የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መስራች አባል የሆኑት አበባው ደሳለው (ዶ/ር) ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲና የፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ማግለላቸውን አስታወቁ።
አበባው (ዶ/ር) ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰራጩት መልዕክት ሲሆን፣ የውሳኔያቸው ዋና ምክንያቶች የህዝቡን በርካታ ችግሮች ለመፍታት በፖለቲካው ያደረጉት ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ ውጤት እንዳላስገኘላቸው መሰማታቸውና ለቤተሰባቸው በቂ ጊዜ መስጠት መፈለጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ጉዟቸውን በማስታወስም፣ አብን ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. 2018 ጀምሮ በንቁ ተሳትፎ እንደቆዩ ጠቅሰዋል። በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫም የአብን እጩ ሆነው የምዕራብ ጎጃምን ጅጋ ከተማና አካባቢዋን በመወከል በማሸነፍ ወደ ፓርላማ መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በ7ኛው ዙር ምርጫም አስቻይ ሁኔታዎች ባይኖሩም፣ ህዝቡ ያለ ውክልና እንዳይቀር በማሰብ በአዲስ አበባ 6 ኪሎ፣ መነንና ሽሮ ሜዳ አካባቢዎች የኢህአፓን ወክለው መወዳደራቸውን፣ ሆኖም ውድድሩ እንዳልተሳካ አብራርተዋል።
በፓርላማ ቆይታቸውና በምርጫ ክርክሮች ወቅት በህዝቡ ላይ እየደረሱ ያሉ የሰላም እጦት፣ የኢኮኖሚ፣ የልማትና የፖለቲካ ችግሮችን ያለ ፍርሃት በትጋት ሲያነሱ እንደቆዩ ገልጸዋል። በተለይም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች በፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈቱ ጥረት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ያለ ፍርድ ከሶስት ዓመታት በላይ በእስር ሲንገላቱ የነበሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ በትጋት እንደታገሉ ገልጸው፣ አብዛኞቹ መፈታታቸው እንዳስደሰታቸውና ቀሪዎቹም መፈታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በአርሲና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶችንም በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ድምፃቸውን ማሰማታቸውን ጠቁመዋል።
ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን ቢያገልሉም፣ ወደፊት በተማሩበት የቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ዘርፍ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ሥራዎች ሙያቸውን በመጠቀም ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አበባው (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
