የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫ በጠቅላዩ አንደበት

Date:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ቀርበው በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምለሻቸውም ስለኢትዮጵያዊነት በተለይም ብዙዎች ስለሚተቹት የለውጥ ወቅትና የለውጥ ማግስት ሁኔታዎች እንዲሁም በዚህ ሂደት ውስጥ መንግሥታቸው ስለገጠመው ፈተና ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከማንነት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ በኢትዮጵያ በርከት ባሉ ሰዎች ላይ የማንነት አረዳድ ችግር እንደሚታይ አንስተው የሰው ልጅ በአንድ ማንነት ብቻ ሊገለጽ አይችልም ብለዋል።

“ማንነትን በአንድ ነገር ብቻ ስንገልጽ፣ አንደኛውን አጉልተን ሌላውን ማኮሰስ ስንጀምር የኢትዮጵያዊነት ምንነት እና ትርጉም ትክክለኛውን ሚዛን ይስታል”ም ሲሉ ገልጸዋል።

“ለምሳሌ እዚህ ቤት ውስጥ 100 ኢትዮጵያውያን ብንኖር መቶ የምንሞላው ኢትዮጵያዊ ስንሆን ነው፤ እዚህ ካላችሁ ሰዎች መካከል ወንዶች 60 ልንሆን እንችላለን፤ ከወንዶች መካከል የብልጽግና አባላት ተለዩ ቢባል ደግሞ 20 ልንሆን እንችላለን፤ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት ሲቪል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ተለዩ ብንባል ደግሞ 3 ልንሆን እንችላለን… ሁሉም የምንለይበት፣ የምንገለጽበትን ነው፤ ሁሉም የሚወድቀው ግን በኢትዮጵያዊነት ሥር ነው” ብለዋል።

ከኢትዮጵያዊነት በታች ያሉ ማንነቶች አሉ፤ ነገር ግን እያነሱ ይሄዳሉ፤ ወደ ትልቁ፣ ወደ ሚሰበስበን፣ ወደሚያጸናን እና ወደሚያዘልቀን ማንነት ይሰበሰባሉ” ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያዊነት ምንነት ላይ ሳንግባባ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መነጋገር አስቸጋሪ መሆኑን በማንሣትም፣ የኢትዮጵያውያን ሕብር ማንነቶች የመለያየት ምክንያት እንዳይሆኑ እንደ አንድ ቤተሰብ የሚያደርግ አሰባሳቢ ትርክት ያስፈልጋል ብለዋል። 

“ማንኛውንም ትልሞቻችን ልናሳካ የምንችለው በግዙፉ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ውስጥ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ትርክት ነው” ሲሉ ነው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

በአሰባሳቢው የኢትዮጵያዊነት ማንነት ውስጥ ቀጣይ ትልሞችን ለማሳካት ለነገ የሚሆን እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

በቅርቡ በፈረንሳይ የኖተርዳም ካቴድራልን መጎብኘታቸውን በማስታወስም፣ ቤተ ክርስቲያኑን ጀምሮ ለመጨረስ 200 ዓመታት መፍጀቱን ጠቁመዋል።

ይህ የሚያሳየው ታዲያ የዚህ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ የጋራ የሆነ ፈረንሳዊ ጥቅም እንጂ የግለሰቦች ወይም የኩባንያዎች ጥቅም ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ብሔራዊ ጥቅም ከግል መሻት የተሻገረ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ መካከል የሚጸና ነው፤ ኢትዮጵያዊነትም የሚጸናው በዚሁ እሳቤ ነው ሲሉ አስምረውበታል።

ኢትዮጵያውያን ሀገርን ለማፅናት ብዙ ትብብር ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው የኢትዮጵያውያን ዕጣፈንታ እስከ ሞት ድረስ ከሀገራቸው ጋር የተሳሰረ መኾኑን አንስተዋል፡፡

ማሳያ ይኾን ዘንድም   “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” የሚል የራሳቸውን ንግግር በመጠቀም “አንድ ወዳጄ ‘ይህ ንግግር ‘አግላይ’ ነው፤ ምክንያቱም ‘ስንኖር ዳያስፖራ ስንሞት ኢትዮጵያ’ የምንኾን አለን” ብሎኛል ሲሉ አስታውሰዋል።

በተለይ ዳያስፖራው ሕይወቱ ሲያልፍ እንኳን የመጨረሻ ማረፊያውን በኢትዮጵያ ማድረግን ይመርጣል ነው ያሉት።

“እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ለዚህ ምኞታቸው የሚያቀርቡት ምክንያት አሳማኝ ላይኾን ይችላል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ይህ የወገኖቻቸው ምኞት እንዲሳካ ሲረባረቡ ይታያሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

“እንዲህ ለሀገር ያለ መውደድን ከሞት በኋላ እንኳን ለማረፊያ የሚመኟትን ሀገር በሕይወት እያሉ በሚሠራው ሥራ ላይ ደካማ ነው” ሲሉ ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል።

“ሰው ሞቶ እንኳን የመጨረሻ ማረፊያው ሀገሩ እንድትኾን የመመኘቱን ያህል የሚወዳትን፣ ለማረፊያው የሚመኛትን ሀገር ለማፅናት ግን በሚገባ ሲተጋ አይታይም” ብለዋል።

በመኾኑም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው መፃኢ የተሻለ እንዲኾን እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጡን ዋዜማ በተመለከተ “የትኛውም ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት እኛ ከወሰንነው ውሳኔ ውጭ ምርጫ አይኖረውም ነበር” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡

ነገር ግን ውሳኔዎች ሁሉ እንደተጠበቀው በጎ ምላሽ ብቻ እንደማይኖራቸው ጠቅሰው፣ ያለው አማራጭ ውሳኔ ወስኖ ጉዳቱን መቀነስ ወይም ጉዳት ፈርቶ አለመወሰን እንደኾነ ገልጸዋል።

ጉዳትን ፈርቶ ውሳኔ መወሰን ካልተቻለ ባለበት መቀጠል ስለሚኾን ግን ውሳኔ ወስኖ የውሳኔው ጥቅም እንዲጎላ መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ይህ አካሄድ ኃላፊነት የሚሰማው አካል የሚከተለው መንገድ በመኾኑ የፖለቲካ እና የሚዲያ ዐወዱ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ክፍት እንዲደረግ መወሰኑን ገልጸዋል።

በወቅቱ ክፉውን ከበጎ የሚለይ ተቋም ስላልነበረ ለሁሉም መድረክ የመስጠት ውሳኔ እንደተወሰነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህ ደግሞ ሕዝብ መዝኖ እንዲወስን ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለውጡ ማግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉ ያተረፍንበት ውሳኔ ነው ያሉ ሲኾን በለውጡ የተቀበልናት ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ የነበረች መኾኗን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት፣ 59 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ ዕዳ የነበረባት፣ በመሬት አቀማመጥ እስረኛ የኾነች፣ የተቋም ድቀት የነበረባት እና በርካታ አሳሪ ሕጎች እንዲሁም ከፋፋይና በታኝ ትርክት የተስፋፋባት ነበረች ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሚድያ እና የፖለቲካ ዐውዱ የተሳከረ እንደነበረ አውስተው፤ በወቅቱ የነበረው ጥያቄ “እንፈርሳለን አንፈርስም” የሚል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ያለ ሀገርን የሚመራ መንግሥት ጠንከር ያለ ፈታኝ ውሳኔዎችን መወሰን እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡

ውሳኔዎቹ ሙሉ በሙሉ መልካም ግብረ መልስ ይኖራቸዋል ማለት ባይኾንም መደረግ ያለበት ጥቅሙን ማጉላት እና ጉዳቱን መቀነስ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡

በመኾኑም በነበረው ዐውድ ሚዲያውን፣ የፖለቲካ ሁኔታውን፣ የተቋማት ግንባታውን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ፣ እስረኞች እንዲፈቱ በመወሰን የፖለቲካ ሁኔታውን ለመቀየር መሠራቱን አስረድተዋል፡፡

“የተፈታው እስረኛ ሁሉ ለሀገር ጠቃሚ ነው፤ ወንጀል ሳይሠራ ጥፋት ሳያጠፋ ነው የታሰረው ብለን ሳይኾን ከነበረው የተቋም ስብራት አንፃር ይህንን ለመለየት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ነው” ብለዋል።

በዚያ ምክንያት መልካሙን ከክፉው ደምሮ በጊዜ ሂደት እየጠራ እንዲሄድ መወሰን እንደነበረበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

“እኛ ስንመጣ መጀመሪያ ቃል የገባነው ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ማምጣት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሁሉንም አካላት እንዳይገቡ ብንከለክል የምናስበውን ዴሞክራሲ ልናመጣ አንችልም ነበር ብለዋል።

የእኛ ውሳኔ የነበረው ሁሉም መድረክ እንዲያገኝ፣ ሁሉም ሐሳቡ ተደምጦ እና ተመዝኖ በሕዝብ እንዲወሰን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አክለውም በአጠቃላይ በውሳኔው አትርፈንበታል፤ የተጎዳንባቸው አካባቢዎች አሉ እነርሱን እየተማርን እና እየቀነስን ጥቅሙን እያጎላን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

“ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን የሚያስደንቁ እና ተዓምር ሊባሉ የሚችሉ ድሎች አስመዝግበናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህም ከለውጡ በፊት በመከላከያ፣ በደኅንነት፣ በሳይበር ደኅንነት እና ሌሎች ተቋማት ውስጥ የነበረው ብቃት እና ዛሬ ላይ ያለው ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከፍተኛ ብቃት መፍጠር መቻሉን ነው አረጋግጠዋል፡፡ አክለውም 130 ሚሊየን ሕዝብ ስላለን ብቻ ሳይኾን ሠልጥነን፣ ተደራጅተን፣ በአዳዲስ ዕውቀት እና ታክቲክ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመከላከል ያለን አቅም ለውድድር የሚበቃ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ሰፋፊ የቨርቹዋል ጥቃቶች ሲፈፀሙ እንደነበር አውስተው፤ የሚመጣን ጥቃት የመለየት እና የመከላከል አቅምን በማሳደግ ረገድ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (ኢንሳ) በኩል ከፍተኛ አቅም ተገንብቷል ብለዋል፡፡

በዚህም በተሟላ መንገድ ሉዓላዊነታችንን ከማንም ኃይል መጠበቅ እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እንደዚህ አይነት ቁመና የተፈጠረው በፈተና ውስጥም ኾነን ጠንክረን በመሥራታችን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኮሮና ወቅትም በራችንን ዘግተን በርሃብ ማለቅ የለብንም፤ መሬት ጦሙን ማደር የለበትም በማለት የተጀመረው በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ የማምረት እንቅስቃሴ በእጅጉ ለኢትዮጵያ ማገዙን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የብልጽግና መሠረት እስከምንጥል ድረስ ትጋቱም ውጤቱም ይቀጥላል ያሉ ሲኾን በተለመደው አሠራር መሪዎች ከቢሮ ስለማይወጡ እና ጉዳዩን በዓይናቸው ስለማያዩ በርካታ የውሸት ሪፖትርቶች እንደሚቀርቡ አንስተዋል፡፡

በአንጻሩ ሥራውን እያዩ የሚመሩ ቁርጠኛ አመራሮች ባሉበት አካባቢ ተግባራት በፍጥነት ይከወናሉ ብለዋል፡፡

በዚህም ወደ መሬት ወርደን ሥራዎችን በአካል እየተከታተልን ስንሠራ በርካታ ትምህርት ይገኝበታል፤ አድካሚ ቢኾንም ለሰዎች ጉልበት ሰጪ ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዚህ መልኩ ጀምረን፣ አስበን፣ ያልጨረስነው ፕሮጀክት የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የማይመስሉ እና በእኛ አቅም የማይታሰቡ ጉዳዮች እናስባለን ነገር ግን ስለሚመሩ እና ክትትል ስለሚደረግባቸው ይጠናቀቃሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አሁንም ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መሰረት እንጥላለን ብለን ቃል የገባነውን ነገር ያለምንም ጥርጥር እናደርገዋለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡

ሐሳቡ አለን፣ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ለመከወን የሚያስችል ትጋቱ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕዝባችንን ይዘን የኢትዮጵያን የብልጽግና መሰረት እስከምንጥል ድረስ ትጋቱም ውጤቱም ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች ይፈለጋሉ

በኢትዮጵያ ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ክፍት የመንግሥት የሥራ መደቦች መኖራቸውንና...

አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሂሳብ መዝገብ ሪፖርትን እስከ ነገ በቅጣት እንደሚቀበል አስታወቀ

  የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ የግብር ግዴታቸውን ያልተወጡ ግብር...

ፈንታዬ በላይነህ የቦስተን ግማሽ ማራቶንን ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ አሸነፈች

በ2026 የቦስተን ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት...