የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ 42 በተናጠል፣ 15 በሁለት የተለያዩ ቅንጅቶች እና በአንድ ግንባር ፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገባቸውን፣ የግል ዕጩዎችም እንዲሁ በመመዝገብ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።
ሆኖም ግን የፓለቲካ ፓርቲዎች የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በሚቆየው የዕጩዎች የምዝገባ የጊዜ ሠሌዳ ውስጥ ምዝገባውን ለማጠናቀቅ እንደማይችሉ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ እንዲራዘምላቸው ቦርዱ ባዘጋጃቸው የተለያዩ የምክክር መድረኮች ላይ እንዲሁም በጽሑፍ ጭምር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ቀናቱን ማራዘሙን ቦርዱ ገልጿል።
በምዝገባው ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን የመመዝገብ ሂደት የተስተዋሉ ተደጋጋሚ የዕጩ መረጃዎችን መቀያየር፣ ያልተሟላ መረጃ ማቅረብ፣ እንዲሁም በሕጉ ላይ የተቀመጠውን የዕጩነት መሥፈርትን ያለማሟላት በምዝገባው ሂደት የታዩ ችግሮች ናቸው ብሏል።
ስለሆነም ቦርዱ ፖለቲካ ፓርቲዎቹና የግል ዕጩዎች በተቀመጠው ጊዜ ዕጩዎችን ለማስመዝገብ እና በዕጩነት ለመመዝገብ ያልቻሉባቸውን ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ይጠናቀቃል የተባለውን የዕጩዎች ምዝገባ የጊዜ ገደብ ወደ የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ማራዘሙን አስታውቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ምዝገባውን የሚያካሂዱላቸውን የሲስተም አስተዳዳሪዎች ለቦርዱ አሳውቀው በሁለት ዙር ሥልጠና እንዲወስዱ፤ በተጨማሪም የምዝገባ ሂደቱን በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስችል “ማንዋል” እና የምዝገባ ቅደም ተከተል የሚያሳያ “ቪዲዮ” ማጋራቱን ጠቁሟል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች በሲስተም አስተዳዳሪዎቻቸው አማካኝነትና የግል ዕጩዎች በራሳቸው በሚያደርጉት የምዝገባ ሂደት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጡ የቦርዱ የአይ.ሲ.ቲና የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ ሥራ ክፍል ባለሞያዎች በነፃ የስልክ መስመር 7555 እንዲሁም የሲስተም አስተዳዳሪዎችን ያካተተ “ቴሌግራም ግሩፕ” በመክፈትም ጭምር ሞያዊ እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል ብሏል።
