በአሜሪካ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት ላይ በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት በመላ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች መሰረዛቸውና መዘግየታቸው ለሦስተኛ ቀን ቀጥሏል።
የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲን ዱፊ፣ መደበኛ የበረራ አገልግሎት እስከ ሰኞ ድረስ እንደማይጀምር ለቢቢሲ አጋር ሚዲያ ሲቢኤስ ተናግረዋል።
በተለይም እሁድ ዕለት በአሜሪካ ከ8 ሺህ በላይ በረራዎች መዘግየት ሲያጋጥማቸው፣ 2 ሺህ 400 የሚሆኑት ደግሞ ተሰርዘዋል። ይህም በአየር ማረፊያዎች የተሳፋሪዎች መጉላላትና መጨናነቅ እንዲፈጠር አድርጓል።
የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (FAA) በረራዎች እንዲታገዱ መወሰኑን አርብ ዕለት ባስታወቀበት ወቅት ከ3 ሺህ 500 በላይ አውሮፕላኖች በአየር ላይ እንደነበሩ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች አቅጣጫቸውን ሲቀይሩ፣ ሌሎች ደግሞ ወደታቀደላቸው መዳረሻ መድረሳቸው ተመልክቷል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ የበረራ መስተጓጎሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከአብራሪዎች ጋር ለመገናኘት የሚጠቀሙበት ወሳኝ የግንኙነት መስመር ላይ በተፈጠረ ብልሽት የተነሳ ነው።
ከመዳብ ገመድ ወደ ፋይበር ኦፕቲክስ የቴሌኮሙኒኬሽን መስመሮች ሲቀየሩ የተገጠመው ራውተር የተሳሳተ መልዕክት ማስተላለፍ መጀመሩ ለችግሩ መንስኤ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል ጊዜ እንደሚወስድም አመልክተዋል።
የቴክኒክ ችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ለመለየት ምርመራ እየተካሄደ ነው።
በተያያዘ ጉዳይ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው “ትሩዝ ሶሻል” ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የሀገሪቱ ሕግ አውጪ አካል የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማዘመን ተጨማሪ በጀት እንዲያጸድቅ ጥሪ አቅርበዋል።
