‹‹ሕይወት›› በሎዛ ድርሣናት

Date:



የመጽሐፉ ርዕስ፡- የሎዛ ድርሳናት (ከላምፔዱሳ እስከ ካሌ)
ደራሲ፡- መርዕድ እስጢፋኖስ ወንድሙ
የገጽ ብዛት፡- 517
የሕትመት ዘመን፡- ሰኔ 2017 ዓ.ም
የሕትመት ቦታ፡- አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ


በኄኖክ ገለታው


ግዮን መጽሔት :- ‹ ‹ሎዛ ድርሳናት›› የተሰኘው የጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ መጽሐፍ፣ ‹‹ሎዛ ዘጸአት›› የተሰኘው ቀዳሚ ሥራው ተከታይ የኾነ የኢትዮጵያውያን የባሕር ማዶ ሕይወት በልቦለድ ዘውግ ዘለግ ብሎ የቀረበበት ሥራ (መጽሐፍ) ነው፡፡

የመጽሐፉን ታሪክ ‹‹የስደት ሕይወት›› ከማለት ይልቅ ‹‹የባሕር ማዶ ሕይወት›› ማለትን የመረጥኩትበት ዋነኛው ምክንያቴ፣ የስደትን እጅግ የመረረ ገጽታ ከሰማነውና ከምንሰማው ለየት ባለ መልኩ (የመጽሐፉ ደራሲ ጭምር የኹነቱ ተጋሪም ሰለባም ኾኖ ስላሳለፈ) በመጀመሪያ መጽሐፉ ‹‹ሎዛ ዘጸአት›› በሚገባ ያስቃኘን በመኾኑ ነው፡፡


ኾኖም ከዚህ የመጀመሪያው ቅጽ የቀጠለው ሁለተኛው ሥራው ‹‹የሎዛ ድርሳናት›› እነዚያው ከሰሐራ በረሃ እና ከሜዲትራኒያን ዓሣ በሕይወት የተረፉትን በመጀመሪያው መጽሐፍ ውስጥ የምናውቃቸውን እና ሌሎች አዳዲስ ገጸባሕርያትን ጨምሮ፣ አውሮፓ ከገቡ በኋላ የጠበቃቸውንና የተጋፈጡትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ባሕላዊ እና ፖለቲካዊ ፈተና በዝርዝርና በጥልቀት የሚያስቃኝ መኾኑ፣ ታሪኩን ‹‹የስደት ታሪክ›› ከማለት ይልቅ ‹‹የባሕር ማዶ ሕይወት›› ማለቱ የተሻለ ገላጭ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡


‹‹የባሕር ማዶ ሕይወት›› የሚለው ኃይለ ቃል ታዲያ፣ ፀሐፊው በመጽሐፉ ገጾች ውስጥ አምልቶና አስፍቶ ያሰጣቸውን ግላዊና ሕብረተሰባዊ ጠባያችንን፣ ለማመን በሚከብዱ መከራና ስቅየቶች ውስጥ አልፈን ሜዲትራንያንን እና አትላንቲክን ከተሻግረን እንኳን እንዴት በቀላሉ ሊናጠቡን ስላልቻሉ ባሕሪያቶቻችን የገላለጣቸውን እውነቶች፣ አልያም ደግሞ፣ ሀገርና አየር ቀይረን ጭምር በአንቀልባ አዝለን የምንዞረው ጤና ቢሱ ፖለቲካችን ምን ያህል በባሕር ማዶ ማኅበራዊ ውርክባችን ውስጥ ተጽዕኖው እንደበረታ እያነሳ የጣላቸውን አያሌ ጉዳዮች ሁሉ የሚያካትት ሐረግ መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡


ምናልባትም መጽሐፉን በትዕግሥትና በአስተውሎት በቀጣይ የሚያነብ አንባቢ፣ ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸውን ሰበዞች ይዞ፣ አጠቃላይ የመጽሐፉን ታሪክና የገጸ ባሕሪያቱን ውርክብ ከሥነልቦና እና ከሌሎችም የማኅበራዊ ጥናት ዘርፎች አንጻር ቅኝት ለማድረግ ቢነሳ አያሌ ጠቃሚ ዕይታዎችና ቁምነገሮች እንደሚያገኝበት አልጠራጠርም፡፡
***


ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ፣ መርዕድ እስጢፋኖስ በዚህ እጅግ ዳጎስ ባለ መጽሐፉ ታይተው በቶሎ የሚጠፉትን ጨምሮ ከ20 እስከ 25 የሚደርሱ ገጸባሕርያት ከላምፒዶሳ ደሴት እስከ ካሌ ጫካ፣ ከፓሪስ እስከ ስቶክሆልም፣ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣…. በሚፈሰው ዥረት ውስጥ እንደልባቸው እንዲዋኙ ፈቅዶላቸዋል፡፡

ኾኖም በዚህ መልክ በገፍ የተቀረጹ የሚመስሉን ገጸባሕሪያት ምንም ዐይነት የሚናም ኾነ የሥሪት መደበላለቅ ሲያጋጥማቸው የተመለከትኩ መስሎ ስላልተሰማኝ፣ በረጅም ልቦለድ ዘውግ አንድ የተዋጣለት ደራሲ በዚህ ዘመን የማግኘታችን የመጀመሪያው ምልክት አድርጌ እንዳስብ ምክንያት እንደኾነኝ በመግለጽ፣ በመጽሐፉ ዙርያ ያለኝን አስተያየት እንዲህ እጀምራለሁ፡-


የአስተያየቴ ማጠንጠኛ የሚኾነው፣ ደራሲውም ኾነ ብርቱዎቹ እና የዋሕ ጦሰኞቹ ገጸ ባሕሪያት በስፋት የሚትከነከኑበትን አንድ ጉዳይ በማንሳት ይኾናል፡፡


በእኔ ዕምነት በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው ገጸባሕሪያት በአመዛኙ የሚገናኙበት አንድ አማካኝ አጀንዳ ጎልቶ የወጣ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ ይኽ አጀንዳ ላምፔዱሳ ደሴት ድረስ የሜዲትራኒያን ማዕበል በሕይወትና በሞት መካከል ለተፋት ውዷ ረጂና፣ ‹‹የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፣ ቀላል የኾነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናል››

የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ዝነኛ ቃል (ትምህርት) ለተገለጠበት ሰላም፣ ከክፉ የዐረብ አሳዳሪዎች እስከ አውሮፓ የገዛ ሀገር ልጆች መሠሪ ተንኮል አካላዊም ሥነ ልቦናዊም ዋጋ ለከፈለችው አፄነሽ፣ ራስ ወዳድነቷ ገዝፎ ያበላሸችው የሰዎች ዓለም የጓጓችለት ደስታን ሳታጣጥመው በመጨረሻቹ ደቂቃዎች ለተነጠቀችው ሎዛማርያም፤ ካለመኖር ወደ መኖር ባመጣው አምላኩ ላይ በፈጸመው በደል፣ መልሶ ወደ አለመኖር የተመለሰው፣ ኾኖም በምሕረቱ ብዛት መልሶ ሕልው የኾነው አዳምን ለምታስታውሰን ማርያማዊት እና ለሌሎቹም… ገጸ ባሕርያት የሚያትከነክነው ይኽ አጀንዳ ታዲያ ‹‹ምንድነው?›› ተብሎ የተጠየቀ እንደኾን፣ መልሱ ‹‹ሕይወት ምንድናት?›› የሚል ሌላ ጥያቄ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡


ይኽ ጥያቄ ከታሪኩ መነሻ እስከፍጻሜ በምናገኛቸው ባለታሪኮች መውደቅ መነሳት ሁሉ ቅርጹን እየቀያየረ ተደጋግሞ የሚጠየቅ ጥያቄ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጥያቄ ለገጸባሕሪያቱ ብቻ ሳይኾን ለራሱ ለደራሲውም ቢኾን ሸክም እንደኾነ የሚገባን፣ በዐጭሯ የመጽሐፉ መግቢያ ስለሕይወት ጥቂት ነገር ፈንጠቅ አድርጎ በስፋት ወደሚያጠይቅበት የታሪኩ ባሕር መሰስ ብሎ ለመግባት ሲሞክር ነው።


መርዕድ ቃል በቃል ‹‹ሕይወት አንዳንዴ የምንፈልገውን ያህል በቂ ጊዜ አትሰጠንም፡፡ አንዳንዴም በጣም አጭር ናት፡፡ … አንዳንዴ ግን በህይወት ውስጥ ስናልመው የነበረ በነገ ላይ የተንጠለጠለ ህልማችን ለዓመታት በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሳይሳካ ቀርቶ በጠዋት የተመኘነው በምሽት ብቅ ይላል። ይሄኔ ነው ታዲያ እንደ ነብዩ እያሱ ጀንብሯ ባለችበት እንድትቆም መለመንን የሚያሰኝ›› ይላል፡፡


በእነኚህ ዐረፍተ ነገሮች ውስጥ፣ ደራሲው በሕይወት ውስጥ ምኞት ፍጻሜ ላይኖራት ዕድሜ አጭር መኾኗን፣ በዚህም ሳቢያ የሚፈልጉት በቶሎ እንደማይገኝ፣ የሚመኙት በጊዜው እንደማይሳካ፣ በዚህ መሃል ግን እርጅና ሳይጠሩት ከተፍ እንደሚል በመግለጽ እስከመቃብር ያታለለችንን ተስፋ ትንሽ ለማቆየት፣ አንዳች መለኮታዊ ጸጋን ሲናፍቅ እንረዳዋለን፡፡ አሁን ይኽን የደራሲው ሕይወትን የተመለከተ መረዳት ይዘን ወደ መጽሐፉ እንዝለቅ፡-  


ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ፣ በታሪኩ ውስጥ የምናገኛቸው ብርቱዎቹ እና የዋሖቹ ገጸባሕሪያት የሕይወትን ብየና ፍለጋ ሲቃትቱ፣ አንዳንዴም ትግልና ኑሮ በሰጣቸው መገለጥ ለመበየን ሲሞክሯት የምንመለከትባቸው አጋጣሚዎች አሸን ናቸው፡፡ ይኽ በራሱ ሕይወት በመጽሐፉ ያላትን መልከብዙ ገጽ እያንዳንዳችን አንባብያን፣ ከየቆምንበት የሕይወት ማዕዘን (አንግል) ለማጤን የሚያስችል አንዳች በር ይከፍትልናል፡፡ ጥቂቶቹን እንደአብነት ማንሳት ሐሳቤን ተጨባጭ ያደርግልኛልና ወደዚያ ልለፍ፡-


በገጽ 82 ሰለሞን ‹‹ሕይወት እንደምን እረፍት የሌላት የማታቋርጥ የመከራ ቋት ናት›› ብሎ ራሱን ይጠይቅና መልሶ ግን ‹‹አይ አይደለችም? እኔ የእድል ጉዳይ ሆኖ ስላልተሳካልኝ፣ ምርጫዬም ኾኖ ነው’ንጂ ከኔ ጋር የመጡ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው ሲስተም ውስጥ የገቡ በፈረንሳይ፣ በቤልጅየም፣ በሆላንድ በሞቀ ቤት ውስጥ [እየኖሩ] ናቸው፡፡ አሁን በዚህ ሰዓት እንኳ እኔ መከራ ውስጥ ብሆንም የተሻለ ኑሮ መኖር የጀመሩ አሉ›› በማለት ‹‹ሕይወት››ን በራሷ ዕጣ ፈንታችንን የመበየን ሥልጣን የሌላት፣ የኾነው ሁሉ የኾነውም በገዛ ምርጫችን ምክንያት እንደኾነ ‹‹እረፍት አልባ የመከራ ቋት›› ላለው ኑሮው የገዛ ዕድሉን ከገዛ ምርጫው ጋር አሰናስሎ ጸጸት በነካው ስሜት ለማስተዛዘን ሲሞክር እናየዋለን፡፡


በገጽ 337 የምናገኘው ብንያም ደግሞ፣ ከልቡ ያፈቀራትና እንደሚያገኛትም ልበ ሙሉ ኾኖ ከኖረ በኋላ ባልተጠበቁ ቀናቶችና
ቅጽበታዊ ኹነቶች በጓደኛው ስለተነጠቀው የአቢጋኤል ፍቅር፣ ተራኪው የቢኒያምን አእምሮ አንብቦ እንዲህ ሲለን እንታዘባለን፡-


‹‹አዎ ሕይወት አንዳንዴ መፍጠን ነች። አንድ ሰከንድ ከዘገዩ ቆማ አትጠብቅም፡፡ ሕይወት አንዳንዴ ውሳኔ ነች፡፡ ቆራጥ ውሳኔ፡፡ ሕይወት አንዳንዴ ድፍረት ነች፡፡ ዕቅድ እና ፕሮግራም የማያስፈልጋት ድፍረት ብቻ..›› ይለናል፡፡ እዚህ ጋር ሕይወት የተሳለችበት መንገድ ለየትም ፈንጠርም እንድትል ኾና ነው፡፡ እንደ ቢኒያም ላለ ሰው ሕይወት ካልቀደሟት ቀድማ ጉድ የምታደርግ ‹‹ጉደኛ›› ናት፡፡ ሰዎች የወደዱትን ለማግኘት የተመኙትን ለመጨበጥ ከተለመደው ‹‹ለእኔ ያለው አይሻግትም›› ብሒል ተላቅቀው ከሕይወት ጋር እሽቅድምድም ውስጥ ካልገቡ ቀልጦ ቀራጭ መኾናቸውን እያረዳን/እያስረዳን ነው፡፡  


የሚገርመው፣ በገጽ 208 ደግሞ የሰላም ጓደኛ ሄኖክ፣ የጓደኛውን የአንድ ወቅት ምክር ወደኋላ ያስታውስና ‹‹ሕይወት ደግ ነች›› ሲል እናገኘዋለን፡፡ ሄኖክ ‹‹ደግ ነች›› ብቻ ብሎ ግን አያበቃም፡፡ የደግነቷን መገለጫዎችም እንዲህ ሲል ይዘረዝራል፡፡ ‹‹…ድንገት በጠራራ ፀሀይ ትከሰትና ደመና ትሆንልኛለች፡፡ ድንገት ደመና በሌለበት ዝናብ ይሆንና ሽለቆዎቼ ይሞላሉ፡፡

ድንገት በጨለማው ውስጥ ብጫቂ ብርሀን ትመጣና አካባቢዬ ብሩህ ይሆናል..››፡፡ ለሄኖክ ተስፋው የነጠፈ መስሎ በተሰማው አስቸጋሪ ጊዜያት፣ ‹‹ነገሬ አለቀ ደቀቀ›› ብሎ ጥርስ ማፏጨት ውስጥ በገባባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ፣ ልክ በተዘጋ ቤት ውስጥ ገብቶ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይኹን›› እንዳለው ክርስቶስ፣ ሕይወትም ያበቃና የተዘጋ በሚመስል ምዕራፍ መሃል ‹‹ብቅ›› ብላ ምሥኪኖችን የምትታደግ ‹‹መሢህ›› ተደርጋ ተስላ እናገኛታለን፡፡


ገጸባሕርያቱ ከገጠማቸው ሁኔታ ተነስተው ስለሕይወት የሚነግሩን የተለያየ ብየና እንዳለ ኾኖ፣ ተራኪው (ምናልባትም ደራሲው) ደግሞ፣ በየገጸባሕርያቱ ሁናቴና ሁለንተና መካከል በመግባት በሚያስገርም መልኩ ስለሕይወት የማይታረቁ ተቃራኒ መልኮች ሊነግረን ሲዳዳው እንመለከታለን፡፡


ለአብነትም በገጽ 309 ‹‹ሕይወት ስስ፣ ለመበላሸት ቅርብ የኾነች የአራት ፊደላት ቅኝት!›› መኾኗን ከነገረን በኋላ፣ ዝቅ ብሎ ደግሞ፣ ‹‹ሕይወት የመጠበስ …የማማረር ውጤት ነች። ሰው ፈልጎ እና ፈቅዶ የሚቃጠልበት። ፈልጎ እና ፈቅዶ የሚጠበስባት›› ሲል ያጨልማታል፡፡ በገጽ 338 እንዲሁ ‹‹ሕይወት… ከምቾት ይልቅ የስቃይ ውጤት ናት›› በማለት የጨለማ ገጽዋን ይበልጥ ያጠቁረዋል፡፡  


ኾኖም በሌላ ሥፍራ፣ ተራኪው መልሶ ‹‹በሕይወት ውስጥ ምንም ነገር ባለበት አይቀጥልም፡፡ ሕይወት የጊዜ ባሪያ ናት ፤ በጊዜ ውስጥ የተሰበረው ይጠገናል ፤ የታመመው ይድናል›› በማለት የምሬትና የምረት ውጤት መኾኗን የነገረን ሕይወት መልሳ የፈውስ ምክንያት እንደምትኾንም በገጽ 431 ይነግረናል፡፡ ወዘተርፈ…     

   
በመጨረሻም…
በዚህ የሎዛ ድርሣናት ‹‹ከላምፔዱሳ እስከ ካሌ›› መጽሐፍ የሁለት ገጸ ባሕርያት ሕይወት እና ፍጻሜ፣ ልክ በኦሮማይ መጽሐፍ ጸጋዬ ኃይለማርያም፣ ሮማን ሃለተወርቅና ፊያሜታ ጊላይ ወክለውታል ተብሎ እንደሚታመነው ‹‹ትዕምርታዊ ሚና››፣ በዚህ መጽሐፍ ታሪክም የፓሪሱ ሰላም እና አጼነሽ እንዲህ ያለ ከተለመደው ሰውኛ ሕይወት ከፍ ያለ ትዕምርትነትን ተላብሰው የተቀረጹ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ እዚህ ጋር መጽሐፉ የሚያጠነጥንበት የጊዜ መቼት ከኢትዮጵያ ሚሌኒየም ዋዜማ እስከ ማግሥት በነበሩት ዓመታት መኾኑን ልብ ይሏል፡፡


በመጽሐፉ እንኳንስ ሀገሩን ዓለምን መቤዠት የሚያስችል፣ በንባብ፣ በዕውቀት፣ በአሰላሳይነት ለብዙዎች የጠቀመ ለራሱ ግን ብዙም ደስተኛ ኾኖ ያልኖረ አንድ መሢህ እናገኛለን፡፡ ይኸውም የፓሪሱ ሰላም ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ አስደናቂ ስብዕናን የተላበሰች፣ ልቧ እንኳንስ ሀገር ዓለምን ማኖር የሚችል፣ ዳሩ ግን ለመከራና ለመርገም የተፈጠረች እስኪመስል ድረስ በአካሏ፣ በሥነልቦናዋ በአጠቃላይ ሁለንተናዋ ስቃይን ያስተናገደች፣ ያልፍልኛል ብላ ብዙ ዕድሜዋን በብዙ ሥፍራ የተንከራተተች ‹‹አጼነሽ›› የተባለች እንስትም እናገኛለን፡፡


የሰላምን ላቆየውና፣ አጼነሽ በመጽሐፉ ገጽ 438 ላይ ተራኪው ስለእርሷ የገለጠልን ነገር ከፍ ብዬ ላነሳሁት ትዕምርታዊ ውክልና (ሲምቦሊክ ሪፕረዘንቴሽን) ስምም ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ተራኪው እንዲህ ይላል፡-  

   
‹‹አንዳንዴ በሕይወቷ የሆነባትን ስታስብ ትገረማለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ሕይወት በማትጠብቀው መንገድ ችግሮች ላይ ትጥላታለች፡፡ የዚያኑ ያህል በማትጠብቃቸው መንገዶች ከችግር ነጻ ትወጣለች፡፡ ሰዎች መከራ ላይ ይጥሏታል። ሰዎች አዳኝ ሆነው ይመጡላታል፡፡ እንክትክት ብሎ ሞራሏ ወድቆ፣ እንባዋ ፈሶ አልቆ፣ ጨላልሞባት ሳለ ድንገት በመጨረሻዋ ሰዓት የማለዳ ጸሐይ ታያለች፡፡ እንደገና ሳቅ ይሆንላታል፡፡

… ‹ጂብራንን ከሊባኖስ፣ ኦሊቪዬን እና ሰላምን ከፓሪስ ያዘጋጀ አምላክ አሁንም አልጣለኝም›› ስትል ብቻዋን ከተቀመጠችበት ክፍል ሆና አምላኳን በከፍታ ድምጽ ታመሰግናለች›› ይላል፡፡


አጼነሽ በብዙ መከራ ውስጥ ኾናም ሕይወትን አስመልክቶ ያላት መረዳት ግን ከፍ ብለን ከጠቀስናቸው ገጸባሕሪያት ለየት ብሎ እናገኘዋለን፡፡ በገጽ 321 እንደምናነበው ለእርሷ ‹‹ሕይወት ዛሬና ነገ ነች፡፡ በሁለት መስመር ላይ የተቀመጠች አስደናቂ ፍጥረት፡፡ ዛሬ አሮጌ ልብስ ስትኾን፣ ነገ ደግሞ አዲስ ልብስ እንደማለት ነች›› ትለናለች፡፡ አጼነሽ ስለሕይወት ይኽን የምትለው በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ ኾና ነው፡፡ ሁኔታዎቹ ግን በዛሬው አሮጌ ልብስ የመሰለቻት ሕይወት፣ በነገው አዲስ ኩታ አምራ የምትጠብቃትን ሕይወት ተስፋ ከማድረግ ወደኋላ አላላትም፡፡


አጼ ነሽ ለዚህ ሕይወትን መሠረት ያደረገ ለየት ያለ ፍልስፍናዋ መሠረቱ ደግሞ፣ ሕልውናዋ ከፈጣሪ መልካም ፈቃድ ጋር አብሮ የተሰፋ መኾኑን በማመኗ ይመሥላል፡፡ ይኽንንም በመጽሐፉ ገጽ 349፣ በጉልበቷ ተንበርክካ፡-


‹‹አቤቱ አንተን ታመንሁ ለዘላለም አልፈር፡፡ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤…ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ…›› የሚለውን የመዝሙረኛው ዳዊትን መዝሙር በኃይል ስትጸልይ እንመለከታታለን፡፡


ጥያቄው ይቺ ‹‹እጆቿን ወደ እግዜአብሔር የምትዘረጋ›› ሴት ማን ናት? የሚል ነው፡፡ ሱዳን ወይስ ሶማሊያ?! ባልተጠበቀ መንገድ በታሪኩ ፍጻሜ እንደምንመለከተው፣ ይቺ ዘመኗ በፈተናና መከራ ያለፈው፣ የእኔ በምትለው የሀገር ሰው ሳይቀር በሰው ሀገር ቁራኛ እስከመኾን የደረሰችው፣ ግን ደግሞ በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥም ኾና በአምላኳ ተስፋ ያልቆረጠችው አጼነሽ፣… ስብዕናው እንደ እረፍት ውሃ ከረጋው፣ ለብዙ የቅርብና የሩቅ ወዳጆቹ የሕሊናም ይኹን የኑሮ ጥያቄ መልስ የኾነው፣ ሥሙም ግብሩም ‹‹ሰላም›› ከኾነው ሰው ጋር ተገናኝታ ባልጠበቅነው መልኩ የሐሴት ሕይወት መኖር ስትጀምር እንመለከታለን፡፡

በዚህም ‹‹ሕይወት ዛሬና ነገ ነች፡፡ በሁለት መስመር ላይ የተቀመጠች አስደናቂ ፍጥረት፡፡ ዛሬ አሮጌ ልብስ ስትኾን፣ ነገ ደግሞ አዲስ ልብስ እንደማለት ነች›› የሚለው ጽኑ ዕምነቷ በተግበር ተተርጉሞ እና ሰምሮላት እናገኘዋለን፡፡


መነሻዬም መድረሻዬም ‹‹ሕይወት›› በሎዛ ድርሣናት መጽሐፍ ነውና፣ ሁለቱንም የመጽሐፉን ቅጾች ያነበብን አንባቢያን የምንጠብቀው አንድ ውጤት ቢኖር፣ ታሪኩ የፓሪሱን ሰላም እና የላምፔዱሳዋ የባሕር ትራፊ ውዷ ሬጂና ወይም የሱቀልዴሟ ሰላም መልሰው ይገናኙ ይኾን የሚል ነው፡፡

በመጽሐፉ ግን ሕይወት በዚያ መልክ እንዲገናኙ አልፈቀ
ደችም ወይም አልተፈቀደላትም፡፡ ለምን የሚለው ጥያቄያችን አሁንም መልስ የሚያገኘው ግን ራሱ ሰላም ስለ ሕይወት በሚሰጠን ሌላ ትርጉም ነው፡፡


ሰላም የኾነው ሁሉ የኾነው ‹‹በራሳችን ስካር ውስጥ ሆነን ሕይወትን ብርሃን ውስጥ ብቻ የምንፈልጋት በመኾናችን ነው›› ይለናል፡፡ ‹‹ሕይወትን ብርሃን ውስጥ ብቻ ሳይኾን ጨለማ የመሰለን ነገር ውስጥም እንፈልጋት›› እያለን መሠለኝ?! ዓለሙን የተቤዠው ንጉሥን ከኢየሩሳሌም እንጂ ከገሊላ ያልፈለጉት ወገኖችን ዕጣ ፈንታ ‹‹አስቡ›› እያለንም መሠለኝ?!… ‹‹የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይወርሳል›› ያለ መስሎም ተሰማኝ?! ጠቅለል ሲል እስቲ ያልተሔደበትን መንገድ ለመሔድ እንሞክር የሚል ትልቅ ጥሪም አድርጌ ወሰድኩት፡፡
አንብቡት!

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር  229 የካቲት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ...

በ’ፊንቴክ’ የማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩት ላይ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጠ

በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ስም በተፈጸመ  የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር...

የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት የኢንቨስመንት መጠን 723 ሚሊዮን ዩሮ መድረሱ ተሰማ

ከ20 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች  በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን...

የቴሌግራም ማስጠንቀቂያ

ቴሌግራም (Telegram) ኦፊሴላዊ ያልሆኑ የቴሌግራም መተግበሪያዎችን (Unofficial Apps) በሚጠቀሙ...