
አቶ ሀብቴ መስፍን የ‹‹ሪቮካፕ ኮፊ ኮርፖሬሽን›› መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ ከሀገራቸው ከወጡ ዘለግ ያለ ዕድሜን ቢያስቆጥሩም፣ ሀገራቸውንና ወገናቸውን ለማገዝ በሚያስችሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎች ውስጥ የተሠማሩ ሀገር ወዳድ ዜጋ ናቸው፡፡ በተለይም በርካታ የፖሊሲ ችግር እንዳለበት በሚተቸው የትምህርቱ ዘርፍ የቻሉትን ክፍተት ለመድፈን በማሰብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን ወደ ሀገር ቤት ልከዋል፡፡ በዚህም ተማሪዎችን፣ መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አግዘዋል፡፡ አቶ ሀብቴ አሁንም ይኽንን ተሳትፏቸውን አጠናክረው በመቀጠል በመጪዎቹ ጊዜያት በርካታ የመጻሕፍት እጥረት ላለባቸው ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ተቋማት ለመለገስ በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ኾኖም እንዲህ ያለውንና የበርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ በእጅጉ የሚጠይቀውን ይኽን ትውልድ የማዳን ሥራ በውጪ የሚኖሩ ወገኖች እንዲደግፉም ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር በአጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ እና እያከናወኗቸው ባሉ አጋዥ ተግባራት ዙርያ የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ሪቮካፕ በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ሥርዓት ለማገዝ እንቅስቃሴ ከጀመረ ምን ያህል ጊዜ ኾነው?
ሀብቴ፡- ሪቮካፕ በትምህርት እንቅስቃሴው ዙሪያ ሥራ ከጀመረ ከዐሥር ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡
ግዮን፡- የትምህርት ሥርዓቱን በዚህ መጠን ለማገዝና ለመደገፍ ያነሳሳችሁ ቁልፍ ጉዳይ ምንድነው? እንደግለሰብም እንደተቋምም?
ሀብቴ፡- ሪቮ ካፕን ስናቋቁም በምን ዓይነት መንገድ ወገንን ማገዝ እንችላለን የሚል ጥያቄ ነበረን፡፡ ይህን ጥያቄ ስናስብ ሦሰት ሴክተሮች ላይ ማተኮር እንዳለብን ተረዳን፡፡ እነዚህ ሦስት የሪቮ ካፕ ፋውንዴሽን ምሦሶዎች የመጀመሪያው ጤና ሲኾን፣ ሁለተኛው ትምህርት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ንግድ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ሁሉም መሠረታዊ መኾናቸውን ብናምንም ቶሎ መድረስ የሚቻለው ግን ትምህርት ላይ ስለነበር በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ ሠርተናል፡፡ ለምን ትምህርት ከተባለ ብዙ መለኪያች አሉት፡፡ ከመለኪያዎቹ አንዱ ለሀገር ቅርብ ከመኾናችን ጋር ተያይዞ ብዙ መረጃዎች ያሉን በመኾኑ ነው፡፡ አጠቃላይ የትምህርት ሒደቱን እንከታተላለን፡፡ በርካታ ዩንቨርሲቲና ኮሌጆች ተቋቋሙ ተብሎ ከዚያ የሚወጡ ወጣቶች ያላቸው የትምህርት ዝግጅትና ብቃት አጠያያቂ መኾኑንም እንረዳለን፡፡ ትምህርትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት እንዳለ ኾኖ ያለበትን የጥራት ችግር ግን በደንብ ተገንዝበናል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ሀገር የሚያጠፋና ትውልድ የሚያመክን በመኾኑ አንድ ነገር ማድረግ አለብን በማለት የትምህርት ሥርዓቱን ማገዝ ጀመርን፡፡
ግዮን፡- በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ፖሊሲ መሠረታዊ ችግር ምንድነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
ሀብቴ፡- የትምህርት ፖሊሲውን መተቸት አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ቢሻሻሉ ብለን የምናምናቸው ነገሮች አሉ፡፡ የአንድ ሀገር የትምህርት ፖሊሲ የሚቀረጸው በሀገሪቱ ፍላጎት ነው፡፡ ትምህርት የማስተምረው ማንን ነው? ትምህርት የማስተምረው ለምንድን ነው? በምን ዓይነት ሙያ ላይ ነው የተማረው ማኅበረሰብ የሚሠማራው? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የትኛውም ሀገር ላይ ያለ የትምህርት ፖሊሲ በሀገሪቱ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት አስገብቶ ነው የሚቀረጸው፡፡ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይልን ለሚያስፈልገው የኢኮኖሚ ማዕከል ማዘጋጀት የትምህርት ተቋማት ሥራ ነው፡፡ የትምህርት ዓላማውም ከመጀመሪያው አንስቶ ይኸው ነው፡፡ ለአንድ ሥራ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ለሥራው የሚመጥን ዕውቀት ወይም የትምህርት ዝግጅት ሊኖረው ይገባል፡፡
ሀገራችን ውስጥ ምንድነው የምናስተምረው ስንል ከ1-12ኛ ያለውን ትምህርት እንደ አጠቃላይ የሰው ልጆችን ጠቅላላ ዕውቀት በተለይም ከማንበብና መፃፍ ውጭ ያሉ እንደ ሂሳብና ፊዚክስ ያሉ ዕውቀቶችን ሊማሩ የሚችሉበት ነው፡፡ ማንን ለየትኛው ኢኮኖሚ ነው የምናዘጋጀው ከተባለ ደግሞ ኢትዮጵያ የገበሬዎች ሀገር እንደመኾኗ መጠን ለዚያ የሚመጥን ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው ከ85 በመቶ በላይ የሚኾነው የሀገሪቱ ሕዝብ ገበሬ ነው፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የቆመውም በግብርና ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የትምህርት ሥርዓቱ እያዘጋጀ ያለው ገበሬ ነው? ወይንስ ግብርናውን ሊቀይር የሚችል የሰው ኃይል ነው? ይኼ በሀገራችን ያለውን የትምህርት ሥርዓት ዓላማ እንዲመረመር የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሀገራችን በዚህ ዙሪያ በቂ ጥናት የተገደረገበት አይመስለኝም፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን ዶክተሮች፣ ኢንጅነሮችና ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱን ሁኔታ መቀየር የሚችሉ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
ግዮን፡- በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ፖሊሲ በርካታ ትችቶችን ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ አንፃር ቅድመ ብልጽግና እና አሁን ባለው ብልጽግና ዘመን ያለውን የትምህርት ፖሊሲ እንዴት መገምገም ይቻላል?
ሀብቴ፡- እንደእኔ እውነት ለመናገር በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው የትምህርት ፖሊሲ ልዩነት አላየሁበትም፡፡ ትምህርት የሀገር ትልቅ ሴክተር ነው፡፡ አስተማሪዎችና ተማሪዎች ያሉበት ከሀገሪቱ 25 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ የሚሳተፍበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ የትምህርት መማር ማስተማር ሂደት ላይ መሠረታዊ ለውጥ አለ ብዬ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ በጥቅሉ በሁለቱ መንግሥታት የትምህርት ሥርዓት ሂደት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡ እኔ እንደማውቀው ከአፍሪካ አንፃር እንኳን ብናየው መንግሥት ለአንድ ተማሪ በዓመት የሚያወጣው በመቶኛ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ተማሪዎችም ባላቸው ዕምቅ አቅም ድረስ ተምረው እየወጡ ነው ወይ የሚለው ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡
ግዮን፡- የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ሀብቴ፡- የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ሁሌም ጥያቄ ውስጥ ያለ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት በየጊዜው እየቀነሰ እንደመጣ ብዙ መረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ትምህርት መማር በጃንሆይ ጊዜ ትልቅ ክብር ነው፡፡ የእንጀራ ማግኛም ነው፡፡ ተምሮ ጥሩ ሥራ ማግኘት የተመለደ ነበር፡፡ ብዙ ተማሪም ሕይወቱ በዚያ መንገድ ይቃና ነበር፡፡ አስተማሪዎቹም ጎበዞች ነበሩ፡፡ ያ ዘመን የተነቃቃ የትምህርት ዘመን የነበረበት ነው፡፡ በዚያን ዘመን አንደኛ ደረጃ ጨርሶ የወጣ ሰው ጥሩ ችሎታ ይኖረው ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን የዚያ ዘመን ተማሪዎች ከዚህ ዘመን ጋር ሲነፃፀሩ በጣም ትልቅ የኾነ የዕውቀት ልዩነት አላቸው፡፡ ይኼ የኾነው የትምህርት ሥርዓቱ እየደከመ በመምጣቱ ነው፡፡
ግዮን፡- እንደ ሪቮካፕ ፋውንዴሽን እስካሁን እናንተ ባደረጋችሁት እገዛ የትምህርት ሂደቱ ላይ ምን ለውጥ መጥቷል ትላላችሁ?
ሀብቴ፡- እኛ የመጻሕፍት እገዛ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ያመጡትን አስተዋፅዖ ለመረዳት ግን የምንፈልገውን ያህል መረጃ እያገኘን አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶችም፣ የትምህርት ቤት ርዕሰ መስተዳድሮችም፣ የትምህርት ጽ/ቤት ቢሮዎችም እነዚህ መጻሕፍት በሚገኙበት አካባቢ ዙሪያ ጥናት ሠርተው እንዲልኩልን ጠይቀን ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ገጠር ውስጥ ስላሉ በቂ መረጃ እያገኘን አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሚነግሩንን ስንሰማ ግን የመጻሕፍቶቹ ጠቃሚነት ለተማሪዎቹ ብቻ ሳይኾን ለመምህራን፣ ለግብርና ባለሙያ፣ ለጤና ባለሙያ እና ለተለያዩ የሙያ ዘርፎች መኾኑን ጭምር ይነግሩናል፡፡ የመጻሕፍቶቹ መኖር ለማመሳከሪያነት እጅግ ጠቅሞናል ብለውናል፡፡ የተሰወሰኑ ትምህርት ቤቶች በተለይ ከብሔራዊ ፈተና ጋር ተያይዞ ደረጃቸው ከፍ እንዳለም ሰምተናል፡፡ በእርግጥ ድሮም ቢኾን በዚህ ዙሪያ የነበረን ግንዛቤ ነበር፡፡ ለምሳሌ ባለፈው 12ኛ ክፍል ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎችና ውጤቱ፣ ቀድመን የገመትነውን ኾኖ አግኝተንዋል፡፡ ምን ያህል ሰው ተፈትኖ ስንት ሰው እንዳለፈ አይተናል፡፡ ይኼ የእኛን የቀድሞ አስተሳሰብ እውን ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በእኛ በኩል የቀረቡት የመጻሕፍት እገዛ በጣም ይጠቅማሉ፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ በዶንኪ ቲዩብ የድጋፍ ማስታወቂያ አሠርታችሁ ተመልክተናል፡፡ ማስታወቂያው ያስፈለገበት ምክንያቱ ምን ነበር?
ሀብቴ፡- ይህን መንገድ ስንጀምር ጥቂት ተማሪዎችንም ቢኾን መርዳት ብንችል ብለን ነበር፡፡ አሁን ግን በ500 ሺህ የሚቆጠር መጻሕፍት ሀገር ውስጥ ማስገባት ችለናል፡፡ ይህ ማለት አንድ መጽሐፍ ቢያንስ በዓመት ውስጥ ከ5-10 ሰው ያነበዋል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው የመጻሕፍት መጠን ከ150 ሚለዮን በላይ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ 150 ሚሊዮን የሚደርስ የትምህርት መጻሕፍት የለም፡፡ ይህ ነገር አሁን ላይ በእኛ ጥረት ብቻ የሚፈታ እንዳልኾነ ይታወቃል፡፡ እኛ በራሳችን ጥረት የቻልነውን አድርገናል፡፡ ወደፊትም ደግሞ አቅም በፈቀደ መጠን እናደርጋለን፡፡ መተባበር ከተቻለ እና እኛም የቢዝነስ ሰዎች ከመኾናችን አንፃር ቢዝነሱ ከተሻሻለ የበለጠ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ከዶንኪ ቲዩብ ጋር በመነጋገር ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቡናችንን ቢገዙ እኛ መጽሐፍ የመላካችንን አቅም ያሰፋዋል፡፡ ጠቅላላ ዕቅዳችንም አንድ ሚሊዮን መጽሐፍ ለመድረስ ነው፡፡ አሁን ያለነው ግማሽ ሚሊዮን ላይ ነው፡፡ ይህን ከ500 ሺ በላይ መጻሕፍት ከተባበርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ልንከው እንችላለን የሚል ግምት አለን፡፡ በተጨማሪም ማስታወቂያ ያስፈለገው ሀገር የምንሠራውን ሥራ ስለማያውቅ ግንዛቤ ለመስጠት ሲባል ነው፡፡
ግዮን፡- በውጭው ዓለም ያለው የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ልዩነታቸው እንዴት ይገለፃል? የእኛ ሀገር ሁኔታስ እንዴት ይመዘናል?
ሀብቴ፡- በሁሉም ዓለም ላይ ማለት ይቻላል ትምህርት በመንግሥት በኩል ለዜጎች የሚሠጥ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ የኾነ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ደግሞ እጅግ ሰፋ ያለ የግል ትምህርት ቤት ፕሮግራሞች አሏቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሀገራት ላይ አብዛኛው ዜጋ የሚማረው የመንግሥት ትምህርት ቤት ነው፡፡ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ሳይኾን በከፍተኛ የትምህርት ደረጃዎች ላይም የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ በየትኛውም ሀገር የትምህርት ፖሊሲ የሚቀረጸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ የግል ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ እየበዙ መጥተዋል፡፡ ካለን የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ ግን ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች መበራከት እኔ በሁለት መንገድ አየዋለሁ፡፡ የመጀመሪያው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ጫና መቀነስ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ውድድር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ድሮ እንደምንሰማው ሳንፎርድ፣ አሜሪካን ስኩል፣ ቅዱስ ዮሴፍ ከሚባሉ የትምህርት ተቋማት ይወጡ የነበሩ ተማሪዎች በጣም ጎበዞች ነበሩ፡፡ በመንግሥት በኩልም ቀደም ሲል እንደ ዊንጌትና ኩየራ የመሳሰሉ ተቋማት የትምህርት አሠጣጣቸው ከሌላው የተሻለ ነበር፡፡ አሁን ግን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በዚህ ደረጃ የሉበትም፡፡
አሁንም ቢኾን ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ይልቅ የግሎቹ ተመራጭ ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሕዝባችን የግል ማስተማር አይችልም፡፡ ያም ቢኾን ግን አሁንም በርካታ ወላጅ ተቸግሮም ቢኾን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ይጥራል፡፡ በሌላ በኩል የግልና የመንግሥት የትምህርት ተቋማት በቂ የትምህርት መሳሪያ አላቸው ወይ ሲባል የግል ትምህርት ቤቶች ከሰው ኃይል አንፃር መርጠው የመቅጠር ዕድል አላቸው፡፡ ያም ኾኖ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሰፊ ኢንቨስትመንት የተደረገባቸው አይደሉም፡፡ የተሟላ ቤተ መጻሕፍት፣ የተሟላ ላቦራቶሪ፣ ወዘተ ያላቸው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ከአርባ ዓመት በፊት አንደኛ ደረጃ የነበረ ትምህርት ቤት እስካሁን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ምንም ነገር ኢንቨስት ሳያደርግ የሕዝብ ቁጥሩ ግን አድጓል፡፡ አብዛኛው የዓለም ሀገር ከ4-5 በመቶ ጂዲፒ ለትምህርት ዘርፍ ያውላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህን ያህል መቶኛ የለም፡፡ የጂዲፒያችን ሁለት በመቶ እንኳን ለትምህርት የሚውል አይመስለኝም፡፡ ለሌላው ዘርፍ እናተርፍበታለን ብለን በጀት የምንመድብለትን ያህል በወጣቶች ላይና በትምህርት ላይም ተመሳሳይ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት የሚሰጠው የመውጫ ፈተና በተማሪዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖራል? የፈተናው ጥቅምስ ምነድነው?
ሀብቴ፡- የመውጫ ፈተና መስጠት በሌላው ዓለም ላይም የተለመደ ነው፡፡ ከዩንቨርሲቲ ዲፕሎማ ሊገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ አንድ ተማሪ ሜዲሲን የሚሰራ ቢኾን የቦርድ ፈተና የሚባል አለ፡፡ ተማሪው ያንን የማለፍ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ፈተና የተማሪው የብቃት ማረጋገጫ ነው፡፡ ነገር ግን ከእኛ ሀገር አንፃር በተለይ በግል ኮሌጆች የተለመደ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ተማሪዎች በክፍል ሳይኖሩ እንዲሁ ድግሪ ይሰጣሉ ይባላል፡፡ አንዳንዴም ከውጭ ሀገር እየተገዛ እንደሚመጣ ይነገራል፡፡ ይህ የመውጫ ፈተና የመጣውም ይህን ችግር ለመቅረፍ ይመስለኛል፡፡ እንደመጥፎ አላየውም፡፡ ነገር ግን አራት ዓመት ሙሉ ሲማሩ ያልፈተናቸውን ተማሪዎች ዛሬ መፈተን የተማሪውን ሥነ ልቦና ሊጎዳ ይችላል፡፡
ግዮን፡- ማኅበራዊ ሚዲያ በአንባቢያን ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው ይባላል፡፡ ይህን ለማከም እና አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር ምን ቢሠራ ጥሩ ነው?
ሀብቴ፡- የተለያዩ ሪፖርቶች ሲወጡ እንሰማለን፡፡ ሕይወታችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቂ ኾኗል፡፡ ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት የነበረን አኗኗርና የአሁኑ አኗኗራችን ለየቅል ነው፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው ጊዜያችን የሚያልፈው በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በአላስፈላጊ ተዝናኖቶችና ጥያቄዎች ነው፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ አቀንቃኞች ‹‹ኮንቴንት ክሪኤተር›› ይባላሉ፡፡ ነገር ግን አይደሉም፡፡ ተመልካች ወይም ተከታይ ባገኙ ቁጥር ሁሉንም ነገር ይላሉ፡፡ ወጣቱ ከዚህ መቆጠብ አለበት፡፡ ምን አልባት የሚያዝናኑ ቢኾኑም ነገ ላይ ድምር ውጤታቸው ሕይወት የሚያበላሽ ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ወጣት በማኅበራዊ ሚዲያ ጊዜውን እየተሰረቀና እየተቀማ መኾኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጊዜን ማጥፋት አግባብነት የለውም፡፡
ግዮን፡- በምዕራቡ ዓለም እምቅ የኾነ እውቀት የሚያጋሩ መጻሕፍትን ወደ ሀገርኛ ቋንቋዎች ተርጉሞ በየደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች ስለማቅረብ ፋውንዴሽናችሁ ያቀደው ነገር አለ?
ሀብቴ፡- በዚህ ዙሪያ ብዙ ጊዜ እንመካከራለን፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ላይ የሚሠሩ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ጃኔ ከርተዝ የምትባል ሴት አለች፡፡ ታዋቂ የልጆች መጻሕፍት ደራሲ ነች፡፡ የ‹‹ኢትዮጵፒያን ሪድስ›› አንዷ መሥራች ነች፡፡ እነርሱም ለመተርጎም ይጥራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ምን ያህል መጻሕፍት ተርጉሞ ማቅረብ ይቻላል የሚል ጥናት አድገን ነበር፡፡ ያገኘነው የተርጓሚ መጠን ቁጥሩ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየቀለለ የመጣ ይመስለኛል፡፡ እንደ ጎግል ትራንስሌት አይነት በርካታ የመተርጎሚያ መንገዶች መጥተዋል፡፡ እኔ ልጅ በነበርኩበት ሰዓት በቤተ መጻሕፍት አንድ ዲክሽነሪ ለማግኘት ሦስትና አራት ሳምንት ጠብቄ ነው፡፡ ዛሬ ግን ሁሉም ነገር በእጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ ብዙ ነገሮች ቀለዋል፡፡ በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ነገሮች ዋጋ እየቀነሱ ሲሄድ ብዙ ነገር ቀላል ይኾናል፡፡ መረጃ አብዮት ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ድሮ አንድ ሀገር እውቀት ነው የሚባለው ነገር ሁሉ አሁን ዓለማቀፋዊ ኾኗል፡፡ ሰው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መማር ይችላል፡፡
ግዮን ሪቮ ካፕ ለመጻሕፍት ከሰጠው ትኩረት አንፃር ወደፊት በአንዳንድ አካባቢዎች ቤተ መጻሕፍት የመገንባት እቅዶች ይኖሩታል?
ሀብቴ፡- ቤተ መጻሕፍት የመገንባት ዕቅድ የለንም፡፡ አሁን የእኛን እገዛ የሚፈልገው ነገር ላይ ብቻ ነው ትኩረት የምናደርገው፡፡ ነገር ግን ከተማ ውስጥም ይሁን በገጠሩ አካባቢ የሚሰሩ ቤተ መጻሕፍት ካሉ የሚፈልጉትን መጻሕፍት ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከዚያ ውጭ ግን እኛ የራሳችንን ቤተመጻሕፍት ከፍተን ለሕዝቡ እንሰጣለን የሚለው ነገር አድካሚና የረጅም ጊዜ ሥራ ስለኾነ ተማሪዎችን የምንደርስበት ሥራ ላይ ነው የምናተኩረው፡፡
ግዮን፡- እንደማጠቃለያ በትምህርት ሥርዓቱ ዙርያ የሚያነሱት ነገር ካለ?
ሀብቴ፡- በትምህርት ዙሪያ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ትምህርት ለአንድ ሀገር ያለው ፋይዳ እያታወቀ አንዳንድ የትምህርት ሴክተር ውስጥ ያሉ አካላት የሚያደርጉትን ነገር ማየት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይኼ ችላ ሊባል የሚገባው ነገር አደለም፡፡ እኛ የራሳችንን ጥረት ብናደርግም በትምህርት ሥርዓቱ ዙሪያ ያለው ነገር ካልተስተካከለ ዞረን ዞረን ያው ነው፡፡ ‹‹የሌላ ሰው ልጅ ወደቀ የኔ ልጅ አልደወቀም›› ከሚል አስተሳሰብ መውጣት አለብን፡፡ የትምህርት ጥራት ችግር የሁሉም ሰው አልፎም የዜጋ ችግር ነው፡፡ አንድ ተማሪ በወደቀ ቁጥር ሀገር እየወደቀ መኾኑን ልንረዳ ይገባል፡፡ ብዙ ተማሪ በወደቀና ባላወቀ ቁጥር የሚጎዳው ሀገር እንጂ ግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ የትምህርት ፖሊሲ በደንብ መጠናት ይኖርበታል፡፡ አሁን እንደምንሰማው ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ወደ ዐረብ ሀገር መላኩን ነው፡፡ ሔደው ደግሞ 300/400 ዶላር ብር እንደሚያገኙ ነው የተነገረው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በደንብ ቢማሩና ነርስ ኾነው ቢወጡ 2500 ዶላር በወር ማግኘት ይችላሉ፡፡ ቶሎ ሊደርስ የሚችል ትምህርትም በጥልቀት ቢማሩ በቀላሉ ብዙ ነገር ሊለወጥ ይችላል፡፡ ትውልዱ መጻሕፍት ላይ ቢያተኩር ደግሞ የእውቀት ባለቤት መኾን ይችላል፡፡
ግዮን፡- በአንባቢዎቻችን ሥም እናመሰግናለን፡፡