የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በኒውዮርክ ከ80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በ3ኛው የብሪክስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር የብሪክስ አባል አገራት ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ እርምጃቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ግጭቶች እና ሰብአዊ ቀውሶች በልማት ላይ የሚያሳርፉትን ተፅዕኖ ለመቀነስ ብሪክስ ሰላምን በማፅናት፣ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በማጠናከር እና ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት ታሪካዊ ዕድል እንዳለው አምባሳደር ሃደራ ገልጸዋል።
በሪዮ ጉባዔ የጸደቀው የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሏት አስተዳደር እና በሽታዎችን ለመከላከል የተደረሰው ውሳኔ ለብሪክስ ሁነኛ መመሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለጋራ መገናኛ ብዙኃን መግለጫው የኢኮኖሚ፣ፋይናንስ እና የንግድ ጉዳዮች ቀዳሚ ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያደርገውን በሕንድ የቀረበውን ኢኒሼቲቭ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
የብሪክስ አባልነትን የማስፋት ጉዳይን በተመለከተ አምባሳደር ሃደራ ሦስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል። መግለጫዎችን ወደ ተጨባጭ ውጤት መለወጥ፣ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ፍትሃዊ ማሻሻያ እንዲደረግ መገፋፋት እና ”Global South”ን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እና በአገሮች መካከል ሰላማዊ እና ወዳጃዊ ግንኙነትን በመፍጠር አርአያነትን ማሳየት በማለት አስቀምጠዋል።
“ሰላምን እና ደኀንነትን ማስጠበቅ ሁሉም ሰዎች የተሻለ ሕይወትን ለመምራት እኩል እድል እንዲያገኙ እንደሚያስችል ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የጋራ ጥረት ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አምባሳደር ሃደራ አረጋግጠዋል።
የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን የጋራ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫን በማጽደቅ መጠናቀቁን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃውን አድርሶናል።
NBC Ethiopia
