ግዮን መጽሔት :- በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሰው ልጅ ሥልጣኔን ወደፊት የገፋው፣ አዳዲስ የሳይንስ ውጤቶችን ያስገኘውና ምድራችንን የለወጠው ዋነኛው ሞተር ‹‹የመጠየቅና የመመርመር ጥበብ›› ነው፡፡ የለንደኑ ጥንታዊ የሳይንስ ተቋም ‘ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች’ ዳይሬክተር ፓዲ ሮጀርስ በቅርቡ ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ ግን ይህ የሰው ልጅ መገለጫ የሆነው የማሰብና የመመራመር አቅም አደጋ ላይ መውደቁን በግልጽ ያሳያል፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም ኤአይ (AI) ውስብስብ ለሆኑ ጥያቄዎችና ችግሮች ቅጽበታዊና ዝግጁ መልሶችን ይዞ በከፍተኛ ፍጥነት ብቅ ማለቱ፣ በገጽታው ታላቅ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና ምቾት ቢመስልም፣ በውስጥ በኩል ግን የሰውን ልጅ ወደ ማሰብ ስንፍና እና ወደ ፍጹም ጥገኝነት እየገፋው መሆኑን የሳይንስ ሊቃውንት በከፍተኛ ስጋት መናገር ጀምረዋል፡፡ በፍጥነት በሚመጡ መልሶች ላይ ብቻ መተማመን፤ ለእውቀት፣ ለሙያዊ ብቃት እና ለፈጠራ መሠረት የሆኑትን የመጠየቅ፣ የመጠራጠርና የመመርመር ልምዶች ደረጃ በደረጃ እንዲጠፉ የማድረግ አደገኛ ዕድል አለው፡፡
የሰው ልጅ ለአንድ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በራሱ ጥረት በሚያደርገው የምርምር ጉዞ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ያልተጠበቁ ጠቃሚ መረጃዎችንና እውቀቶችን ያገኛል፡፡ አንድን መጽሐፍ ገልጦ ሲያነብ፣ በቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ሲፈልግ ወይም ታሪካዊ ሰነዶችን ሲያገላብጥ ካለመው አጀንዳ ውጭ የሆኑ፣ ነገር ግን ለሌላ ታላቅ እውቀት በር የሚከፍቱ እውነታዎችን ያጋጥመዋል፡፡ ለምሳሌ ቀደምት የከዋክብት ተመራማሪዎች መረጃዎችን ሰብስበውና ደክመው ሲያከማቹ ዛሬ ላለንበት የጠፈር ጉዞ እና የአየር ንብረት ምርምር ታላቅ ሀብት እንደሚሆን አላወቁም ነበር፡፡ የምርምር ጉዞው ራሱ አእምሮን የሚያሰልጥ፣ አዳዲስ የፈጠራ መስመሮችን የሚዘረጋ እና የማገናዘብ ክህሎትን የሚያዳብር ሂደት ነው፡፡ የኤአይ መተግበሪያዎች ግን ይህንን የመንከራተት፣ የመማርና የመታገል ጉዞ ሙሉ በሙሉ ያሳጥሩታል፡፡ ጥያቄውን እንዳቀረብንለት የተጠቃለለ እና የተበጠረ መልስ በቀጥታ ስለሚሰጠን፣ ተጠቃሚው መልሱን ቢያገኝም ከመልሱ ጀርባ ያለውን ሰፊ እውቀት፣ የመከራከሪያ ነጥቦችን እና የታሪክ ድርድርን ሳያውቅ እና ሳይረዳው ያልፋል፡፡ ዝግጁ ምግቦችን ማዘውተር የሰውን አካላዊ ጤንነት እንደሚያውከው ሁሉ፣ ዝግጁ መረጃዎችን ብቻ መመገብም የአእምሮን የመተንተን፣ የማብሰል እና የማመራመር ብቃት ያደክመዋል፡፡
በኢንተርኔት ታሪክ ውስጥ እንደ ዊኪፒዲያ ያሉ የቀድሞ መገልገያዎች መረጃን በስፋት ተደራሽ ቢያደርጉም፣ አንድ ትልቅና ጠቃሚ ሥርዓት ነበራቸው፤ እሱም ተጠቃሚው ወደ ዋናው የመረጃ ምንጭ ሄዶ እውነተኝነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያስገድዱ የግርጌ ማስታወሻዎችንና ማጣቀሻዎችን ማስቀመጣቸው ነው፡፡ ይህ አሰራር ተጠቃሚው መረጃውን በጥርጣሬ እንዲያይና ራሱ ሄዶ እንዲመረምር ያበረታታ ነበር፡፡ በአንጻሩ የዛሬዎቹ የኤአይ ቻትቦቶች መልስ የሚሰጡት በማጠቃለያ መልክ ነው፡፡ መረጃውን ከየት እንዳመጡት፣ እንዴት እንዳቀናጁት እና ምን ያህል እውነተኛ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ የመጨረሻ ውሳኔ አስመስለው ያቀርቡታል፡፡ ይህ ደግሞ በሰዎች ዘንድ ኤአይ የነገረው ሁሉ ፍጹም ትክክል እንደሆነ የመቀበል ጭፍን እምነትን ይፈጥራል፡፡ ሰዎች መረጃን በራሳቸው የመመርመር፣ እውነትና ሀሰትን በራሳቸው ሚዛን የመለየት ልምዳቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ማንኛውም ክህሎት ወይም ሙያዊ ብቃት የሚዳብረው በሥራ እና በስህተት ሂደት ውስጥ አእምሮን በማድከም ነው፡፡
አንድ ጸሐፊ ድርሰት ሲጽፍ፣ አንድ መሐንዲስ ንድፍ ሲነድፍ ወይም አንድ የሕግ ባለሙያ ክርክር ሲያዘጋጅ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች የአስተሳሰብ አድማሳቸውን ያሰፉታል፡፡ ዛሬ ግን በጽሑፍ፣ በምሥል፣ በቪዲዮ እና በድምፅ የሚሰሩ የኤአይ መገልገያዎች እነዚህን ሁሉ የፈጠራ ሥራዎች በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ ሰርተው ማቅረብ በመቻላቸው፣ የፈጠራ ስራዎች በኤአይ በተወሰዱ ቁጥር የሰው ልጅ የራሱን የማሰብ ጡንቻ የመጠቀም ዕድሉ እየጠበበ ይሄዳል፡፡ ማሰብን እና መፍጠርን ለቴክኖሎጂ አሳልፎ የሰጠ ትውልድ ደግሞ ውሳኔዎችን የማመዛዘን እና አዳዲስ ፍልስፍናዎችን የመውለድ አቅሙ የኮሰመነ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ይህ ቀውስ ከአስተሳሰብ መዳከም አልፎ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ገጽታዎች አሉት፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደ ቀላል ረዳት ወይም መሳሪያ ብቻ የሚታዩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን የኤአይ ቻትቦቶች የሰዎችን ስሜት በሚረዱ፣ በሚያጽናኑ እና የቅርብ ወዳጅ በሚመስሉ መንገዶች እየተቀረጹ በመሆናቸው፣ በሰዎች እና በማሽኖች መካከል የሚፈጠር የእውነት ያልሆነ ምናባዊ ትስስር የሰዎችን እውነተኛ ማኅበራዊ ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል፡፡ ከሰዎች ጋር ከመወያየት፣ ከመከራከርና ሐሳብን ከመግለጽ ይልቅ ሁልጊዜ እኛን የሚስማማንንና የምንፈልገውን ብቻ የሚነግረንን የኤአይ ረዳት መምረጥ ማኅበራዊ መገለልንና የሐሳብ መገዳደርን ያጠፋል፡፡ በተጨማሪም፣ ምሥል ፈጣሪ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች እጅግ አደገኛ በሆነ ፍጥነት እውነተኛ የሚመስሉ ነገር ግን የሐሰት የሆኑ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን እያመረቱ በመሆናቸው በሕብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን የዕምነትና የእውነት ትስስር የሚበጥሱ ናቸው፡፡ ያየኸውን አትንካ፣ የሰማኸውን አትመን የሚለው ብሂል ተጠናክሮ፣ የሰው ልጅ እውነተኛውን ዓለም ከምናባዊው ዓለም መለየት ወደማይችልበት የታወከ የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡
ቴክኖሎጂው ለአሥርት ዓመታት በሰዎች ሳይታዩ የቆዩ የኮዲንግ ስህተቶችን በማውጣት፣ ውስብስብ የሕክምና ምርምሮችን በማፋጠን እና የእለት ተእለት ሥራዎችን በማቀለል ረገድ የሚደነቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ባይካድም፣ ዋናው አሳሳቢ ችግር ያለው በቴክኖሎጂው መኖር ሳይሆን እኛ በምንጠቀምበትና ሙሉ በሙሉ ጥገኞች በምንሆንበት መንገድ ላይ ነው፡፡ ይህንን የሰው ልጅ የማሰብ አቅም የመዳከም አደጋ ለመከላከል ኤአይን እንደ መነሻ እንጂ እንደ መድረሻ አለመጠቀም ፍጹም ወሳኝ ነው፡፡ ማንኛውንም የኤአይ ውጤት እንደ መጨረሻ እውነት ከመውሰድ ይልቅ፣ ለተጨማሪ ፍለጋ እና ምርምር እንደ ማነቃቂያ መነሻ ማድረግ ይገባል፡፡ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎች መረጃን እንዴት እንደሚመረምሩ፣ ምንጩን እንደሚያረጋግጡ እና በራሳቸው አመክንዮ እንደሚሞግቱ የሚያስተምሩ የሂስዊ አስተሳሰብ ስልጠናዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡ ከተዘጋጁ የኤአይ መልሶች ወጥቶ መጽሐፍትን በተመስጦ የማንበብ፣ በእጅ የመጻፍ እና በቡድን በመሆን የሃሳብ ፍጭት የማድረግ ባህልን ማደስ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጅ የፈጠረው ታላቅና ረቂቅ መሳሪያ ነው፡፡ ነገር ግን መሳሪያው ተጠቃሚውን መግዛትና መምራት ሲጀምር የሥልጣኔ አቅጣጫ ይዛባል፡፡ ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች እንዳሳሰበን፣ በኤአይ ላይ የሚኖር ፍጹም የሆነ ጥገኝነትን ማስወገድ የአስተሳሰብ ነጻነታችንን የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ ፈጣን መልሶች ጊዜን ሊቆጥቡልን ይችላሉ፤ ነገር ግን የአእምሯችንን የማሰብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተፈጥሯዊ ጸጋ ሊቀሙን አይገባም፡፡ የሰው ልጅ የራሱን ጥረት፣ ድካም እና የምርምር ጉዞ ጠብቆ ካላስቀጠለ፣ በራሱ የፈጠራ ውጤት ተበልጦና ተደንቁሮ የማሰብ አቅሙ የሰለለ እና ለማሽኖች እጅ የሰጠ ትውልድ መፈጠሩ የማይቀር እውነታ በመሆኑ፣ ከወዲሁ ቆም ብሎ ማሰብና ሚዛንን መጠበቅ ይገባል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 234 ግንቦት 2018 ዓ.ም
