በትግራይ ክልል የታወጀው የሀብት ማሰባሰብ ዕቅድ ለከፋ የኑሮ ቀውስ ሊዳርግ ይችላል

Date:

በትግራይ ክልል ከፌዴራል መንግሥት የሚላከው በጀት መቀነሱን ተከትሎ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት የጀመረው የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ማኅበረሰቡን ለከፋ የኑሮ ቀውስ ሊዳርግ እንደሚችል በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስጠንቅቀዋል፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሰጠው መግለጫ፣ ከፌዴራል የሚላከው በጀት በመቀነሱ ምክንያት አዲስ የሀብት ማሰባሰብ ደንብ አጽድቆ ወደ ሥራ መግባቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የሀብት ማሰባሰብ ሂደትም በነጋዴዎች ላይ በሚጣል የዋጋ ጭማሪ አማካኝነት የሚሰበሰብ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የሚገኘው ገንዘብም ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለፍትሕ አካላት፣ ለደኅንነት ኃይሎችና ለፖሊስ ደመወዝ ክፍያ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አሠራር በሕዝቡ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት የትንሣኤ ሥርዓት ቃንጪ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ደጋፊ ጎደፋይ፣ ቀደም ሲል ከፌዴራል የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉ አሁን ላለው ችግር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ደጋፊ ለአሐዱ እንደገለጹት፣ የፌዴራል መንግሥት “ገንዘብ ባክኗል” በሚል በጀት ማቋረጥ የለበትም፤ ይልቁንም የቁጥጥር ሥርዓቱን በማዘመን መሥራት ይኖርበታል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም በነጋዴዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝቡን ከማማረር ይልቅ፣ በክልሉ ያለውን ተፈጥሯዊ ሀብት በመጠቀምና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመግባባት ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ተመሳሳይ ሥጋት ያላቸው የትግራይ ክልል ስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባል አቶ ጣዕመ አረዶም በበኩላቸው፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ በጀት የመመደብ ግዴታ እንዳለበት ለአሐዱ ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተመደበው በጀት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉ አሁንም ትልቅ ፈተና መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ሕዝቡን ወደ አላስፈላጊ ምሬትና ችግር ውስጥ እንደሚከተው የገለጹት አቶ ጣዕመ፣ ይህ ሁኔታ ወደ ሁከት በማምራት “ለጠላት በር የሚከፍት” እንዳይሆን ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አካላት ሕገ መንግሥቱን ባከበረ መልኩ በመተማመን መሥራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችና ተፈናቃዮች አሁንም በከፋ ችግር ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የሀብት ማሰባሰቡ ሥራ አማራጭ የሌለው መሆኑን ይሞግታል፡፡

በጦርነት የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማገገም እስካሁን የተሠራ ሥራ አለመኖሩን የጠቀሰው አስተዳደሩ፣ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግና የመንግሥት መዋቅሩ እንዳይፈርስ ደመወዝ ለመክፈል ይህ አዲስ ደንብ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በፓርቲዎችና በአስተዳደሩ መካከል ያለው የሐሳብ ልዩነት፣ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጥረት ይበልጥ አጉልቶታል።

(አሐዱ ራድዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...