የወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ምልከት!

Date:


አርቲስት መርዓዊ ስጦት

አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት መርዓዊ ስጦት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ጉልህ አሻራን ካሳረፉ ሁለገብ የጥበብ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ፡፡ አርቲስት መርዓዊ፣ ተተኪዎችን የሚያበረታቱ ፤ በሁለንተናቸው አርአያነትን የተላበሱ፤ ታታሪ የሥነምግባር ሰው፣ ይኽም የተመሰከረላቸው ታላቅና አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ሲኾኑ፣ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ/ም ምሽት 12፡00 ሰዓት አካባቢ በሥራቸው ሕያው ሆነው በተወለዱ በ89 ዓመታቸው ከዚህች ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ/ም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሙያ አጋሮቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት የሽኘት ፕሮግራም የተከናወነላቸው ሲሆን፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በዕለቱ ተከናውኗል፡፡


መጽሔታችን ግዮን ለመላው ኢትዮጵያውያን የጥበብ ወዳጆች የተሰማትን ሐዘን እየገለጸች፣ ከእኚህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ጋር ከዚህ ቀደም በግዮን መጽሔት ቁጥር 2 መጋቢት 2010 ዓ.ም ያደረጉትን ቃለ ምልልስ የተወሰነውን ለትውስታ እንደሚከተለው አቅርባዋለች፡-


ግዮን፡- ስለብሔራዊ ቴአትር አመሠራረት በዚህ አጋጣሚ ብትነግረን?
መርዓዊ፡- ለቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ 25ኛ ዓመት የዘውድ በዓል አሁን የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ባለበት ቦታ ላይ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲሠራ ነበር የፈለጉት። በኋላ ላይ ግን የአሁኑን ብሔራዊ ቴአትር ጣሊያኖች ሲኒማ ማርኮኒ ብለው ጀምረውት ስለነበር እሱን ጨርሳችሁ ግቡ ተብሎ በ3.5 ሚሊዮን ብር ወጪ በሦስት ወር ተጠናቆ ነው በ1948 ዓ.ም በዚያ የገባነው። ቴአትር ቤቱን የሠሩትም የፈረንሳይ አርክቴክቶች ናቸው።


ግዮን፡- ቴአትር ቤቱ ሥራ ሲጀምር ከነበሩት ቀዳሚ ሙዚቀኞች መሀል ነበርክ?
መርዓዊ፡- አዎን እንጂ! ስልሳ የሚሆኑ ሙዚቀኞች ከ1939 ጀምሮ ነው ሲሠለጥኑና ሲሠሩ የነበሩት። እኔ ደግሞ የተቀጠርኩት በ1942 ዓ.ም ነበር። ከመካከላችንም ምርጫ ተካሂዶ ሙዚቃ የምንጫወተው ወደ ሙዚቃ፣ የቴአትር ሙያተኞችም ወደ ቴአትሩ ክፍል ተመደብን። ይህ ከሆነ በኋላ ከቴአትር ቤቱ ኦርኬስትራ አባላት መካከል አንዱ እኔ ሆንኩ ማለት ነው።


ግዮን፡- ከስንት ዓመት አገልግሎት በኋላ ጡረታ ወጣህ?
መርዓዊ፡- በሙዚቃውም ይሁን ለሃያ ሰባት ዓመታት የኦርኬስትራው ኃላፊ ሆኜ ካገልገልኩ በኋላ በ1986 ዓ.ም ነው ጡረታ የወጣሁት።


ግዮን፡- ታዋቂ የሆንክበትን ክላርኔት የተባለ የሙዚቃ መሣሪያ እንዴት ልታጠና ቻልክ?
መርዓዊ፡- ማዘጋጃ ቤት እያለሁ ሙሴ ነርሲስ መረጡኝ። ከዚያ ኃ/ጊዮርጊስ ገመዳ አስተማረኝ። ልጅ ስለሆንኩና አጭርም ስለሆንኩ ነው ክላርኔት እንዳጠና የተደረገው።


ግዮን፡- ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማው ጊዜ የምትለው የትኛውን ዘመን ነው?
መርዓዊ፡- ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስና የጦር ሠራዊት ኦርኬስትራዎች አብረው ሲሠሩ በነበረበት ዘመን ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ብዬ አስባለሁ። የክብር ዘበኞች፤ ከዚህም ከዚያም እያሉ ዓመቱን ሙሉ አስበውበት ነው የሚቀርቡት። ጥላሁን ገሠሠም ከሀገር ፍቅር ወጥቶ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ‹‹ጥላ ከለላዬ›› የሚለውን ዘፈን ሲዘፍን ነው የማውቀው። ጥላሁን ውስጤ ገብቶ የቀረው በዚያን ጊዜ ነው። በ1946 ዓ.ም እኔ የ16 ዓመት ስሆን፤ ጥላሁን 14 ዓመት ነው ብዬ አስባለሁ። የአበሻ ልብስ ለብሶ፣ የቀርክሃ ጃንጥላ ይዞ ሲዘፍን ካየሁት ጊዜ ጀምሮ ዛሬ ድረስ ውስጤ አጠቃላይ ሥዕሉ አለ። እስክሞትም አብሮኝ ይኖራል። ክብር ዘበኛ ጥላሁንን ይዞ፣ ጦር ሠራዊቶች እነታምራት ሞላን፣ እነዓለማየሁ እሸቴን ይዘው፤ በስተኋላ ደግሞ ምኒልክ ወስናቸው፣ ጠለላ ከበደ፣ እነጌጡ አየለ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ ተጨምረው፤ ከፍተኛ የሙዚቃ ዕድገት መጥቷል። እስከ 1966ዓ.ም በእውነት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ጊዜ ነበር ማለት እችላለሁ። እስካሁን ጊዜ ድረስ የሚደመጡት ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች የተሠሩት በዚያን ጊዜ ነው።


ግዮን፡- የደርግ ሥርዐት ለሙዚቃ እንዲሁም ለኪነ-ጥበብ ያለውን ድርሻ፤ አንዳንዶች ለራሱ ፕሮፓጋንዳ አስቦም ቢሆን እንዳስፋፋውና ድጋፍ እንዳደረገለት ሲናገሩ፤ ሌሎች ደግሞ በተለይም ከሳንሱር፣ ከርዕሰ ጉዳይ መረጣና ከትዕዛዝ ጋር አያይዘው፤ በሙዚቃም ሆነ በአጠቃላይ በኪነ-ጥበብ ላይ ጉዳት እንዳደረሰ የሚቆጥሩት አሉ። አንተ ወደየትኛው ነህ?
መርዓዊ፡- ሳንሱር በንጉሡ ጊዜም ነበር። ደርግ ግን ሁሉንም አብዮታዊ አደረገው። በሙሉ አሸገው ማለት ይቻላል። የመዝናኛ ሙዚቃ አልፈለገም። እኛም ደግሞ ስሜታዊ ሆነን ወደዚያው ነው ያዘነበልነው።


ግዮን፡- ወዴት?
መርዓዊ፡- ደርጉ ወደሚፈልገው። ለምሳሌ መሬት ላራሹ የሚለውን ሙዚቃ፤ ከታምራት አበበ ጋር ያዘጋጀሁት አንዱ እኔ ነኝ። በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፈለት መስሎን አብዛኛውን ሙዚቃ ወደ አብዮታዊ መዝሙር የወሰድነው እኛ ነን።


ግዮን፡- ሳትገደዱ በፍላጎታችሁም ትሠሩ ነበር?
መርዓዊ፡- እንደውም እኛ ነን የገፋፋነው። ደርግ ‹‹ያለምንም ደም… ›› ሲል፤ እኛ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ ተነሽ!›› የሚለውን ሙዚቃ አዘጋጀን። የሙዚቃው ግጥም የጸጋዬ ገብረመድኅን ነው። ዜማው የእኔና የሃይማኖት ዓለሙ ሲሆን፤ አቀናባሪው ደግሞ እኔው ነበርኩ። ‹‹አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!›› የሚለውን ዜማ የ1969 ዓ.ም የሶማሌያን ወረራ ምክንያት አድርገን በማዘጋጃ ቤት ስናቀርብ፤ አዳራሽ ሙሉ ሕዝብ ነው የተላቀሰው። ያኔ ‹‹ሀገር ልሙት ወይም አድኑኝ ነው የምትለው›› ሲባል፤ ሕዝቡ አምጾ ነው አደባባይ የወጣው። የሶማሌያው ጦርነት፣ የሰሜንም ጦርነት ተደምሮ፣ ኢትዮጵያዊው ሁሉ እልህ ይዞት፣ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች የነበርነው ሙዚቀኞች አብዛኞቻችን የአብዮቱ ደጋፊዎች ነበርን ብዬ ነው የማምነው። ይህ ምንም ጥርጥር የለውም።


ግዮን፡- ምን ያህል አብዮታዊ ሙዚቃዎችን ተጫውተሃል?
መርዓዊ፡- መዓት ናቸው። ብዙ ሠርቻለሁ፣ አቀናብሬአለሁ። እንደውም ሌላ ሙዚቃ፣ የፍቅር ምናምን ስሠራ ደስ አይለኝም ነበር። እውነቱ ይኼ ነው።


ግዮን፡- በወቅቱ አብረውህ የሠሩ ሁሉ፤ ትልቁም ትንሹም ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ተገዶ እንደሠራህ ነው የሚወራው። አንተ ግን በፍቅር መሥራትህን በግልጽ ተናገርክ። እንዴት ነው ይሄ ነገር?
መርዓዊ፡- እንዴ! ‹‹ገንጣይ አስገንጣይ… ›› ብዬ የዘመርኩት እኔ አይደለሁም? ካሴቱ እኮ በእጃቸው አለ። እዚህ ብሔራዊ ቴአትር መጥተው ሲያነጋግሩን ‹‹እናንተን ከደርግ ለይተን አናያችሁም›› ብለውናል እኮ። በሰላም ስለገቡ እንጂ፤ በጦርነት ቢሆን አንደሚረሽኑን ነው የሚሰማን። ስለዚህ እኛም ዘምረናል፣ እነሱም እየዘመሩ ገብተዋል። ይልቅ የሚቆጨኝ አሁን ነው። ለልማትና ለሀገር ዕድገት መሥራት ሲገባቸው፤ በየቴአትር ቤቱ አይሠሩም። ዓባይን በሚመለከት ጠንካራ ሥራ መች ወጣ? ትልቅ ሙዚቃ የሠሩት ሙሉ ገበየሁና ብንያም ኃ/ሥላሴ ናቸው። ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች… ›› እያሉ በሠሩት መዝሙር እቀናለሁ። ምክንያቱም ዜማው ሕዝባዊ ነው። የሚሠራው ለሀገር፣ ለዓባይ፣ ለዕድገታችን ነው። አይደለም እንዴ? እንዲሁ ከበሮ ለመምታትማ ኢሕአዴግ የራሱ ከበሮ መቺዎች አሉት። ‹‹ዝፈኑልኝ›› አላለም። ለሀገራችሁ ዘምሩ ነው ያለን፤ ዘመርን።


ግዮን፡- በደርግ ጊዜ በሠራሃቸው ሥራዎች ቅሬታ ወይም ጸጸት ይሰማሃል?

መርዓዊ፡- ለምን? እንደውም እኮራለሁ እንጂ! የምን ጸጸት ነው? በሥራዎቼ በጣም እኮራባቸዋለሁ። እኔ ሰው ጠቁሜ አላስገደልኩም። የዘመርኩት ለኢትዮጵያ ዕድገት ነው። አሁንም የጤናዬ ጉዳይ ባያግደኝ ለሀገሬ እሠራለሁ። ነገ ርካሽ የሚሆን ሽንጥና ዳሌ እንዳመሰግን አልፈልግም። እግዚአብሔር ነገ የራሱ ፕሮግራም አለው። ፕሮግራሙ እስኪሟላ መሥራት ያለብን ለሀገራችን ነው።


ግዮን፡- በሥራህ ዓለም አቀፍ የጎልድ ሜርኩሪ ተሸላሚ ሆነሃል። ከአንተ ሌላ ይህን ሽልማት ያገኙት የሀገራችን ሰዎች እነማን ናቸው?
መርዓዊ፡- እነሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤል፣ይድነቃቸው ተሰማና ራሳቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተሸልመዋል። ለዐሥራ ስምንት ሰዎች ሲሰጥ እኔና አንዲት ከገበሬ ማኅበር የመጣች ኢትዮጵያዊት ነን በኑሯችን ዝቅ ያልን እንጂ፤ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ዕንቁ ሰዎች ናቸው። ለምሣሌ እኔ ሽልማቱን ላለመውሰድ ወደ አንድ ወር ገደማ አንገራግሬ ነበር።
ግዮን፡- ለምን አንገራገርክ?


መርዓዊ፡- ጥላሁን ገሠሠን ያህል ትልቅ አርቲስት እያለ ሽልማቱ ለእኔ አይገባኝም ብዬ ነው። መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹ሁለ-ገብ የጥበብ አባት›› ብለው የኢትዮጵያ ባሕል ማእከል ዕውቅና ሽልማት ሲሰጡም ተቃውሜአለሁ።
ግዮን፡- በምን የተነሣ?


መርዓዊ፡- ዐፄ ምኒልክን ሳያከብሩ ለመርዓዊ ሽልማት ቢሰጡ ምን ዋጋ አለው? ዐፄ ምኒልክ በሚሰደቡበት ዘመን መርዓዊ ዘፈነ ተብሎ ሽልማት መስጠቱና ‹‹እናከብርሃለን›› የሚለው አይስማማኝም። መጀመሪያ ምኒልክን ያክብሩልኝ። ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ ሽልማቱን እንኳ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነው የሰጠሁት። ሽልማቱ አብረውኝ የሠሩት ሙዚቀኞች ሁሉ ሽልማት ነው።


ግዮን፡- ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ለጥላሁን ገሠሠ ስላለህ አክብሮት የሚሰማህን ብትነግረን?
መርዓዊ፡- ምኑን ልናገር? ጥላሁን ከ‹‹ጥላ ከለላዬ›› ጀምሮ አንዱም ሥራው ያልወደቀበት ነው። ድምፁ ብቻ አይደለም፤ እንቅስቃሴው ልዩ ነው። እንደሱ ያለ ድምፃዊ ዳግመኛ በዚህች ሀገር ይፈጠራል ብዬ አላምንም። የድምፁ ጣዕም ልዩ ነው። ከተክለ-ሰውነቱ ጀምሮ፣ ሥራው… እጅግ በጣም ነው የማከብረው። የአምልኮት ያህል! እንደውም በእሱ የተነሣ ራሴን ገድያለሁ።


ግዮን፡- እንዴት ማለት?
መርዓዊ፡- አንገቱ ከተቆረጠ በኋላ ወደ መድረክ ሲመለስ፤ የልደቱን በዓል በሚመለከት በብሔራዊ ቴአትር በተሰናዳ ዝግጅት ላይ፣ ‹‹እንኳ አተረፈህ ጥላሁን ገሠሠ፤ ዳግም ልደትህ በሕይወትህ ታደሠ…›› የሚል ግጥምና ዜማ አውጥቼ በወቅቱ የነበረው ሥራ አስኪያጅ ከለከለኝ። ከዚያ በራሴ ፈቃድ ደርግ የጨመረልኝን አምስት ዓመት ትቼ ጡረታዬን በማስከበር ወጣሁ። በዚያም ምክንያት ነበር ራሴን ላጠፋ የነበረው። ሦስት አራት ቀን ራሴን ስቼ ነበር። ጥላሁንም እግዚአብሔር ይስጠው፤ ለሼህ መሐመድ አላሙዲን ተናግሮ አሜሪካ ሄጄ እንድታከም አድርጎኛል። አቶ አብነት ገ/መስቀልን የማውቀው በዚያ ምክንያት ነው። ልቤ ላይ ባትሪ ገብቶልኝ መጀመሪያ 26 ሺሕ፣ በኋላም 36 ሺሕ ብር የከፈለልኝ አብነት ነው። እኔማ ከየት አባቴ አመጣለሁ?


ግዮን፡- ምን ያህል ግጥምና ዜማዎችን ሠርተሃል? የአንተን ሥራዎች የተጫወቱትስ እነማን ናቸው?
መርዓዊ፡- ቁጥሩን አላስታውሰውም። ግን በጣም በርካታ ናቸው። ብቻ በብሔራዊ ቴአትር የባንዱ ኃላፊ ስለነበርኩ አዲስ ዓመት በባተ ቁጥር የራሴን የፈጠራ ሥራዎች አቀርብ ነበር። ከሁሉም ጎልቶ የሚታየኝ ምኒልክ ወስናቸው የተጫወተውና ‹‹አፈር አትንፈጊኝ… ›› የሚለው ነው። ሌላው ‹‹ብዕር! ብዕር›› የሚለውም ነው። ለምሳሌ አርምስትሮንግ ጨረቃን ሲረግጥ አልቅሻለሁ። ወዲያውም ‹‹ጨረቃን በሰው እጅ›› ብዬ ግጥም በመጻፍ ተስፋዬ ሳህሉ ተጫውቶታል።


አንጋፋው አርቲስት መርዓዊ ስጦት ማን ነበሩ?
(1928 – 2017 ዓ.ም)


አንጋፋው አርቲስት መርዓዊ ስጦት እርቁ ከአባታቸው ከአቶ ስጦት እርቁ እና ከእናታቸው ወሮ ዘውዲቱ ፈለቀ በ1928 ዓ/ም ደሴ አምባሰል ውጫሌ አውራጃ ልዩ ስሙ ድብል በሚባል አካባቢ ተወለዱ፡፡


በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት በ1942 ዓ.ም ጀምሮ በሙዚቀኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት በ1948 ዓ/ም ሲከፈት ወደቴአትር ቤቱ ተዛወሩ፡፡ የክላርኔቱ ንጉስ በማባል በአልቶ ሳክስ የክላርኔት ተጫዋች፣ የቶኖር ሳክስን ሙያ ደርበው በአንድ መድረክ መጫወት የሚችሉ ባለልዩ ተሰጥኦ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እድገት ላይ ደማቅ አሻራቸውን ያሳረፉ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ ከተወለዱባት አምባሰል ቢርቁም በክላርኔት አምባሰልን ከሽነው በአስደናቂ ሁኔታ በመጫወት በሙዚቃ መድረክ ላይ ነግሰው ኖረዋል።


አርቲስት መርዓዊ ስጦት የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍልን በኃላፊነት መርተዋል፤ ሀገራቸው በሞያቸው በፈለገቻቸው ጊዜ ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ግንባር ድረስ የተሰለፉ ፤ በሥራቸው እጅግ ታታሪና ጠንካራ ዲስፕሊንን የተላበሱ አርአያ የሆኑ ታላቅ ባለሞያ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር ፤ የሙዚቃ ዝግጅት ግብረሀይል፣ የትዕይንተ ጥበባት፣ የቅስቀሳ ዝግጅት አስተባባሪ ሆነው ሀገራቸው በፈለገቻቸው ቁጥር በየክፈለሀገሩና አፍሪካ ሀገራት በሞያቸው ላሳዩት ትጋት፣ ተባብሮ የመሥራት ፍጹም የሆነ ፍቃደኝነት፣ ለሥራ የዕረፍት ጊዜያቸውን ሁሉ ያለስስት የሚሰዉ ፤ ከፍተኛ የሥራ ዲሲፕሊን የተላበሱ ታላቅ የጥበብ ሰው መሆናቸውን የግል ማህደራቸው ያስረዳል፡፡


ከሙዚቃ ሞያቸው በተጨማሪ የዘመናዊ ኦኬስትራ ሀላፊ፤የውዝዋዜ ክፍል ሀላፊ ሆነው በመሪነት አገልግለዋል፡፡ አርቲስት መርዓዊ ስጦት የግጥማና ዜማ ደራሲ እና አቀናባሪ ሲሆኑ ለአርቲሰት ምኒልክ ወስናቸው፣ ለመልካሙ ተበጀ፣ ለጠለላ ከበደ፣ ለፍቅርተ ደሳለኝ እና ለሌሎች አርቲስቶች ግጥምና ዜማ ደርሰዋል። ሙዚቃ አቀናብረዋል። እኚህ ባለልዩ ተሰጥኦ አንጋፋ ባለሙያ ሙዚቃ በማቀናበር ረገድ የምኒልክ ወስናቸው የእንጆሪ ፍሬ፣ ትዝታ አያረጅም፣ ስኳር ስኳር፣ አፈር አትንፈጊኝ፣ በምድረ ሱዳን ያለሽው፣ ጥቁሯ ጽጌረዳ፣ የመልካሙ ተበጀ፣ ብዕር ብዕር፣ ሰላም ጤና ይስጥልኝ፣ ንቢቱ፣ እንዲሁም የአርቲስት የፍቅርተ ደሳለኝ ልማት ልማት እና ሌሎችንም ሙዚቃዎች አቀናብረዋል።


ከዚህም ባሻገር ከ200 የማያንሱ አብዮታዊ መዝሙሮችን ለሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እና ለሌሎችም በርካታ ታዋቂ ቴአትሮች ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ደርሰዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብም የመጀመርያ የሆነውን የክለቡን መዝሙር የሠሩት አርቲስት መርዓዊ ስጦት ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በደርግ እና በኢህአዲግ ዘመን በተሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ላይ የጋሽ መርዓዊ የትንፋሽ አሻራ ታትሞበታል! ኦርኬስትራውን የመምራትና የማስተባበር ሥራንም በታላቅ ትጋትና ሥነምግባር ተወጥተዋል።


‹‹All Black People Music Festival›› ጨምሮ በናይጄሪያ፣ በግብጽ፣ በሱዳን፣ በቻይና፣ በራሺያ፣ በአሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ሀገራቸውን ወክለው በሞያቸው ተሳትፈዋል። ከሙዚቀኛ ያሬድ ተፈራ ጋር በመሆን አምባሰልና ትዝታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ በካሴትና በሲዲ አስቀረጸው አሻግረዋል። ለዚህ ታላቅ ሥራቸው አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜያት ሽልማትን አግኝተዋል።


★ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ የማበረታቻና የመጻሕፍት ሽልማት፡-
★ በደርግ ዘመን በማስታውቂያ ሚኒስትር የምስጉን ሰራተኛ ወርቅ ተሸላሚ፡★ አለማቀፋዊና ትላልቅ የአለም መሪዎችን ጨምሮ ሳይንቲስቶችና ምሁራን የሚሸለሙት የአለም አቀፍ ጎልድ ሜርኩሪ ሽልማት፡-
★ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የወርቅ ሽልማት፡-
★ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ማህበር የክብር ሽልማት፡-
★ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (ባህል ማዕከል) የክብር ዋንጫ ተሸላሚ።
★ ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ከሽልማቶቻቸው ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ መርዓዊ ስጦት የ 3 ወንድ እና 2 ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ የ6 ልጆች አያት የ1 ልጅ ቅም አያት ነበሩ፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 መጋቢት 20 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ንባብ ለሕይወት ባዛር እየተካሄደ ነው !!!

በንባብ ለሕይወት ፕሮጀክትና በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዘጋጅነት የሚካሄደው...

በኢራን የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ አዲስ መጠነ ሰፊ ጥቃት መታቀዱ ተሰማ

የአሜሪካ ጦር በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት...

የብሔር ፌደራሊዝምን ለማስቀጠል “የቆረጡ” ተመካካሪዎች

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 14ኛ ቀን ውሎ “ስልታዊ” ቡድኖች የአጀንዳ...

“የሩሲያ ክርስቲያኖች ከኢራን ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው” ፓትርያርኩ

የሩሲያ ክርስቲያኖች ከኢራን ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው...