰጠኝ ሼድ ውስጥ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ይህን ለማድረግ አስፈላጊ የኾኑ ማሽነሪዎችን በማስገባትና የገበያ ትስስር በመፍጠር አልፎም የሚሠሩትን ነገር ገቢ እንዲያገኙበት በማድረግ አሁን ላይ ጥሩ ገቢ እያገኙበት ይገኛል፡፡ የሚኖሩበትንም የመጀመሪያ ዓመት የኪራይ ቤት ከእነእቃው ችዬ እየኖሩና እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በጣምም ደስተኞች ናቸው፡፡ በጣም ውጤታማም ናቸው፡፡ እኔም በዚህ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡


ግዮን፡- ተቋሙ ወደፊት ምን የመሥራት እቅድ አለው? የልጆቹን ስኬት ሲያዩስ የተሰማዎት ነገር ምንድነው?
ሳራ፡- ለልጆቹ ያለኝ ስሜት የተለየና የቤተሰባዊነት ስሜት ያየለበት ነው፡፡ ሰዓት ሳይገድበኝ በየጊዜው እየሄድኩ አያቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም የመጡበት ሕይወት የኋላ ታሪክ አስቸጋሪ ስለኾነ በየጊዜው ሄጄ የሕይወት ታሪኬን በማጋራት ሥነ ልቦናቸውን ለመጠገን እሞክራለሁ፡፡ በተለይ ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና ከቁጠባ ጋር በተያያዘ ስላሉ ነገሮች በየጊዜው እንወያያለን፡፡ እነሱም በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ አሁንም ከ400 በላይ የሚኾኑ ወጣቶች ለሥልጠና ገብተዋል፡፡ እነሱ ሠልጥነው ሲወጡ ተቋሙም ተመሳሳይ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡


ግዮን፡- አፍሪካን ሆልዲንግ ላይ ያለዎት ኃላፊነትስ ምንድነው?
ሳራ፡- አፍሪካን ሆልዲንግ ለሕብረተሰቡ እንደሼር ካምፓኒ የተቋቋመ ነው፡፡ ከተቋቋመ አራተኛ ዓመቱ ነው፡፡ እኔ የተቋሙ የቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፡፡ በብዙ ነገሮች ላይ ይሳተፋል፡፡ አሁን በቅርቡ ሼር ውስጥ በመግባት የመኖሪያ ቤቶችን እየገነባ ይገኛል፡፡


ግዮን፡- የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማኅበርን በተመለከተስ ምን ይሉናል? በማኅበሩ ውስጥ የእርሶስ ድርሻ ምንድነው?
ሳራ፡- የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማኅበር ላለፉት በርካታ ዓመታት ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ያለፉትን ሰባት ዓመታትም ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ ሲጀምር በራሱ አቅም ብዙ የጣረ ነው፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩ የቦርዱ አባላት ከኪሳቸው አውጥተው ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ እኔም በቅርቡ በዚህ ማኅበር ፕሬዝዳንት ኾኛለሁ፡፡ አሁን ሥራ አልጀመርኩም፡፡ ምክንያቱም ገና የርክክብ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ማኅበሩ በርካታ አባላት ያሉት ነው፡፡ ማኅበሩ ግዴታውን ከመወጣት አኳያ ብዙ ነገሮችን አድርጓል፡፡ ዲያስፖራው ወደሀገሩ ሲመጣ ለሀገር የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ይዞ ይመጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያም በውጭ ምንዛሬው በኩል ያለው ጥቅም ከፍ ያለ ነው፡፡


ግዮን፡- ወደ ቀድመው ተቋም እንመለስና የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ቀጣይ መዳረሻው ምንድነው?
ሳራ፡- ግባችን የጀመርነውን ሥራ ማስፋፋት ነው፡፡ የመኖው ችግር ሲቀረፍ ወደ እርባታ እንገባለን፡፡ ያ ከኾነ ምርታችንን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንሠራለን፡፡ የውጭ ገበያ ላይ ከሠራን በምንዛሬው በኩል ለሀገራችን የሚያስገኘው ጥቅምም ለእኛ የግባችን አካል ነው፡፡


ግዮን፡ ለንግዱ ማኅበረሰብ በተለይ ለሴቶች ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
ሳራ፡- ሴቶች የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ እናት ሲኾኑ ብዙ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚያው ልክም ሴቶች ብዙ እውቀት አላቸው፡፡ የቤተሰብን ማኅበራዊ ግንኙነትና አጠቃላይ አስተዳደራዊ ሂደት መምራት በራሱ አንድ የፋይናንስ የዕውቀት ማዕከል መኾን ነው፡፡ እናት ለሕብረተሰብ የምታበረክተው ነገር ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ለእህቶችና እናቶች ቤተሰብ ብቻ ሳይኾን ተቋማትን መርቶ ሀገርን አገልግሎ መኖር ይቻላል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡


ግዮን፡- ለሀገርዎ ያለዎት ፍቅር ኃያል ኾኖ ይታያልና ኢትዮጵያ ምን ላይ ደርሳ ማየት ይሻሉ?
ሳራ፡- የእኔ ደስታና ሕልም መዳረሻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ተደስቶ፣ ሲያድር ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዜግነታዊ ግዴታውን ተወጥቶ ሁሉም በልቶ ማደር ሲችል ካየሁ ሕልሜ ተሳክቷል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ከሌላው ሀገር እኩል ኾናለች ብዬ እናገራለሁ፡፡ ከምንታወቅባቸው የድህነት፣ የጦርነት፣ የእርስ በእርስ ግጭት ወጥተን እንደማንኛውም እውቀት እንዳላቸው ሀገራት በኢኮኖሚውም አቻ ኾነን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ውጭ የምናያቸው አስደማሚ ነገሮች እኛ ሀገርም ኾነው ማየትንም እሻለሁ፡፡


ግዮን፡- እንደ ማጠቃለያ የሚሉት ሐሳብ ካለዎት?
ሳራ፡- ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ረጅም ዓመት የኖረ ድርጅት እንደመኾኑ መጠን ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው፣ ሀገር ስትፈልገውም ሁሌም ከጎኗ የሚቆም ድርጅት መኾኑን ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡


ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 መጋቢት 20 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...