የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች

Date:

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና የቅዱሳን አበው ሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ

“ተጋብኦቶሙ ለኤጲስ ቆጶሳት ወውእቱ በኵሉ ዓመታት ፪ተ ጊዜ፤ ወዳግሚትኒ አመ ፲ወ፪ ለጥቅምት”

የኤጲስ ቆጶሳት መሰባሰብ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን ሁለተኛዋም ጉባኤ በጥቅምት 12 ቀን ትሁን”
በሚለው ጥንታዊ ቀኖና መሠረት ከጥቅምት 12 – ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም. ስብሰባውን ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡
ልዑል እግዚአብሔርን አጋዥና መሪ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ወቅታዊ ስለሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት፣ ስለ ሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነት ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በተለይም ወቅታዊ ስለሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች፣ ስለ ሀገር ሰላምና የሕዝብ አንድነት በስፋት ተወያይቶ ተገቢ ውሳኔዎችን አሳልፏል
በዚሁ መሠረት፡-
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሀገራዊ ሰላምና በወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ ሀገራዊ የጸሎትና የምሕላ አዋጅ በማስተላለፍና ሌሎች ጥረቶችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ለመላው ሀገራችን ዘላቂ ሰላምና እድገት እንዲገኝ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑዕ ያሳስባል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ ካህናት፣ ንፁሐን ምእመናንና በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የጅምላ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያወገዘ፣ ይኽ ድርጊት እንዲቆም፣ ወንጀለኞች ለፍረድ እንዲቀርቡ፣ የምእመናን የእምነት ነፃነትና የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት እንዲከበር ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን በአጽንዖት ያስተላልፋል፤

በአርሲ ሀገረ ሰብከት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናን ልጆቻችንን ታሳቢ በማድረግ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦች፣ በአጠቃላይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ መድረስ ይቻል ዘንድ የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሰብሳቢነት የተቋቋመ ሲሆን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ባንክ ቁጥሩም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000 779 196 651 በአባይ ባንክ 1841 1131 1733 9013 እና ሌሎች ወደፊት በኮሚቴው እንደሚገለጹ እየገለጽን ሁላችንም ለወገኖቻችን የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንድናደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፤

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን የሚወክሉ ዐሥራ ስድስት ብፁዓን ሊቃና ጳጰሳት ከፍተኛ የመንግሥት አካልን ለማነጋገር ቅዱስ ሲኖዶስ የወከለ ሲሆን የችግሩን ምንጭ የሚያጣራ የጥናት ኮሚቴ እንዲሰየም ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፤

የበዓለ ሃምሳ ወይም በዓለ ጰራቅሊጦስ ቀደም ሲል በሀገራችን ብሔራዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓል የነበረ ሲሆን፤ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ከወረደበት ከመጀመሪያው በዓለ ሃምሳ ጀምሮ ያለማቋረጥ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲከበር የኖረው በመሆኑ ይኽ ታላቅ በዓል እንደ ሌሎቹ ዓበይት በዓላት ማለትም በዓለ ልደትና በዓለ ትንሣኤ በሁሉም የሀገራችን ክፍልና በመላው ዓለም ባለችው ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት እንዲከበር ተወስኗል፣

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራዊ ምክክር ሂደት አወንታዊና መልካም ተሳትፎን ያደረገች ሲሆን በዚህ ሀገራዊ መርሐ ግብር ቤተ ክርስቲያናችንን ወክለው የተሳተፉ ልዑካንን በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ እያመሰገነ፣ በቀጣይም በቅድመ ምክክር እና በምክክሩ ወቅት እንደተደረገው የቤተ ክርስቲያናችን ተሳትፎው እንዲቀጥልና ክትትል እንዲደረግ ቋሚ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲሰየም ሲል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፤

የወላይታ ሀገረ ሰብከት ያቀረበውን የመንፈሳዊ ኮሌጅ ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው ያጸደቀ ሲሆን የቀድሞው የወላይታ ካህናት ማሰልጠኛ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት መንፈሳዊ ኮሌጅ” ተብሎ ወደ ኮሌጅነት እንዲያድግና የባሕር ዳር ሀገረ ሰብከት ጽርሐ ጽዮን መንፈሳዊ ኮሌጅ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ” ተብሎ እንዲጠራ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉበኤ ወስኗል፤

በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ – አሶሳ አህጉረ ሰብከት የተፈጠሩት የሃይማኖት ቀኖና ጥሰት፣ የአስተደዳር ሥራ ክፍተትና የፍይናንስ ጥፋቶችን አስመልክቶ በተደረገው ማጣራት የአህጉረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ምልዓተ ጉባኤውን በጽሑፍ ይቅርታ በመጠየቃቸው፤
እስከ 2019 ዓ/ም የግንቦት ርክበ ካህናት ድረስ በደብረ ሊባኖስ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት ገዳም በጸሎት እንዲቆዩ ተወስኗል፣

አዲስ አበባ ሀገረ ሰብከትን በተመለከተ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት አጣሪ መሰየም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፡-
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመሩት ከመንበረ ፓትርያርክ አራት የሥራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ኮሚቴ የተሠየመ ሲሆን ኮሚቴው የማጣራት ውጤቱን ለግንቦት ርክበ ካህናት ምልዐተ ጉባኤ እንዲያቀርብ፣

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የሐድያና ስልጤ ሀገረ ስብከትን ብቻ እየመሩ እንዲቆዩ በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

የአባቶች ምደባ የሚያስፈልጋቸው አህጉረ ሰብከትን በተመለከተም
ሀ) ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር) የጋምቤላ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣
ለ) ብፁዕ አቡነ ሰላማ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣
ሐ) ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ሀገረ ስብከትን ደርበው እንዲመሩ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰነበተባቸው ቀናት ስለ ሰው ልጅ ክብር፣ ስለ ሀገር እና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ድኅንነት በየቀኑ በጋራ በመጸለይ ጉባኤውን ሲያካሂድ ቆይቷል፤
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ዛሬ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምን ትፈልጋለች፣ ምእመናን ደኅንነትና የተረጋጋ አኗኗርን ይሻሉ፣ መላው ኢትዮጵያውያንን ዜጎቻችን ማኅበራዊ እድገትና የተሻለ የአኗኗር ዘይቤን ይመኛሉ፤
ስለሆነም ያለፉ ቅራኔዎች በዕርቅና በይቅርታ ተፈትተው፣ በእኩልነትና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ዘመን እንዲሆን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡

በዘመናችን በመላው ዓለም እየተከሰቱ ያሉ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የሚቀጥፉ፣ አካልን የሚያጎድሉ፣ ንብረትን የሚያወድሙ፣ የሰውን ልጅ ከመኖሪያ ቀየው የሚያፈናቅሉ፣ የሰላም አለመኖር ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ፣ አለመግባባቶችና ግጭቶች በሰላማዊ ውይይትና ምክክር እንዲፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን እያስተላለፈ ምልዓተ ጉባኤው ለ13 – ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ በዛሬው ዕለት በሰላም ፈጽሟል፤

ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ሰላምና ፍቅርን፣ ለሕዝቧ ሁሉ አንድነትና ደኅንነትን እንዲሰጥልን በቸርነቱ ይርዳን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...

ፍልውሃ እና ሶደሬ!

ከሐዉለት አህመድ በቀደም ከብዙ ዓመታት በኋላ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ሔጄ...