የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢን በተመለከተ የተደነገገው አንቀጽ 29 ድንጋጌ፣ አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ከቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎቶች፣ ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ ከድምፅ ማስተላለፊያ (ፖድካስት) አገልግሎቶችና የቀጥታ ሥርጭት መድረኮች ከሚገኙ ገቢዎች ዓመታዊ ግብር እንዲከፍል ግዴታ ይጥልበታል፡፡
በኦንላይን መድረኮች ዲጂታል ይዘትን በመፍጠርና በማሠራጨት የሚገኝ ማንኛውም ገንዘብ ወይም ገንዘብ ነክ ያልሆነ ገቢ ግብር የሚከፈልበት እንደሆነ ያብራራል፡፡
ማስታወቂያዎችና ስፖንሰርሺፖች፣ የምርት ስምምነቶችና ድጋፎች፣ የአጋርነት ግብይትና የምርት ምደባዎች፣ የደጋፊዎች አስተዋጽኦ፣ የገንዘብ ስጦታዎች ወይም የብዙኃን የገንዘብ ማሰባሰብ (ክራውድ ፈንዲንግ)፣ የዲጂታል ወይም የአካላዊ ሸቀጦች ሸያጭ፣ ለማስተዋወቂያ እንቅስቃሴ የተገኙ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶችና ተመሳሳይነት ያላቸው ሌሎች ክፍያዎች ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ በሚል ግብር ይጣልባቸዋል ተብሏል፡፡
በረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ መረጃዎችን በኬብል፣ በሬዲዮ፣ በኦፕቲካል ፋይበር፣ በቴሌቪዥን ማሠራጫ፣ በአነስተኛ ማሠራጫ ተርሚናል (ቪሳት)፣ በኢንተርኔት ሳተላይት ወይም በሌላ ተመሳሳይ የመገናኛ ዘዴ በማሠራጨት የሚያገኘው ገቢ መረጃው የመነጨው ከኢትዮጵያ ቢሆንም ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ የተገኘ ገቢ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚቆጠር መደንገጉን ሪፖርተር ነው የዘገበው ።
