የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

Date:


ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመርጡ – First-time voters) እና የሁለተኛ ዙር መራጮች (Second-time voters) ተሳትፎ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። የሕዝባችን አብዛኛው ክፍል ወጣት በመሆኑ፣ የእነዚህ መራጮች ድምፅ የምርጫውን ውጤት የመወሰን አቅም አለው።


ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃቸውን የሚሰጡ ወጣቶች፣ በፖለቲካው መድረክ ላይ አዲስ ኃይል፣ አዲስ አስተሳሰብ እና የነገ ተስፋን ይዘው ይመጣሉ። እነዚህ ወጣቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሰፊ መረጃ ያላቸው፣ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብን የተላበሱ እና የተሻለ የኢኮኖሚ፣ የሥራ ዕድል፣ እንዲሁም የዘመናዊ አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያነግቡ ናቸው። የእነሱ ተሳትፎ የፖለቲካ ሥርዓቱን ሕጋዊነት (Democratic legitimacy) ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለመደው እና ካረጀው የፖለቲካ ትርክት ወጥተው አዳዲስ ፖሊሲዎችን እና አማራጭ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ጉልበት አለው።


በሌላ በኩል፣ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተሳትፈው አሁን ለሁለተኛ ዙር ድምፃቸውን የሚሰጡ ወጣቶች፣ የተሻለ የፖለቲካ ብስለት እና የምርጫ ሒደት ልምድ ያካበቱ ናቸው። ምርጫ የገባውን ቃል ኪዳን በማመዛዘን እና የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ብይን የሚሰጡበት መድረክ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበዋል። እነዚህ የሁለተኛ ዙር መራጮች የፖለቲካ ሥርዓቱን በተከታታይ በማደስ (Political renewal) ረገድ ትልቅ ፋይዳ አላቸው።


የእነዚህ ሁለት የወጣቶች ስብስቦች ተከታታይ እና ንቁ ተሳትፎ፣ ዴሞክራሲን የአንድ ጊዜ ክስተት (Event) ከመሆን አውጥቶ፣ የረጅም ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ባህል (Long-term democratic culture) በኢትዮጵያ ውስጥ ስር እንዲሰድ በማድረግ ረገድ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል። ዴሞክራሲያዊ ባህል የሚዳብረው ዜጎች ምርጫን እንደ መደበኛ የሕይወት ዘይቤአቸው ሲቀበሉትና በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ሲያሳርፉ ነው።


ለሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የወጣቶች ኃላፊነት


በምርጫ ሒደት ውስጥ መሳተፍ ሕገ መንግሥታዊ መብት ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ እና ሲቪክ ኃላፊነትም (National and civic responsibility) ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህንን ምርጫ እንደ አንድ ታሪካዊ አጋጣሚ በመውሰድ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎን (Peaceful political engagement) መገለጫቸው ሊያደርጉ ይገባል።


ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያብብ የሚችለው ልዩነቶች በውይይት፣ በምክክር እና በመቻቻል ሲፈቱ ብቻ ነው። በመሆኑም፣ ወጣቶች ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ የጥላቻ ንግግር እና ከአመጽ ድርጊቶች (Rejecting violence and political extremism) ራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል። በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችን እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በምክንያታዊነት በመመርመር፣ ለሀገር ሰላም እና አንድነት ጠባቂ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ወጣቶች የፖለቲካ ነጋዴዎች እና የጽንፈኛ ኃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆን ነቅተው መጠበቅ አለባቸው።


ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ማለት ድምፅ ከመስጠት ባለፈ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች የሚያቀርቧቸውን ፖሊሲዎች በጥልቀት መመርመርን፣ መቻቻልን እና የሐሳብ ልውውጥን (Promoting tolerance and dialogue) ማበረታታትን ያጠቃልላል። ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ እንጂ፣ የተለየ ሐሳብ ያለውን አካል ማጥላላት ወይም ማጥቃት ከዴሞክራሲያዊ መርሆች ያፈነገጠ ኋላቀርነት ነው። በመሆኑም፣ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ፣ የምርጫውን ሒደት በመታዘብ፣ ኃላፊነት የተሞላው የሲቪክ ተሳትፎ (Responsible civic participation) በማድረግ አዎንታዊ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መሆን አለባቸው። በምርጫ ቅስቀሳ፣ በድምፅ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ከምርጫው በኋላ በሚኖሩ ሒደቶች ሁሉ፣ ሕግንና ሥርዓትን የተከተለ ተሳትፎ ማድረግ፣ ሀገራችንን ከተለያዩ የፖለቲካ ቀውሶች ይታደጋታል።


ጠቃለያ


በአጠቃላይ፣ 7ኛው አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ወደፊት ለማራመድ፣ የሕዝብን ውክልና ለማረጋገጥ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ወሳኝ ምዕራፍ ነው። የዚህ ምርጫ ስኬትና የሀገሪቱ የነገ ሰላም በከፍተኛ ደረጃ የተንጠለጠለው በወጣቶች እጅ ላይ ነው። የወጣቶች ተሳትፎ የፖለቲካ ሥልጣንን ሕጋዊ መሠረት ከማስያዝ፣ ፖለቲካዊ ዕድሳትን ከማምጣት፣ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከመገንባት አኳያ የማይተካ ሚና አለው።


የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ከትላንት ታሪካቸው በመማር፣ አፍራሽ የሆኑ አስተሳሰቦችን እና የፖለቲካ ጽንፈኝነትን በመጸየፍ፣ ገንቢ የለውጥ ኃይል እና የሰላም ዘብ መሆናቸውን በድጋሚ ሊያረጋግጡ ይገባል። ድምፅ መስጠት መብት ብቻ ሳይሆን፣ የተሻለች፣ ዴሞክራሲያዊት፣ የበለጸገች እና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚከፈል ከፍተኛ አገራዊ ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለመጪው ምርጫ በነቂስ፣ በኃላፊነት ስሜት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የነገዋ ኢትዮጵያ የምትመስለው፣ ዛሬ ወጣቶች በሚያሳዩት ዴሞክራሲያዊ ስብዕና እና የሰላም አጋርነት ልክ ነው!

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foundation – YCDF) ከ UNDP ጋር በመተባበር ነው። የወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶችን በማሳደግ፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በማስፋፋት እና የወጣቶችን ንቁ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሠራ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ’ፊንቴክ’ የማጭበርበር ወንጀል በተጠረጠሩት ላይ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጠ

በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ስም በተፈጸመ  የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር...

የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት የኢንቨስመንት መጠን 723 ሚሊዮን ዩሮ መድረሱ ተሰማ

ከ20 በላይ የጣሊያን ኩባንያዎች  በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን...

የቴሌግራም ማስጠንቀቂያ

ቴሌግራም (Telegram) ኦፊሴላዊ ያልሆኑ የቴሌግራም መተግበሪያዎችን (Unofficial Apps) በሚጠቀሙ...

ለ7ኛው ምርጫ 51 ሺህ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 51 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ...