‹‹ሀገር ጥለው የጠፉና ድርጅቶቻቸውን ለመዝጋት የተገደዱ አሉ››

Date:


አቶ አለማየሁ ከተማ
(የኢትዮጵያ ሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት)


ግዮን መጽሔት :- በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሪልስቴት ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠርና የከተማ ገጽታን የመለወጥ አቅም ቢኖረውም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በገቡት ቃል መሠረት ቤቶችን የማያስረክቡ አልሚዎች መበራከት ዘርፉን በልቅሶና በጭቅጭቅ እንዲታጀብ አድርጎታ፡፡ በርካታ ደንበኞች ጥሪታቸውን አፍስሰው ለዓመታት የቤት ተስፋ ሲሰንቁ፣ በአንጻሩ አንዳንድ አልሚዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ሳያውሉ ቀርተው፣ ዘርፉ አላዋጣ ሲላቸው አገር ጥለው እስከመጥፋትና ድርጅቶቻቸውን እስከመዝጋት ደርሰዋል።

ይህንን የዘርፉን የጠቆረ ስም ለማጠብና የአልሚውንም ሆነ የቤት ፈላጊውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት ‹‹የኢትዮጵያ ሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር›› ከአንድ ዓመት በፊት በይፋ ተመሥርቷል፡፡ የዛሬው የግዮን መጽሔት እንግዳም ይኽንን ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ በትጋት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ከተማ ናቸው፡፡

‹‹የሚጎርሱት በሚውጡት ልክ ነው›› የሚለውን መርህ ለዘርፉ ጤናማነት እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት አቶ አለማየሁ፣ የሪልስቴት አልሚዎች ሌቦችና ሕዝብ የሚያስቸግሩ ሳይሆኑ፣ በሕግና በታማኝነት የሚንቀሳቀሱ የሀገር ልማት አጋር እንዲሆኑ ለማድረግ የጀመሩትን ጉዞና የወደፊት ዕቅዶቻቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!


ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?


አለማየሁ:- አለማየሁ ከተማ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ኢሊባቡር ነው፡፡ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ እንደማንኛውም የአካባቢው ወጣት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በአካባበው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመማር እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርቴን በተግባረ ዕድ በመማር በኮንትራክተርነት ተሰማርቻለሁ፡፡ ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ በኮንትራክተርነት ከ40 ዓመታት በላይ ሰርቻለሁ፡፡ የራሴ ድርጅትም አለኝ፡፡


ግዮን፡- የድርጅታችሁ ስም ማን ይባላል?


አለማየሁ፡- የድርጅታችን ስም ‹‹አለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሕንፃ ተቋራጭ›› ይባላል፡፡ ተቋራጫችን መንገድ ይሠራል ፤ ግድብ ይሠራል ፤ ሕንፃዎችን ይሠራል ፤ በርካታ ተመሳሳይ ሥራዎችንም ያከናውናል፡፡ ይህ ተቋም በሥሩ ከ5ሺህ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡


ግዮን፡- የኢትዮጵያ ሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር መቼ ተመሠረተ?


አለማየሁ፡- የኢትዮጵያ ሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር የተመሠረተው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተበት ዋነኛ ምክንያት በሪልስቴት ሥራዎች ዙሪያ በርካታ ልቅሶዎችና ጭቅጭቆች አሉ፡፡ በመኾኑም እነዛን ችግሮች ለመፍታት እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ድርጅት ያስፈልጋል በሚል ነው የተመሰረተው፡፡ መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ያሉ አልሚዎች ማኅበርንም ኾነ የቤት ፈላጊ ገዢዎችን የሚጠቅም አዋጅ በቅርቡ አውጥቷል፡፡ እኛም የዘርፉን አባላት የሚጠቀም ተቋም መሠረተን፤ ከመሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እየሠራን እንገኛለን፤ ይህን ማኅበር ለመመስረት ብዙ ጊዜ ተሞክሮ ነበር ፤ ነገር ግን በየጊዜው እየተጀመረ ይወድቅ ነበር፤ አሁን ላይ ግን እነኢንጂነር ከድርና ኢንጅነር ጀበልን የመሳሰሉ ጠንካራ ሰዎች ስላሉ በሁለት እግሩ ቆሞ እኛንም ሊሰበስበን ችሏል፡፡


ግዮን፡- ማኅበሩን ለመመሥረት ያስፈለገበት ጉዳይ ምንድነው?


አለማየሁ፡- ማኅበሩን ለመመሥረት ያስፈለገው የቤት ገዢና የቤት ገንቢውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት በሚል ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ዙርያ ሁለቱም ጋር ችግር አለ፡፡ የቤት ገንቢው በጊዜው ቤቱን ገንብቶ አያስረክብም፡፡ የቤት ገዢውም በሰዓቱ ገንዘቡን አይከፍልም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሲባልም የኛ ድርጅት ሊመሠረት ችሏል፡፡


ግዮን፦ የማኅበራችሁ የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅድ ምንድነው?


ዓለማየሁ፡- የማኅበራችን ዕቅድ በዋናነት የአባላትን ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ አንድ መቶ የሚኾኑ አባላት ናቸው ያሉን፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ የሪልስቴት ተቋማት አሉ፡፡ ሁሉም እንዲመዘገቡ እንፈልጋለን፡፡ በሌላ በኩል ለአባላቱ ሥልጠና መሥጠት እንፈልጋለን፡፡ አባላቱ በተሻለ መንገድ ቤቶችን ገንብተው በሚያዋጣ መልኩ እንዲሸጡ እንመክራለን ፤ ምክንያቱም በዚህ የሥራ ዘርፍ ውስጥ በርካቶች ሥራው አላወጣ ብሏቸውና እንዳሰቡት ሳይኾን ቀርቶ ሀገር ጥለው የጠፉና ድርጅቶቻቸውን ለመዝጋት የተገደዱ አሉ፡፡ ከሚገባው ላይ ገንዘብ ሰብስቦ የተጠበቀውን ሥራ ሳያስረክቡ ከሀገር መሰደድና ራስን ለቀውስ መዳረግ አግባብ አይደለም፡፡ ሰው ‹‹የሚጐርሰው በሚውጠው ልክ ነው›› እንዲሉ እንዲህ ዓይነት ሥራ ሲሠራም ገንዘብ የሚሰበሰበው በሚሠራው ልክ ነው። ስለዚህ የኛ አንዱ እቅድ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች እንዲቀሩ በባለሙያ ተጠንቶ በኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች የተሻሉ ሥልጠናዎችን መስጠት ነው፡፡ ማኅበራችን ወደፊት ደግሞ በደንብ ሲጠናከር ለገንቢው ክፍል የሚሠራቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡
ለምሳሌ የመሬት ግዥን አንድ ተቋም አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ከምትገዛ አንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር ብትገዛ ዋጋው ይቀንሳል፡፡ በዚህ ስምምነት የማኅበሩ አባላት በአንድ ላይ ይመጡና ግዥ ይፈጽማሉ፡፡ ማንኛውም ነገር በቡድን ስንንቀሳቀስ ዋጋ ለመቀነስ ሰፊ ዕድል አለው፡፡ በጋራ ማሰብ በጋራ መሥራት አንድን ነገር ተነጋግሮ ከውጤት ማድረስ ይቻላል፡፡
ግዮን፦ ማኅበራችሁ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኅበር ጋር ምን ግንኙነት አለው?
አለማየሁ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ብዙ የኮንስትራክሽን ማኅበሩ አባላት የኛም አባላቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪ አብዛኞቹ አባላት ኮንትራክተር ናቸው። ኮንትራክተር በመኾናቸውም በእኛ ሪልስቴት ማኅበር አማካኝነት በኮንትራክተርነት ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ የሥራው ባሕሪ አንድ አይነት ስለኾነ መገናኘታችን ግድ ነው፡፡
ግዮን፡- የማኅበሩ አባል በመኾን የሚገኘው ጥቅም ምንድነው?
አለማየሁ፡- የማኅበሩ አባል በመኾን የሚገኘው ጥቅም የመጀመሪያው በዘርፉ ሰፊ ግንዛቤ መያዝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ከግዥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማቅለል ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከፍ ሲል እንዳልኩት ጉዳዮችን በጋራ ማስጨረስ የተሻለ ጥቅም አለው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የማኅበሩ አባል የኾነ አካል ወደ አላስፈላጊ መንገድ እንዳያመራ እንታደገዋለን፡፡ ይህ ማለት በኪሳራ እንዳይሸጥ ሌሎች ስሕተቶችንም እንዳይሠራ እንመክረዋለን፡፡
ግዮን፡- የማኅበራችሁ አባል ያልኾኑ ባለሪልስቴቶች አባል አንኾንም ቢሉ ምን አስገዳጅ ነገር ታደርጋላችሁ?

አለማየሁ፡- ለጊዜው አስገዳጅ ማዕቀፍ የለንም፤ ነገር ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደፊት በዚህ ዙሪያ ትልቅ ሥራ እንደሚከናወን ጥርጥር የለውም። መንግሥት ራሱ በዚህ ዙርያ እየሠራ ያለው ሥራ አለ፡፡ በዚያ የግንባታ ሥራ ላይ የሚሠማራ ማንኛውም አካል የሚታየው ደግሞ በማኅበሩ በኩል ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበሩ አባል መኾን በራሱ በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያሉት አባላት ራሱ ጥሩ ሥራ ለመሥራት በቂ ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ይዞ በርካታ ድንቅ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የማኅበራችን አባል ያልኾኑ ሪልስቴቶች ደግሞ በማኅበራችን አባልነት ቢታቀፉ ለእነሱ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ እኛም በየጊዜው የማደራጀት ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ የኢትዮጵያ ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱ የእኛ አባል ነው፡፡ ይህ ትልቅ የመንግሥት ተቋም አባላችን የኾነው ጥቅሙን አይቶ ነው፡፡ ይህ ተቋም እንደሚታወቀው የአገሪቱን የቤት ችግር እየቀረፈ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ነው።


ግዮን፡- መንግሥት የአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ቤቶች ግንባታ እቅድ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ ይህ ዕቅድ እናንተን ያካትታል?


አለማየሁ፡- በቅርቡ ሞርጌጅ ባንክ ይቋቋማል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያወጡት ዕቅድ አለ፡፡ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ቤቶች በዚህ አምስት ዓመት በመላው ኢትዮጵያ ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይኽን ተግባራዊ የሚያደርገው ሪልስቴቱ ነው፡፡ እኛ ከዕቅዱ በፊት ከጥናቱ ጀምሮ አብረን በሒደቱ ውስጥ ስንሳተፍ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር የመንግሥት ዋና ዓላማ የቤት አቅርቦት ለሕብረተሰቡ እንዲሟላ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ሊሠራ የሚችለውን ቤት ከዋጋና ከአዋጭነት አንጻር በማጥናት በኩል ትልቅ ሥራ ሠርተናል፡፡ በጥናቱ ውስጥ በርካታ ፕሮፌሰሮች፣ ኢኮኖሚስቶች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳትፈውበት ጥናቱ አልቋል፡፡


ግዮን፡- ጥናቱ የሚያካትተው አዲስ አበባን ብቻ ነው ወይስ ሁሉንም ኢትዮጵያን ያማከለ ነው?


አለማየሁ፡- ጥናቱ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል ያካተተ ነው። በክልል ከተሞች የሚያስፈልጉ ቤቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ቦታዎች ላይ 20 እና 30 ፎቅ መሥራት ላይኖርብን ይችላል፡፡ ጠረፍ አካባቢ ወደ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ አፋር የመሳሰሉት አካባቢዎች የሚያስፈልጉት ቤቶች ቪላ ቤቶች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የግንባታ ሂደቶቹ እንደሕብረተሰቡ ፍላጎትና እንደአካባቢው ሁኔታ የሚተገበሩ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ላይ አንድ ረጅም ፎቅ ለመኖሪያ ቤት ስለተገነባ ትግራይ ላይም ተመሳሳዩ መደረግ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ የግንባታ ሥራው ሲከናወን እንደአካባቢው ሁኔታ የመሬት ዓይነት የማኅበረሰቡ ፍላጎትና እንደከተማው ይዘት ነው፡፡ ለምሳሌ መሬት ባዶ ኾኖ ከተማ ትንሽ ከኾነ ቪላዎች በደምብ መሥራትና ከተማውን ማሳደግ ያስፈልጋል።


ግዮን፡- አባሎቻችሁ አብዛኞዎቹ አዲስ አበባ ነው ያሉት፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የሪልስቴት አልሚዎችን ለማካተት ምን ዓይነት ሥራዎችን እየሠራችሁ ነው?


አለማየሁ፡- ማኅበራችን በተመሠረት በዚህ አንድ ዓመት ውስጥም የአፍሪካ ሪልስቴት ማኅበር አባል ኾኗል። ቀጥሎ የዓለም ሪል ስቴት አባል ይኾናል፡፡ የውጭ ሪልስቴት አልሚዎችም ወደ አገራችን እየገቡ ነው፡፡ እነሱም አባል ይኾናሉ፡፡ ስለዚህ እንኳን የውስጥ የውጭውንም የአባልነት ሂደት እያጠናከርን እንቀጥላለን፡፡ አባል ሲኮን በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከባንክና ከመሬት ጋር በተገናኘ ጥሩ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ አሁን ከዓለም ባንክ ሰዎች እየመጡ እያነጋገሩን ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ተጠቃሚ መኾን የሚቻለው በአባልነት በመታቀፍ ነው፡፡


ግዮን፡- የአፍሪካ ሪልስቴት ማኅበር አባል በመኾናችሁ የተጠቀማችሁት ምንድነው?


አለማየሁ፡- የአፍሪካ ሪልስቴት አባል በመኾናችን የመጀመሪያው ጥቅማችን የ2026 የአፍሪካ ጉባኤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከናወን ማድረጋችን ነው። አባል ስለኾንን ነው አዲስ አበባ ላይ ጉባዔው የሚደረገው፡፡ አባልነት ባይኖር ኖሮ አይመጡም ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት እኔም በግሌ የተሳተፍኩበት ሞሮኮ ላይ ነበር የተካሄደው፡፡ አሁን ግን እኛ አባል በመኾናችን ጉባዔውን አዲስ አበባ ሊያደርጉት ችለዋል፡፡ ከዚያ በፊት ናይጄሪያና ኡጋንዳ ተከናውኖ ነበር፡፡ በሀገራችን ይህ ጉባዔ መካሄዱ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ በጉባዔው የሚሳተፉት ባለሀብቶች ሀገራችንን አይተው ዝም ብሎ አይሄዱም፡፡


ግዮን፦ ማኅበሩ እንደማኅበር ይህን ጥቅም ሲያገኝ አባላቱስ የሚያገኙት ጥቅም ምንድን ነው?


አለማየሁ፡- አባላቱ በአፍሪካ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች ላይ መሳተፍ ቢፈልጉ የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሪልስቴት ባለሀብቱ በአፍሪካ ቢሰማራ የእኛ ማኅበር አባል በመኾኑና እኛ ደግሞ የአፍሪካ ሪልስቴት ማኅበር አባል በመኾናችን እንደ አባል ታይቶ የፈለገውን ሥራ በተቀላጠፈ መንገድ ማከናወን ይችላል፡፡ ማኅበሩ እርስ በእርሱ ስለ አባሉ ይነጋገራል ማለት ነው ፤ ይህም የባለሀብቱን ሥራ ቀላል ያደርግለታል፡፡


ግዮን፡- በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት በተለይም እንደኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ባሉ አገራት ኢንቨስት እያደረጉ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?


አለማየሁ፡- በርካታ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በአፍሪካ ኢንቨስት ያደርጋሉ የሚባለው ነገር የምቀበለው ባይኾንም እንደ ሀገራችን ስፋትና እንደ ቁጥራችን ብዛት አፍሪካ ላይ በተሻለ መጠን መሥራት እንችል ነበር ባይ ነኝ። በተጠቀሱት ሀገራት ያሉትን ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶች አውቃቸዋለሁ። ለምሳሌ እኛ ጋቦን አምስት ሺ ቤት እንድንሠራ ተጋብዘናል፡፡ ከዚህ አንጻር በርካታ ኢትዮጵያ ባለሀብቶች በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ብዙ ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አልተጠቀምንበትም፡፡


በሀገራችንም እንዲሁ ሰፊ እድል አለ፡፡ እርሱንም በበቂ ሁኔታ አልተጠቀምንበትም። በሀገራችን እስካሁን ሪልስቴት አልሚውም ገዢውም አልተጠቀሙም፡፡ ከዚህ በፊት ከእኛ ተቋራጭ ጋር የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶችም ጠፍተው ቀርተዋል፡፡ የጠፉት መሥራት የሚችሉትን ነገር ባለመሥራትና አንዳንዶቹም ለራሳቸው ታማኝ ባለመኾናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክት አሥር ቢሊዮን ብር እኔ ተፈራርሜ ከኾነ አዋጥቶኝ ሥራውን ሠርቼ ለሰራተኞቼ ደመወዝ ከፍዬ ቢያንስ 10 በመቶ አትርፌ ሥራውን ማስረከብ አለብኝ፡፡ ትርፍ ከሌለው እንኳን ሥራውን አጠናቅቄ ማስረከብ ይኖርብኛል፡፡ የአንዱን ሥራ በሌላው ማጣፋት አይቻልም፡፡ እንደዚያ ሲኾን ኪሳራው እየሰፋ ይሄድና መጨረሻ ላይ በኪሳራ ምክንያት ከሥራው ውጪ መኾንን ያስከትላል፡፡


ግዮን፡- በእኛ ሀገር የሚከሰቱ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ከእውቀት ማነስ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል? ትርፍና ኪሳራን አለማወቅ፤ ሠርቶ ማስረከቢያ የጊዜ ገደብ አለማስቀመጥ፤ የመሳሰለው ችግር የሚመጣው ከምንድነው?


አለማየሁ፡- የእኛ ሀገር ነጋዴ መነሳት የሚፈልገው ከሌለው ነገር ላይ ነው፡፡ በውስጣችን ኢጎ አለ። ባለሙያዎችን አማክረው ሁሉንም ነገር አስልቶ ወደ ሥራ የሚገባው ጥቂት ነው፡፡ ባለሙያን አለማዳመጥና አለማማከር ትልቁ የባለሀብቱ የኪሳራ መንገድ ነው፡፡ እኔ መኪና እየነዳሁ እሱ በእግሩ እየሔደ ደግሞ ይመክረኛል የሚል አለ፡፡ እውቀት ማለት የአንድ ግለሰብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ እውቀት ማለት በዘርፉ ያሉ ሰዎች ሁሉም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ጥቅም ላይ ማዋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዶክተር እንዳጠናችው የአካል ክፍሎች ሁሉ እውቀቱ እንደሚለያየው በእኛም ዘርፍ አንድ ግለሰብ ብቻውን የሚያውቀው በአብዛኛው ስለአንድ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

አንድ ኩባንያ በርካታ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉታል፡፡ ስኬታማ መኾን የሚቻለው ይህ ሲኾን ነው፡፡ ሚስጥራዊ ጉዞ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም፡፡ በዚህ የሥራ ዘርፍ ላይ ያለው አብዛኞቹ አካላት አንድን የሥራ ሂደት በሚስጥር ይዘው መከወን ይወዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከእውቀት ማነስም ይሁን በሌላ ምክንያት ብዙዎችን ለኪሣራ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ አንድ ተቋም ሥራውን በግልጽ መከወን ይኖርበታል፡፡ ስኬቱን ወይም ውድቀቱን በአደባባይ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ውድቀት ካለ ለመነሳት ከባድ አይኾንም፡፡ ስኬት ከኾነም በአደባባይ ተረጋግጦ ለሌሎች መማሪያ ይኾናል፡፡ ካለዚያ ግን ‹‹ጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል›› የሚሉትን ዓይነት ይኾናል፡፡


ግዮን፦ ማኅበራችሁ ውስጥ ላሉ አባላትም ይሁን አዲስ ለሚመጡ አባላት ምን ምክር ይሰጣሉ? የዚህን ጥያቄና የሌሎቹን ጥያቄዎች መልሶች ይዘን በሚቀጥሉት ቀናት ይዘን እናቀርባለን ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የሰላም ስምምነት ሳይፈጸም የንግድ መርከቦች ጉዞ እንደማይጀምሩ የነዳጅ ጫኝ ኩባንያ ኃላፊ ተናገሩ

የሲውዲን ነዳጅ አጓጓዥ ኩባንያ የሆነው ‘ስቴና በልክ’ ዋና ስራ...

የታሪካዊው ቁልቢ ገብርኤል የዕድሳት ጥሪ ፦ የ134 ሚሊዮን ብር ግዙፍ ፕሮጀክት

! ከተገነባ 64 ዓመታትን ያስቆጠረውና በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን የሚሳለሙት...

መርስክ የበርበራ ወደብ የጭነት አገልግሎቶችን ለጊዜው አቋረጠ

የዓለማችን ግዙፍ የመርከብ ድርጅት የሆነው መርስክ ፣ ወደ በርበራ...

የምርጫ ካርድ፡ የአገር ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ

ግዮን መጽሔት :- በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ ውስጥ ምርጫዎች የሥልጣን...