“ጥሩ ፕሮጀክቶችን ይዘን ነው ወደ ከተማው መምጣት የምንፈልገው”

Date:

ኤዶም ዳምጠው

ግዮን መጽሔት :- በንግዱ ዓለም ስኬት በአንድ ጀምበር የሚገኝ ድል ሳይሆን በጽናት፣ በእውቀትና በማያወለዳ ቆራጥነት የሚገነባ ረጅም መንገድ ነው፡፡

በመጽሔታችን እንግዳ አድርገን ያቀረብናት ግለሰብ ይህንኑ እውነት በሕይወት ተሞክሮዋ ያስመሰከረች ብርቱ ሴት ናት፡፡ በሪል ስቴት ማርኬቲንግና በሥልጠናው ዘርፍ አሻራዋን እያሳረፈች የምትገኘው የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን እና የዶክሳ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ — ኤዶም ዳምጠው፡፡

​የኤዶም የሥራ ሕይወት ታሪክ የሚጀምረው ገና በለጋ ዕድሜዋ፣ በቀን በሱፐር ማርኬት እየሠራች ማታ ማታ ደግሞ የፋርማሲ ትምህርቷን ትከታተል በነበረበት የትግል ወቅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ድንገት ያገኘችው የሽያጭ (Sales) ሥራ የሕይወቷን አቅጣጫ ቀየረው፡፡

በሕክምናው ሳይንስ ፋንታ ወደ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት በማዘንበል፣ ላለፉት 20 ዓመታት በዘርፉ ዘልቃበታለች፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ያገኘችው ሙያዊ ሥልጠናና በዘመን ባንክ እንዲሁም በአክሰስ ሪል ስቴት የነበራት ቆይታ ለዛሬው ማንነቷ ትልቅ መሠረት እንደሆነላት ትናገራለች፡፡

​ኤዶም ለሥራ ያላት ፍቅርና ለውድቀት እጅ አለመስጠቷ፣ በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር በነበራት በዚህ ቆይታም ኤዶም ከቀበና ካቶሊክ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ስለነበራት የትምህርት ጉዞ፣ በሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ስላጋጠሟት ተግዳሮቶች፣ ከ600 በላይ ወጣቶችን በነፃ ስላሰለጠነችባቸው መድረኮችና ከትዳርና ከልጆች አስተዳደግ ጋር የሥራ ስኬትን እንዴት ማጣጣም እንደቻለች በዝርዝር ታካፍለናለች። መልካም ቆይታ!

ግዮን:- በቅድሚያ የመጽሔታችን እንግዳ ለመኾን ፈቃደኛ ስለኾንሽ እያመሰገንን፣ ራስሽን በማስተዋወቅ ብትጀምሪ?

ኤዶም፡- ኤዶም ዳምጠው እባላለሁ። የተወለድኩት አዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ነው። እስከ 10ኛ ክፍል የተማርኩት ቀበና ካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው። 11ኛ 12ኛ ክፍል ደግሞ የካቲት 12 ነው የተማርኩት። የተመረቅኩት ደግሞ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ነው። አድማስ ዩኒቨርስቲ ነው የተማርኩት። ከዚያ ቀደም ብሎ ወደ ሕክምና እና ሳይንሱ አደላ ነበር።

ነገር ግን የዚህኛውን አጋጣሚ ሳገኝ ወደ ማርኬቲንግ መጣሁ። በማርኬቲንግ ሥራ ላይ ከ20 ዓመት በላይ ቆይቻለሁ።  ሱፐር ማርኬት ተቀጥሮ ከመስራት ተነስቼ አሁን የራሴ ሁለት ድርጅቶች እየመራሁ እገኛለሁ፡፡ ረጅም ጊዜ ያሳለፍኩት ማርኬቲንግ ሥራ በመሥራት ነው።

ግዮን:- የመጀመሪያ ሥራሽ ምን ነበር?

ኤዶም:- ቀን ቀን ሸዋ ሱፐር ማርኬት እየሰራሁ ማታ ማታ ደግሞ ፋርማሲ እማር ነበር። በአጋጣሚ አንድ ድርጅት ውስጥ የሴልስ ሥራ አገኘሁና የፋርማሲስት ትምህርቴን አቁሜ ወደ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ቀየርኩት፡፡

አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ሰርቻለሁ። ዘመን ባንክና አክሰስ ሪል ስቴት ሲቋቋም ሠርቻለሁ። ጥሩ እውቀትም ያገኘሁት እነዚህ ተቋማት ላይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሪል ስቴት በመመለስ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በሴልስ ማናጀርነት ሠርቻለሁ።

ግዮን:- የሪል ስቴት ሥራው ላይ እንዴት ረጅም ጊዜ መቆየት ቻልሽ?

ኤዶም:- በመጀመሪያ ደረጃ ሙያዊ የኾነ ሥራ የጀመርኩት አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ውስጥ ነው። እዚያ የምንሠራው የሪልስቴት ሥራ አይደለም፡፡ እዚያ ተቋም ላይ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስለምንገናኝ ከበርካታ ሰዎች ትምህርት መውሰድ ይቻላል። አጠቃላይ ስለደንበኛ አያያዝና ግለ ስብዕናዊ እውቀቶችን የተማርኩት ከዛ ነው። 

እንዳጋጣሚ ኾኖ ወደ ሪል ስቴት ገበያው ስሄድ የወደድኩት ገበያውን ሳይኾን የሽያጭ ሥራውን ነው። ምን ይሸጣል የሚለው ብቻ ሳይኾን እንዴት ነው የሚሸጠው የሚለውን ነው የወደድኩት፡፡

ግዮን:- ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሺን መቼ ተመሰረተ? የካቦድ ትርጉምስ ምንድነው?

ኤዶም:- ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሺን የተመሰረተው 2012 ዓ.ም ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሳስበው የነበረ ሐሳብ ነበረ። አንድ ድርጅት ውስጥ ማርኬቲንግ ማናጀር ኾኜ እሠራ ነበር። እንደአጋጣሚ የድርጅቱ ፕሮጀክት ሰፋፊ የቤት ፕላኖችን የያዘ ነበረ ፤ ይህን መሰል ሥራ መሥራት እንዳለብኝ አሰብኩ።

ይህን የመሳሰሉት ሦስት አራት ፕሮጀክቶችን ይዤ ብሰራ ውጤታማ እኾናለሁ በሚል ተስፋ ወደ ሥራው ገባሁ፤ ኾነልኝም፡፡ ካቦድ ማለት የእግዚአብሔር ክብር ወይም ‹‹ግሎሪ ኦፍ ጋድ›› ማለት ነው።

ግዮን:- ዶክሳ የተመሠረተው መቼ ነው?

ኤዶም:- ዶክሳ የተመሰረተው 2017 ዓ.ም ዓ.ም ነው። ቢዝነስ ማማከር ሥልጠናና ኢቨንት ላይ የሚሠራ ድርጅት ነው። መደበኛ የአሰራር ሂደትን ተከትለን በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት መጣን እንጂ በርካታ ሥራዎች ከካቦድ ጋር ይሠራሉ።

ቀደም ሲል ተቀጥሬ በምሰራበት ሰዓትም ከአለቃዬ ሥር ኾኜ እሰራ ነበር። ስለኾነም ሥራውን በደንብና በሚገባ አውቀዋለሁ። በነገራችን ላይ የካቦድና የዶክሳ ትርጓሜ ተመሳሳይ ነው። ዶክሳም ኾነ ካቦድ ማለት የእግዚአብሔር ክብር ማለት ነው።

ግዮን:- እንዲህ ዐይነት ስም ለማውጣት ያነሳሳሽ ምክንያት አለ?

ኤዶም:- እኔ ህይወቴን የምመራው እንደ ሮል ሞዴል የምከተለው የእግዚአብሔርን ቃል ነው። መንፈሳዊ ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ክብር በላይ ለኔ ትርጉም የሚሰጥ ነገር የለም። ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያለ ቃል ነው።  ስያሜውን ያወጣሁትም በእሱ መነሻነት ነው።

በራሴ አቅም ጥረትና ድካም ሥራዎችን የመሥራት ልምድ የለኝም፤ የሚያበረታኝ እና የሚደግፈኝ እግዚአብሔር ነው። እሱን ተደግፌ ነው ሥራዎችን የምሰራው። ስለዚህ ይህንንም ስም ያወጣሁት ለዚያ ነው። ቀጣይ የምመሠረታቸው ተቋማትንም ተመሳሳይ ስም ነው የሚኖራቸው፤ ስያሜያቸው ግን ምናልባት በተለያየ ቋንቋ የሚሰጥ ሊኾን ይችላል።

ግዮን:- ተቋማችሁ እስካሁን ምን ሥራዎችን ሰርቷል? አንቺ በስኬታማነት ተወጣሁት የምትይውና ምሥጋና ያገኘሽበት ሥራ አለ?

ኤዶም፡- በካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሺን 2012 ላይ አንድ ድርጅት ይዘን ነው ሽያጭ የጀመር ነው። ቦታው ቦሌ መድኃኔዓለም ነው። ትንሽ ቆየት ብለን ሁለት ሦስት ድርጅቶች ይዘን መስራት ጀመርን። ሳይቶቹ ቦሌ መድኃኔዓለም ስድስት ኪሎ እና ቡልቡላ ነበሩ። ያን ጊዜ ማለትም 2012 አካባቢ ብዙም እንደዚህ ማርኬቲንግ አልነበረም።

እኛ በተለምዶ ድለላ ብለን የምንጠራቸው ግለሰቦች ፈቃድ አውጥተው ሥራውን ይሰሩታል እንጂ በተቋም ደረጃ የሚሰሩት በጣም ጥቂት ነበሩ። እኔ ፈቃድ አውጥቼ ወደ ሥራው ስገባ አንድም ሰው አልነበረም በዘርፉ የተሰማራ።

የኾኖ ኾኖ ቀደም ሲል የጠራኋቸው ሳይቶች ላይ ሥራዎቻችንን በሚገባ ሰርተን ነው ሁሉንም ሳይቶቻቸውን ሸጠን ነው ያስረከብነው፡፡ በጣም ስኬታማ ሥራ ነበር የሰራነው፤ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ በጣም የተዋጣለት ሥራ ሰርተናል። አሁን እየሰራን ካለናቸው ድርጅቶች ውስጥ ከ20 በላይ የምስጋና ሰርተፊኬቶችንና ዋንጫዎችን አግኝተናል።

ድርጅታችን በሥራ ሂደትም ይኹን በዲስፕሊን የተመሰገነ ድርጅት ነው። ቲማችን ሥራ ወዳድ ቲም ነው። ስንጀምር ሰባት ስምንት ኾነን ነበር አሁን ወደ ከ60 በላይ ኾነናል።ዕቅዳችን ግን እስከ 100 ሆኖ መሥራት ነው፡፡

ብዙ ሥራዎችን አንኳኩተን ሳይኾን የምናገኘው ተፈልገን ነው። ደንበኞች ናቸው ቢሮ መጥተው የሚያናግሩን ወይም ደውለው የሚነግሩን። እኛም ብንኾን በቻልነው አቅም ጥሩ ፕሮጀክቶችን ይዘን ነው ወደ ከተማው መምጣት የምንፈልገው። አንዳንዴ ለሕብረተሰቡ የማይመጥኑ ሥራዎች ከገጠሙን ምናልባት ልናቋርጠው እንችላለን።

ሰውን አምነን ጀምረን አንድ ሁለት ከሸጥን በኋላ ውጤት ካላየንበት ሥራውን እናቋርጠዋለን። አብዛኛውን ጊዜ የሚገጥመን ስኬታማ ሥራ ስለኾነ ከብዙ ድርጅቶችን ጋር እስካሁን ውጤታማ ሥራ ሠራተናል። ለምሳሌ ከጃምቦ ሪልስቴት ፣ ከቴምር ሪል ስቴት፣  ከአኮያ ሪል ስቴት፣ በነዚህ ድርጅቶች በሙሉ የዋንጫ ተሸላሚ ነን።

ግዮን:- በርካታ ወጣቶችን በሴልስና ማርኬቲንግ አሰልጣናችኋል። ለሰልጣኝ ወጣቶች መስፈርቱ ምን ነበር? ምን ያህል ወጣቶችስ አሰለጠናችሁ? ይሄንና ሌላ ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዘን የቃለ ምልሱን ሁለተኛ ክፍል ይዘን በሚቀጥሉት ቀናት እናቀርባለን ።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 234 ግንቦት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ግዮን መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 9 2019 ዓ.ም ገበያ ላይ ውሏል !!!

-የግዮን እንግዳ አምዳችን :- ‹‹ምንጩና ጸሐፊው በማይታወቅ መረጃ መመራት አደገኛ...

ሸኽ መሃመድ አል አሙዲ ተጨማሪ 40 ሺህ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ አቅጣጫ ሰጡ

የMIDROC Investment Group ሊቀመንበር ሼክ መሃመድ ሁሴን አል...

የወርቅ ማዕድን ሠራተኛው ከመገደላቸው በፊት ቤተሰባቸው ከታጣቂዎች ጋር ያደረገው የመጨረሻው የስልክ ምልልስ

ማስጠንቀቂያ፡ ቀጥሎ የሚያነብቡት ታሪክ ሊረብሽዎት ይችላል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ...