የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ ለ12 ቀናት ከኢራን ጋር ሲካሄድ የነበረውን ድንበር ዘለል ግጭትን ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያስታወቁት ማክሰኞ ማለዳ ላይ ነው።
ነገር ግን ከረፋድ ጀምሮ ሁለቱም አገራት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከሱ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱ አለመከበሩን ሲገልጹ ነበር።
ለእስራኤል በማገዝ ዕሁድ ዕለት ከባድ የቦንብ ድብደባ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የፈጸመችው አሜሪካ እና ሰኞ ምሽት የተወሰኑ ሚሳዔሎች የተተኮሱባት ኳታር ያሳኩት እንደሆነ የተነገረለት የተኩስ አቁም ዕውን እየሆነ ይመስላል።
ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁሙን በመጣስ መካሰሳቸውን ተከትሎ በአገራቱ ላይ ቁጣቸውን የገለጹት ትራምፕ በተለይ በወዳጃቸው እስራኤል ላይ ጠንከር ያለ ቁጣ ከመሰንዘራቸው በተጨማሪ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒኣሁ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
ከሁለቱ አገራት በኩል ለቀናት በዘለቀው ግጭት የመጨረሻ የነበሩት ጥቃቶች ሌሊት ላይ ኢራን ወደ እስራኤሏ ቤርሼባ የተሰነዘረው እና የሰው ሕይወት የጠፋበት ጥቃት ሲሆን፣ በእስራኤል በኩል ደግሞ በሰሜናዊ ኢራን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
የተኩስ አቁሙ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ይፋ ከሆነ በኋላ ኢራን እና እስራኤል ጥቃቱ መቀጠሉን እና አጸፋ እንደሚመልሱ ከገለጹ በኋላ ግጭቱ እንደማይቆም ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከሰዓት በኋላ መጠቃቃቱ ጋብ ብሎ ተኩስ አቁሙ የያዘ መስሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የጦር አውሮፕላኖቻቸው ጥቃት እንዲያቆሙ ያዘዙ ሲሆን፣ የኢራኑ ፕሬዝዳን ማሱድ ፔዜሽኪያን እስራኤል ጥቃቷን እስካቆመች ድረስ አገራቸው ተኩስ አቁሙን እንደምታከብር አሳውቀዋል።
BBC Amharic
