“ጦርነቱን ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል”
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ፑቲን ሁለቱ መሪዎች በአላስካ የሚያደርጉትን ስብሰባ ተከትሎ፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ፣ “በጣም ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃቸው አስጠነቀቁ።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ረቡዕ ዕለት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው።
የአውሮፓ መሪዎች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቪዲዮ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ፣ ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት በአላስካ ተገናኝተው የዩክሬን ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ትራምፕ የስብሰባው ዓላማ በሞስኮና በኪየቭ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ መሆኑን ለአውሮፓውያን መሪዎች መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
