“የሀገሪቱ የፖለቲካ ቁመና ቀውስ ውስጥ እንዳለ ሁሉ የኦፌኮ እንቅስቃሴም በተወሰነ ደረጃ ቀውስ ውስጥ ነው፡፡ ይህን ሕዝቡም የሚያውቀው ነው፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እጅግ የጠበበ በመኾኑ የድርጅታችን በርካታ ጽሕፈት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ የተዘጉት ደግሞ በግልጽ ኃይልና በተጽዕኖ ነው፡፡ የተዘጉት ጽሕፈት ቤቶቻችን ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም፡፡ በጥቅሉ በዞንና በወረዳ ደረጃ ከ200 በላይ የሚኾኑት ተዘግተውብናል፡፡ ለምሳሌ ምዕራብ ወለጋ ላይ ያለው ጽሕፈት ቤታችን በመንግሥት ኃይሎች ተሰብሮ ንብረቶቻችን ተዘርፈውብናል፡፡ በተመሳሳይ በምዕራብ ሀረርጌም ጽሕፈት ቤታችን ተሰብሮ ንብሮቶቻችንን ተሰባብረውብናል፡፡”

አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ

አዲስ ማለዳ ቲዩብ፣ ነሐሴ 27/2016 ዓ.ም

“ስታዲዬሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ እና ለዓላማ እንዲወሉ ማድረግ ዋና ተግባራችን ነው፡፡ የባሕርዳር ስታዲየም የፊፋ ደረጃዎችን በሚያሟላ መልኩ እየተገነባ ነው፡፡ ጥራቱን ጠብቆ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ እቅድ ይዛለች፡፡ ስለዚህ የዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማድረግም ኾነ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲዬሞች ያስፈልጉናል፡፡ ተጀምረው የቆዩ ስታዲዬሞችን ማጠናቀቅ የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ወሳኝ ነው፡፡ በ2017 ዓ.ም በልዩ ትኩረትና ሥራ ውጤት እናመጣለን፡፡ ለሌሎች ስታዲዬሞች ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል፡፡”

ሸዊት ሻንካ፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር

አማራ ቲቪ፣ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም

“አቤል ያለው ጉዳት ላይ መሆኑን መረጃ ልኳል አቡበከር ግን እመጣለሁ ብሎ ባለቀ ሰዓት ነው ጉዳት አለብኝ ብሎ የቀረው እውነት ነው የሚለው መጣራት አለበት ውሸት ከሆነ ግን ለሱ ጥሩ አይሆንም፡፡ በውጪ ሃገር የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ፕሮፌሽናልነት ይዘው ስለሚመጡ ጠንክሮ መስራትን ስለሚያስተምሩ አብረው መዘጋጀታቸው ጥቅሙ የበዛ ነው። የወዳጅነት ጨዋታን ሳናካትት ያደረግነው ጨዋታ አራት ነው፤ ከሜዳ ችግር አንጻር አራቱም ከሜዳ ውጪ የተደረገ ሆኖ ለምን ግብ አይቆጠርም የሚለው ልክ አይደለም፡፡ ይሄ የአጥቂ ችግር የአገሪቱ እግርኳስ ችግር ነው፡፡ ዓለም ላይም አጥቂ ጠፍቷል፤ እኛ ጋር ደግሞ የባሰ ነው፡፡ ለውጡ በአንድ ጀምበር አይመጣም፤ ለለውጥ አመታት ይፈልጋል፤ ለዚህ ነው እንደ ቡድን ማጥቃት ያለብን ” ሲል ተናግሯል”

ገብረመድህን ሃይሌ፣ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ

ሀትሪክ ስፖርት፣ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

“ካሲናዬ ማለት ከትርጉሙ ስንነሳ አልፋና ኦሜጋ ወይም የመጀመሪያየም የመጨረሻየም ማለት ነው፡፡ እኔ በዚያ ሥራ ውስጥ በትዳር ውስጥ ሀገርን ነው የመሰልኩት፡፡ ይህም ማለት ከመለያየት ምንም አናተርፍም፤ በዚያው ልክ አንድ በመኾን የምናጣው ነገር የለም፤ የሚል መልዕክት ያለው ነው፡፡ሥራውን በትዳር አስመስየ ነው የሳልኩት፡፡ የፊልሙ ዋና ታሪክ ሁለት አፍላ ወጣቶች መጋባታቸውና በተጋቡ ዕለትም መጣላታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ሲጣሉም የልጂቱ እናት ትዳሩን ለማትረፍ የሚሄዱበትን ርቀት ያሳያል፡፡”

ብርሃኑ ወርቁ፣ አርቲስት

አሻም ቲቪ፣ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

“አንዲት ታካሚ አስፈላጊው ምርመራ ሁሉ ተደርጎለት የጤናው ችግር ምን እንደሆነና ሕክምናውም በምን ሁኔታ ሊሰጥ እንደሚገባ ከቤተሰቡ ጋር ምክክር ተደረገ፡፡ ቤተሰቦቹ ለህ ክምናው የሚያስፈልጋቸውን ነገር አሟልተው አመሻሹ ላይ መድሀኒት እንዲጀመርና በነጋ ታው ቀዶ ህክምና እንደሚደረግ ተነግሮአቸው ይሄዳሉ፡፡ ቤተሰቦች ታካሚውን ይዘው እንደ ሄዱ ባልታወቀ ምክንያት የተወሰነ ጊዜ ይቆያሉ፡፡ እንደገና ተመልሰው ሲመጡ ሕመሙ የመስፋፋት እድሉ ጨምሮአል፡፡ በዚህ ጊዜ ታካሚዋን የማቆየት እንጂ የማዳን እድሉ ይዳ ከማል፡፡”

ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

“ካሽጎን ስንሠራ ብዙ ገንዘብ አጥፍተንበታል፡፡ አሁን ለካሽጎ የመጣው እድል ነው፡፡ ነገር ግን ትንሽ የሚያሳዝን ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነጋዴ ጫማ ቤት ሲከፍት ጎረቤቱ ሁሉ ጫማ ቤት ይከፍታል፡፡ ጫማ ቤት ሲከፈት ከጎረቤቱ ማሰሪያ የሚያመርት አይደለም የሚከፈተው፡፡ ይህን ተግዳሮት ያለፉትን ሦስት ዓመታት አልፈን ነበር፡፡ ካሽጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በኢትዮጵያ የጀመረው፡፡ ከቪዛ ካርድ ወይም ከክሬዴት ካርድ ወይም ከሌላ ካርድ ላይ ከግዢ ሌላ ሪሚታንስ እንዲካሄድበት ያደረግነው እኛ ነን፡፡ ከዚህ አንጻር የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ካለ ምናልባት መንግሥት ቢመዘግበንና ጥበቃ ቢያደርግ ጥሩ ነበር፡፡”

አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ናሁ ቲቪ፣ ነሐሴ 27/2016 ዓ.ም

“ኢትዮጵያ ውስጥ በመስኖ ማልማት የሚያስችል ትልቅ እድል እያለ አልተጠቀመችበትም። የሚጠበቅብንን ያህል አላመጣነውም። እስከዛሬ የነበረን አመለካከት ከውጭም የሚመጡ አማካሪዎቻችን ጭምር የእኛን ውሃ ለመጠቀም እንዳንችል ከመፈለግ አንጻር የሚመክሩን በአብዛኛው በዝናብ እንድናመርት እንጂ ወደ መስኖ ልማት ስራ ውስጥ እንድንገባ አይደለም። ወይም እዚያ መስመር ውስጥ እንድንገባ አልገፉንም። እኛም መረዳታችንን አስፍተን የመስኖ ልማታችንን የአመለካከት፣ የግንዛቤ አቅጣጫ መቀየር እና ማስተካከያ ስላላደረግን ነው። በአብዛኛው በእኛም ዘንድ ያለው ግንዛቤ ኢትዮጵያ በዝናብ ውሃ መልማት ትችላለች የሚል ነው።”

በለጠ ብርሃኑ (/)

አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

“ለኅብረተሰቡ ጠንቅ ነው የሚባል ወንጀል አለ፡፡ ዳኞች በሕጉ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ወንጀልን ማክበድ ይችላሉ፡፡ ምክንያታቸውን በመጥቀስ ብቻ ለማኅበረሰብ ጠንቅ ነው የሚሉት ወንጀል ሊኖር ይችላል፡፡ የካሚላት የወንጀል ታሪክን ማስታወስ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የወንጀሉ አፈጻጸም ከዚያ ወዲህ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አክፍቶታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉ አፈጻጸም ለሕዝብ እንዳይገለጽ ቢያደርግ ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ወዲህ ነው አሲድ ሴቶች ላይ መድፋት እየተስፋፋ የመጣው፡፡ የማኅበረሰቡን ስሜት የሚያውክ ወንጀል አለ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አራት ኪሎ አካባቢ አህያ አርደው ሥጋ ይሸጣሉ የሚል ክስ ሲሰማ ነበር፡፡ በአሰላ አካባቢም እንዲሁ አህያ አርደው ሥጋ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ ሲባል ሰምተናል፡፡ የአህያ ሥጋ መብላት ለጤና ምንም ዓይነት ጠንቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው መታወክ እጅግ ከባድ ነው፡፡”

አቶ አንዷለም በዕውቀቱ፣ የሕግ ባለሙያ

ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም