“ሪልስቴቶች ስማቸውን ማጽዳት አለባቸው”

Date:

“አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ዳግም ያረጋግጣል”

‹‹ሕዝባችን ማን ምን እንደሚሠራ ጠንቅቆ ያውቃል››


አቶ አለማየሁ ከተማ
(የኢትዮጵያ ሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት)

የግዮን መጽሔት እንግዳ የሆኑት አቶ አለማየሁ ከተማ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ናቸዉ። የሪልስቴት አልሚዎች ሌቦችና ሕዝብ የሚያስቸግሩ ሳይሆኑ፣ በሕግና በታማኝነት የሚንቀሳቀሱ የሀገር ልማት አጋር እንዲሆኑ ለማድረግ የጀመሩትን ጉዞና የወደፊት ዕቅዶቻቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር ያደረጉት ቆይታ የመጨረሻዉ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፦ ማኅበራችሁ ውስጥ ላሉ አባላትም ይሁን አዲስ ለሚመጡ አባላት ምን ምክር ይሰጣሉ?


አለማየሁ፡- የግንባታ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ተቋም በየዘርፉ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት ያስፈልገዋል፡፡ የማማከር ሥራ የሚሠራ፤ የማርኬቲንግ ሥራ የሚሠራ ሌሎች ማናቸውም ጉዳዮች በየበኩሉ የሚጨርስ ክፍል ሊኖረው ይገባል።


ግዮን፡- ወደ ተቋማችሁ ቅሬታ ይዘው የሚመጡ አካላት አሉ?


አለማየሁ፡- በዚህ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጋር ተፈራርመን አንዳንድ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ እነዚህን ቅሬታ ያቀረቡ አርባ የሚኾኑ አካላትን ወደ አዲስ ቻምበር ልከናል፡፡

ለምሳሌ አንድ ቤት ፈላጊ ‹‹ከአሥር ዓመት በፊት ተዋውዬ ገንዘቡን ከፍዬ ከጨረስኩ ሁለት ዓመት ኾኖኛል፡፡ ነገር ግን ቤቱን እስካሁን ማግኘት አልቻልኩም›› ብሎ ይመጣል፡፡ ይህ በሚኾንበት ጊዜ ግለሰቡ ቤቱ ወይም ገንዘቡ እንዲመለስለት የማስማማት ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህ አንፃር የሪልስቴት አሠራርን ከባድ የሚያደርገው ወይ ቤቱ ፈርሶ ወይ ቦታው ተሸጦ ገንዘቡን በቀላሉ መመለስ አይቻልም፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ቢፈታ በጣም ጠቃሚ ነው ብለን ከአዲስ ቻምበር ጋር ተፈራርመን ሥራ ጀምረናል፡፡


ግዮን:- ከአዲስ ቻምበር ጋር የተፈራረማችሁት ምንድን ነው?


አለማየሁ፡- በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሰሩበት ሁኔታ ስላለ ጥያቄ ስናቀርብላቸው በጋራ ለመስራት በታላቅ ፍላጎት ተቀብለውናል፡፡ በመሆኑም ዛሬ የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ በመፈራረም ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ በገዢና በሻጭ በኩል ያሉ አለመግባባች ተጨማሪ ፍ/ቤት ሔደው ሳይንገላቱ እንዲፈቱ ለማስቻል መሆኑን በደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

ከምክር ቤቱ የምናገኘውን እውቀትና ልምድ ተጠቅመን በቀጣይ የማኅበሩን የራሱን የግልግል ዳኝነት የሚያቋቁም መሆኑን በደስታ እንገልፃለን፡፡ አዲስ ቻምበር ከቀዳማይ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ በአሸማገይነት ሥራ የታወቀ ነው። በዚህ ዙሪያ ተቋሙ ትልቅ ልምድ ያለው ስለኾነ ለእርሱ ልንሰጠው ችለናል፡፡


ግዮን:- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?


አለማየሁ:- ማኅበራችን ከተመሠረተ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድ እስከ መሬት አስተዳደርና መሰል መንግሥታዊ ተቋማት ጋር አብረን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ እስካሁን በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ለምሳሌ ቤት እየወደቀ ችግሩ ወደእኛ ዘንድ ይመጣል፡፡ ይህን በተመለከተም በርካታ ሥልጠናዎችን አሰልጥነናል፡፡

የሕንጻ ግንባታ ላይ የሠራተኛው ደህንነት ዋንኛው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመኾኑም መሬቱና ግንባታው የማይጣጣሙ ቦታዎች ላይ ግንባታዎች እንዳይፈፀሙ ግንባታ ፈቃድ እንዲከለከል ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይህን የምናደርገው ከከተማ አስተዳደር ጋር አብረን በምንሠራው ሥራና ካለን እውቀትና ግንዛቤ በመነሳት ነው፡፡ ‹‹ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም›› እንደሚባለው ሁሉ ኢትዮጵያም ቀስ በቀስ እየተገነባች ትሄዳለች፡፡


ለዚህ ግንባታ ሂደት ግን ትክክለኛውን መንገድ መከተል ይኖርባታል፡፡ ባለንበት ዘመን ቴክኖሎጂ በጣም እየመጠቀ መጥቷል፡፡ የቴክኖሎጂው መምጠቅ ደግሞ በግንባታ ሂደቱ ላይ የራሱ የኾነ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰፈር የተሠራ ቤት ሄደን አይተናል፡፡ ከዚያ ህንፃ ሥር መኪኖች ለመውጣት ሦስት ሰዓት ይጨርስባቸዋል፡፡ ለምን እንደዛ ተደርጎ እንደተሠራ እራሱ ግራ ይገባኛል። ያን ሕንፃ የሠራ ግለሰብ ‹‹እኔስ እዚህ ብኖር›› ብሎ አለማሰቡ አስገርሞኛል፡፡ ግንባታ ማለት እኮ ገንዘብ ተቀብሎ ድንጋይ እና ሲሚንቶ ቆልሎ መሄድ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ 

በአሰላሳይ አእምሮ የፀዳ ፕላን አዘጋጅቶ በተሻለ መንገድ ግንባታውን አከናውኖ ለሚመለከተው አካል ማስረከብ ያስፈልጋል እንጂ አንድ መኪና ከግራውንድ እስኪወጣ ሦስት ሰዓታት እንዲጨርስ አድርጎ መሥራት አግባብ አይደለም፡፡ በእንዲህ ዓይነት የሥራ ሂደት ውስጥ የታመሙ ሰዎች፣ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አዛውንቶችን ሁሉ ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሲሠሩ በቂ መንገድና በቂ ፓርኪንግም አብሮ ሊታሰብ ይገባል፡፡ የኛ ሥራ ደግሞ እንደ ሌሎች የሥራ ዘርፎች አይደለም፡፡ አንድ ሐኪም ሰው ካረፈበት በኋላ ብዙ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ እኛ የገነባነው ሕንጻ ግን እድሜ ልክ ቆሞ ያስወቅሰናል፡፡ እኛ ከሞትን በኋላም ልጆቻችንን ሲያስወቅስ ይኖራል፡፡


ግዮን:- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋራ ማኅበራችሁ እየሠራ ያለው ነገር ምንድን ነው?


አለማየሁ:- ለአቅመ ደካሞች የሚሆን ቤት G+4 ለ30 አባወራ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 08 የሚገኝ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኅበር እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን ብር 60,000,000 ብር የሚገመት ፕሮጀክት ማኅበራችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን የማኅበራችን አባላት በግላቸው የተለያየ ማኅበራዊ አገልግሎት ቢፈፅሙም በጋራ በመሆን ዜጎችን ለመርዳት ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ማኅበራችን በአሁኑ ሰዓት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር አርባ ለሚሆኑ አቅመደካሞች ቤት እየሠራ ነው፡፡ ከኮንትራክተር ማኅበሮች ጋር በመኾን ነው እየሠራን ያለነው፡፡


ግዮን፦ የዚህ ማኅበር አባል ለመኾን ምንድን ነው የሚያስፈልገው?


አለማየሁ፡- በመጀመሪያ ፎርም ይሞላል፡፡ በየዓመቱ የምዝገባ ይከፈላል፡፡ ከዚያ አባል መኾን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ቦርዱ የቀረው አንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ሌሎች ተመራጮች ይተካሉ፡፡ እነሱ ደግሞ መጥተው በእኛ ቦታ ማከናወን ይጀምራሉ፡፡ እንዲህ እየተቀባበልን የማኅበሩን ዓላማ እናሳካለን፡፡ ዘርፉንም እያሳደግን እንሄዳለን፡፡ ሥልጠናዎች ሲኖሩ እየሰለጠንን እራሳችንን እናበቃለን፡፡ ችግሮች ካሉም እናማክራለን፡፡


ግዮን፦ በሀገራችን እየጨመረ ያለውን የመሬት ዋጋ መናርና መወደድ የቤት ውድነት ለመቆጣጠር ምን እየሠራችሁ ትገኛላችሁ?


አለማየሁ፡- ለምሳሌ 2500 ቤት የሚገነባ ሰው በነፃ ቦታ ይሰጠዋል። ቤቱ እንዴት ይገነባል የሚለው ደግሞ 250 ቤት ለአሥር ሪልስቴቶች በመከፋፈል በቀላሉ መሥራት ይቻላል፡፡ እንዲህ መሥራት የሚቻልበት ሕግ የወጣው በቅርቡ ነው፡፡ ቤት አልሚው ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ መንግሥት አሥር ሺህ ክፈል ያለው ቦታ ላይ 300 እና 400 ሺህ እየከፈለ በራሱ ላይም በሌላው ላይም ጭነቶችን ይፈጥራል፡፡ ይኼን ከማኅበሩ አባላት ጋር ተነጋግረን መፍትሔ ማምጣት አለበት፡፡


ግዮን፡- ይኼ ግንባታ ሥራ ላይ ውሏል?


አለማየሁ፡- በቅርቡ የወጣ ሕግ ነው፡፡ መንግሥት 70/30 በሚል ለአልሚው 70 ቤት ለመንግሥት 30 ቤት በሚል ነው ያሰቀመጠው፡፡ ይኼ ለሪልስቴቱ ዐዋጪ አይደለም ብለን ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርንበት ነው፡፡


ግዮን፦ የአፍሪካ ሪልስቴት አባል ከኾናችሁ ሰንብታችሏል፡፡ ወደፊት ደግሞ የዓለም ሪልስቴት አባል ልትኾኑ ነው፡፡ ለአባልነት የሚጠበቅባችሁ መስፈርት ምንድነው? የምታገኙትስ ጥቅም ምንድነው?

አለማየሁ:- የአፍሪካ ሪልስቴት አባል በመኾናችን ጉባዔው በኢትዮጵያ እንዲካሔድ አደርገናል፡፡ ይህን ማድረጋችን ትልቁ ውጤት ነው፡፡ በርካታ የዘርፉ አፍሪካውያን ባለሙያዎች ኢትዮጵያችንን ያዩዋታል ማለት ነው። በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን አባላቶቻችን እንዲሳተፉ በማድረግ ተጠቃሚ እንኾናለን። አሁን ዓለም የሰለጠነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ከሡልጡኑ ዓለም ጋር አብሮ ለመራመድ ይህን ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ እንደአፍሪካ የአባሎቻችንን አቅምና የብቃት ደረጃ እየገመገምን ማን ብቃት እንዳለው እና እንደሌለው መለየት እንችላለን፡፡ የድሮ አሠራር አሁን ቀርቷል፡፡ አሁን ሥራዎች ሁሉ ተጠቅለው ሞባይል ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለእርሱ የሚመጥን እውቀት ያስፈልገናል፡፡ ለዚያም ነው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መሥራት ያለብን፡፡ አሁን ያለው ሕጋችንም ለዚህ በአመቺ መንገድ ተቀንብቧል፡፡ ስለኾነም ማንም ከሕግ ውጪ ሊሠራ አይችልም፡፡


ግዮን፦ አሁን ላይ በሀገራችን በርካታ ሪልስቴቶች ጀምሮ መጨረስ አቅቷቸዋል። ለእነዚህ ተቋማት የእናንተ እገዛ ምንድነው?


አለማየሁ፡- የእኛ እገዛ መጀመሪያ ችግሩ ለምን እንደተፈጠረ ማጥናት ነው፡፡ ገንዘቡን አውጥቶ ሌላ ጥቅም ላይ አውሎታል? በእውቀት እጥረት ምክንያት ነው? ቢደግፉትስ መሻሻል የሚችልና ወደፊት ማደግ የሚችል ነው ወይ የሚለውን ካጠናን በኋላ በተቻለ መጠን እንደግፋለን፡፡
ግዮን:- ለአባላቶቻችሁ በባለሙያ ያዘጋጃችሁት ሥልጠና አለ?
አለማየሁ፡- አዎ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፋይናንስ ጋር ሥልጠና ወስደናል፡፡ ሁሉም አገር ሥራ የሚሠራው በሕግ ነው፡፡ ያለ ሕግ ያደጉ አገራት የለም፡፡ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዱባይ የትም ብንሄድ የሚሠራው በሕግ ነው። ስለኾነም በሀገራችን ያለ ሕግ እየሠሩ ያሉ አካላትን ወደ ትክክለኛው የሕጋዊ አሠራር እንዲመለሱ እናማክራለን፡፡ በሕግ መሥራት የሚጠቅመው ለሠሪው አካል ነው፡፡


ግዮን:- ተቋማቸው ከመንግሥት ተቋማትና ከሌሎች የግል ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?


አለማየሁ፦ ቀደም ሲል እንዳልኩት ከአዲስ ቻምበር ጋር፣ ከግንባታ ፈቃድ ጋርና ከሌሎችም መሰል ተቋማት ጋር እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ ቻምበር ጋር በመሥራታችን የበርካታ ሰዎች ቅሬታ እየታየ ይገኛል፡፡ ምናልባትም ችግሩ በግንባታ አልሚው ብቻ የመጣ ሳይኾን በገዢውም በኩል የተከሰተ ሊኾን ይችላል፡፡ በግንባታ ፈቃድ በኩል ለተቋማችን አባላት ብዙ እገዛ እየተደረገ ነው፡፡


ግዮን:- በሀገራችን ያሉ የሪልስቴት ገንቢዎች ለገዥዎች በገቡት ቃል መሠረት ማስረከብ ባለመቻላቸው ብዙ ጊዜ ችግሮች ሲፈጠሩ አይተናል። እንዲህ ዓይነት ኹነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ምን ለመሥራት አቅዳችኋል?


አለማየሁ፡- ይህ ችግር የሀገራችንን ፍርድ ቤቶች ያጣበበ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝቡን ያማረረና የሪልስቴት ዘርፉን ያጨለመ ጉዳይ ነው፡፡ የሀገር እድገትንም በእጅጉ ወደኋላ የጎተተ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በትኩረት ካየነው ሪልስቴት ማለት ትልቅ ፋብሪካ እንደማለት ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ቤት ሲሠራ የቤት እቃ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፈርኒቸር ፋብሪካ ይጠቀማል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ቤቱ ሲሠራ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞችን ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሥራ አጥነትን ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ አንድ ቤት ሲሠራ ኢኮኖሚው ይንቀሳቀሳል ፤ ሃገርም በዚያው ልክ ያድጋል፡፡ ስለዚህ ቶሎ ተመልሰን ሁሉንም ነገር ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ እኛ የምንከተለው ‹‹የምትውጠውን ያህል ጉረስ›› የሚለውን መርህ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ከጎረስክ ያንቅሃል እንላለን፡፡


ግዮን፡- በግንባታ ሥፍራዎች በመንግሥት በኩል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ማለትም እንደ ውሃና መብራት ያሉ የኃይል መቋረጦችንና አለመኖርን ለማስተካከል በእናንተ በኩል ምን የተሠራ ነገር አለ? እነደሲሚንቶና ብረት ያሉ የግብዓት እጥረቶችንስ እንዴት ትፈታላችሁ?


አለማየሁ፡- በእኛ በኩል ይህ ሁኔታ እንዲቀየር እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን በቅርቡ ብረት የሚመረትበትንና ከእኛም አልፎ ወደ ውጭ እንድትልክ ለማድረግ እየጣርን እንገኛለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሲሚንቶ ዋጋንም ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት እያልን ሀሳብ እያቀረብን እንገኛለን። በሦስተኛ ደረጃ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች እዚሁ እንዲመረቱ እንመክራለን፡፡ ለምሳሌ ድንጋይ ከውጭ የሚያመጣ አካል አለ፡፡ እንዲህ ዐይነት የሸክላ ድንጋዮች ከውጭ ከሚመጡ እዚህ የሚመረቱበትን መንገድ ማመቻቸት ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ ልማት ባንክ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው፤ እኛም እየሠራንበት እንገኛለን፡፡ ለነዳጅና ለመድኃኒት መውጣት ያለበት ዶላር ቻይና ሔዶ ድንጋይና ሸክላ ሲገዛ ይገኛል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች እኮ በሀገራችን የሚገኙ ነገሮች ናቸው፡፡ ችግር የኾነው በሥርዓቱ አምርቶ የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ማናቸውንም የግራናይትና የማርብል ዝርያዎችን እዚሁ ማምረት ይቻላል፡፡


ግዮን፡- ሪልስቴቶች ከኢትዮጵያ ወጥተው በሌላው ዓለም ራሳቸውን ለማስተዋወቅና የቪዛ ክልከላ ለሚያጋጥማቸው ተግዳሮት የእናንተ ማኅበር ምን ዓይነት መፍትሔ ያቀርብላቸዋል?


አለማየሁ:- ሪልስቴቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ ስማቸው ጥሩ ስላልኾነ ኤምባሲዎችም ገንዘብ ሰብሰበው ሊጠፉ ነው ብለው ይሰጋሉ። ስለዚህ በመጀመሪያ ስማቸውን ማጽዳት አለባቸው፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ እንደ ማኅበር ሪልስቴቱን ወደ ትክክለኛ ማንነት በማምጣት በሌሎች አገሮች ላይ ተወዳዳሪ ኾነው ቀርበው የሚሠሩበትን መንገድ ግንዛቤ ለመፍጠር እንጥራለን፡፡

ከዚያ ውጪ ፍቃድ ያለው ሪልስቴት ሁሉ የገባበት ቦታ እየገባን የማጀብ ሥራ አናከናውንም፡፡ እኛ የምንሠራው በሕጋዊ መንገድ እየሠራ ታማኝነቱን ሀብቱ ካደረገ ድርጅት ጋር ነው፡፡ አካውንቱ የማይታወቅና ወጪ ገቢው ይፋ ያልኾነ፣ መንግሥት የጣለበትን ግዴታ የማይወጣ ማለትም ታክስ የማይከፍል ተቋም ከእኛ ጋር ሕብረት የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ሕዝባችን ማን ምን እንደሚሠራ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡


ግዮን፡- በቅርቡ በለንደን የሚካሄደው የባዛር ዝግጅት ቀኑ መቼ ነው? ተሳታፊ ለመኾንስ መስፈርቱ ምንድነው?


አለማየሁ፡- በግንቦት 2018 ዓ.ም በለንደን ይካሔዳል፡፡ መስፈርቱ ሊሸጥ የሚችል ቤት ገንብቶ በእጁ ላይ ያለ ተቋም መኾን አለበት፡፡ መሬት ወስዶ አጥር ያጠረ የዚህ ባዛር ተሳታፊ መኾን አይችልም። በባዛሩ ለመሳተፍ ቤት ከመሥራቱም ባለፈ ለሠራቸው ቤቶችም የተናጠል ካርታ ያዘጋጀ መኾን ይኖርበታል፡፡
ስለዚህ ባዛር ላይ መሳተፍ ለሚሹ ተቋማት በእኛ በኩል ደብዳቤ በትነናል፡፡ እነርሱ ደግሞ ያላቸውን ቤትና ካርታ በዝርዝር ያሳያሉ፡፡


ግዮን፡- በፊት ላይ ገንዘብ ተሰባስቦ ቤት ይሠራል ይባልና ቤቱም ሳይሠራ ገንዘቡ ሳይመለስ ይቀራል፡፡ ይህን ሂደት ለማስተካከል የእናንተ ማኅበር ምን ያቀደው ነገር አለ?


አለማየሁ፡- ይህን አሠራር ለማስተካከል በፓርላማ ሕግ ጸድቋል፡፡ ገንዘቡ ተሰብስቦ በአካውንት ይቀመጣል፡፡ ቤቱም በታለመለት የጊዜ ማዕቀፍ ይገነባል፡፡ ይህን ሂደት የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አካል አለ፡፡ የገዢውን ገንዘብ የሚያስተዳድረው መንግሥት ነው፡፡ በገዢውና በገንቢው መካከል ሕግ አለ፡፡ ከዚህ በፊት ግን ማንም በትውውቅና በዘፈቀደ ገንዘብ ስብስቦ ቤት ሳይኾን መኪና ገዝቶ ሊነዳበት ይችላል፡፡ አልፎም ዱባይ ሄዶ ‹‹ኢትዮጵያ ሪልስቴት አለኝ›› እያለ ተጨማሪ ገንዘብ ሊሰበስብበት ይችላል፡፡ አልፎም በዚያው በዱባይ የግሉን ቤት ሊገዛበት ይችላል፡፡ እስካሁን በነበረው አሠራር ገንዘብ ሰብስቦ ሲያበቃ ‹‹ሂድ ክስሰኝ›› የሚል ጉልበተኛ የገነነበት ነበር።


ግዮን፦ በቅርቡ በኢትዮጵያ በምታዘጋጁት ባዛር ሪልስቴቶች ለመሳተፍ ምን ይጠበቅባቸዋል? ቦታውና ቀኑ መቼ ነው?


አለማየሁ፡- ለመሳተፍ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ሕጋዊ ፈቃድ ያለው መኾን ነው። ከዚያ ውጪ ደግሞ ከፍ ሲል እንዳልኩት የገነባቸው ቤቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡ ቤትና ካርታውን ይዞ ከቀረበ ገበያ ማግኘት ይችላል፡፡ የእኛ አባላት ሰላማዊና የተከበሩ የሀገሪቱ ልማት ገንቢዎች እንጂ ሌቦችና ሠርቀው ሕዝብ ያስቸገሩ እንዳይኾኑ እንሠራለን፡፡ ይህን ለማስተካከልም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ገንቢው ሠርቶና ተከብሮ እንዲኖር ሳይሰርቅና ሳይሽማቀቅ እንዲሠራ ለማድረግ እንጥራለን፡፡


ግዮን፡- ባዛሩ መቼ ይካሔዳል?


አለማየሁ፡- የመጀመሪያውን የአፍሪካ ሪልስቴት ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ጉባዔና ‹‹አዲስ – አፍሪካ›› የተሰኘውን የሪል ስቴት ኤግዚቢሽን ከሚያዝያ 15 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ለአራት ቀን ይካሄዳል፡፡ መርሃ-ግብሩ ከንግድ ትርኢት ባለፈ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤን እና የአፍሪካ ሪል ስቴት ማኅበር የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ስብሰባን በአንድ ላይ የሚያስተናግድ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው መድረክ መሆኑ ተገልጿል። አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ዳግም ያረጋግጣል የተባለው ኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ልዩ ኤግዚቢሽን ላይ የማኅበሩ አባላት የሆኑ አልሚዎች የተለያዩ ፕሮጀክቶቻቸውን ይዘው የሚቀርቡ በመሆኑ፣ መኖሪያ ቤት እና የንግድ መደብር ፈላጊው ማኅበረሰብ አማራጮችን በአንድ ቦታ እንዲያገኝ ሰፊ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡


ግዮን፡- መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላችሁ የምትፈልጉት ነገር አለ?
አለማየሁ፡- መንግሥት እስካሁን ድረስ የቻለውን ሁሉ እያደረገልን ይገኛል፡፡ እኛ ነን እንደውም ወደኋላ የቀረነው፡፡ ስለዚህ በመንግሥት በኩል ምንም የጎደለ ነገር የለም፡፡ መንግሥት በዚህ ዙሪያ የተስተካከለ አሠራር እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ እኛ ጋር ነው ድክመቱ ያለው፡፡ በመንግሥት በኩል ሙሉ ድጋፍ አለን፡፡ የትኛውም ተቋም ለእኛ ክፍት ነው፡፡


ግዮን:- በመጨረሻ ስለ ማኅበራችሁ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድል ልስጥዎት?


አለማየሁ፡- ማስተላለፍ የምፈልገው በመጀመሪያ ሁሉም ሰው የማኅበራችን አባል እንዲኾን እንሻለን የሚለውን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ወደኛ ማኅበር ስትመጡ ትክክለኛ አልሚ እንደምትኾኑ አምናችሁ ኑ ማለት እፈልጋለሁ፡፡


ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር  232 ሚያዝያ  2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት 54 ‹‹አስገዳጅ›› ህጎችን አፀደቀ

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃዎች ቦርድ ባካሄደው 5ኛው መደበኛ ስብሰባው፤...

የአዲስ አበባ ቻምበር የንግድ ትርኢት ማካሄድ ጀመረ

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 27ተኛውን አለማቀፍ...

“ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች”:-  ከዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል ጋራ ውይይት

ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል በተለይ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ 97...

የ12ኛ ክፍል የፈተና ቀን ታወቀ

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርተፊኬት (12ኛ ክፍል ፈተና) ከሰኔ...