በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ በመምጣቱ፣ በኢራን የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ያለምንም መዘግየት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ አወጣ።
በኢራን የሚገኘው የአሜሪካ ቨርቹዋል ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ዜጎች አሁኑኑ ከኢራን እንዲወጡ ያሳሰበ ሲሆን፣ ለጉዞአቸውም ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ ሳይጠብቁ በራሳቸው መንገድ እንዲወጡ አሳስቧል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ካስጠነቀቁ በኋላ ውጥረቱ ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል። ፕሬዝዳንቱ የዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን ጨምሮ በርካታ የጦር መርከቦችን ወደ ፋርስ ባህረ ሰላጤ መላካቸውን ገልጸዋል።
ይህ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በአካባቢው ሰፍሮ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ዜጎቻቸው በኢራን ውስጥ የኢንተርኔት መቆራረጥ እና የበረራ ስረዛ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኢራን ባለስልጣናት የመጠየቅ ወይም የመታሰር ከፍተኛ ስጋት እንዳለ በመግለጫው ተካቷል።
ይህ የደህንነት ስጋት መመሪያ የወጣው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሰነዘሩትን ዛቻ ተከትሎ በቀጣናው ያለው ወታደራዊ ዝግጅት በጨመረበት ወቅት ነው።
