ግብጽ እና ሶማሊያ ምን እያሤሩብን ነው?

Date:

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ‹‹በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል›› በማለት ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳን ተከትሎ፣ ሥጋት ላይ የወደቀውን የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የሶማሊያ መንግሥትንም ‹‹ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል›› በማለት በግልጽ ከሷል፡፡ ‹‹ነገርን ከሥሩ፤ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ፣ ለመኾኑ ግብጽ እና ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ ለማሤር ወዳለመ እንዲህ ያለ እንቅስቃሴ ውስጥ ለምን እና እንዴት ገቡ? የሚለውን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡

ጃንዋሪ 1 ቀን 2024 በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ ላለፉት ሰባት ወራት በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል የተፈጠረው መቃቃር፣ በምሥራቅ አፍሪቃ እና የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ላይ አዳዲስ ትኩሳቶች ወልዷል ፤ ቀድሞ የነበሩ የኃይል አሰላለፎችን ሳይቀር አዛብቷል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በአካሔድ እና በዲፕሎማሲ ረገድ የታዩት ሽንቁሮች፣ ‹‹መንግሥት›› ኾኖ መቆም ሰማይን የመቧጠጥ ያህል ፈተና ኾኖባት ለቆየችው ሶማሊያ አንዳንድ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች እንድታስመዘግብና ኢትዮጵያንም ጠብ አጫሪ አስመስላ ዓለም ፊት ገጽታዋን ለማወየብ የቻለችውን እንድታደርግ በር የከፈተ ነበር፡፡

ያም ኾኖ ባለፉት ሁለት ወራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኳ ዋና ከተማ አንካራ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ተፈጥሮ በማያውቅ መጠን በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ይረዳል የተባለ ውይይት ቢያደርጉም ሊሳካ አልቻለም፡፡

ሶማሊያ ባለፉት ሰባት ወራት ኢትዮጵያ ‹‹ሉዓላዊነቴን ደፍራለች ፤ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነትም ግዛቴን በኃይል የመያዝ ሙከራ ነው›› በማለት በፕሬዝዳንቷ ሐሰን ሼህ መሐመድ በኩል በዐደባባይ ክስ ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ የምታነሣውን የባሕር በር ጥያቄ አስመልክቶም፣ አልጀዚራ ላይ አስተያየቱን አስፍሮ የነበረው የቀድሞ የሶማሊያ ፕላኒንግ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዲ አይንቴ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ኤርትራ ከጉያዋ ስትነጠል እንድታጣ በተደረገችው የባሕር በር ምክንያት ከሠላሣ ዓመታት በኋላ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ተጥሶ ካሣ የምታገኝበት አግባብ ሊኖር አይችልም›› በማለት እስከ መከራከር ደርሶ እንደነበርም አይረሳም፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሐሰን ሼክ መሐመድ ደግሞ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የመግባቢያ ውል ከቀደደች፣ የባሕር ተደራሽ በምትኾንበት አግባብ ዙርያ መነጋገር ይቻላል›› በማለት ቅድመ ኹኔታቸውን ግልጽ አድርገው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስምምነቱን ለመቅደድ ከመድፈር ይልቅ ከሶማሊያ ጋር ተነጋገሮ እልባት ለመሥጠት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ኾኖም በሞቃዲሾ በኩል የታየው መልስ በዚያው የመግባቢያ ስምምነቱ በማፍረስ ቅድመ ሁኔታ ላይ የጸና መኾኑን ተከትሎ፣ ከአራት ወር በፊት፣ ‹‹ብሉምበርግ›› የተባለው የዜና አውታር ለጉዳዩ ቅርብ ከኾኑ ምንጮች አገኘሁት ያለውን መረጃ ተንተርሶ፣ ኢትዮጵያ ለሱማሌ ላንድ እውቅና ሰጥታ የወደብ ኪራይ ለማግኘት የገባችውን ስምምነት ለመተው ማሰቧን ዘግቦ ነበር፡፡ በተለይም ናይሮቢ ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ጋር አድርገውት በነበረው ውይይት፣ ከሶማሊያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት፣ ከሶማሊላንድ ጋር በተደረሰው ስምምነት ውስጥ አወዛጋቢ ተደርገው የተወሰዱትን ነጥቦች ለመተው ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጾ የነበረው ዘገባው፣ ከእነኚህ አወዛጋቢ ከተባሉ ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛውም ‹‹ለሶማሊላንድ ዕውቅና መሥጠት›› የሚለው እንደኾነ በወቅቱ አትቶ ነበር፡፡

ዘገባው ይኽን ይበል እንጂ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ መካከል የታየው ግንኙነት በማደግ እንጂ በመቀዝቀዝ ስለሔዱ የታዩ ምልክቶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ በሜይ 18 ቀን 2024፣ ሶማሊላንድ ሠላሳ ሦስተኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ስታከብር፣ በቅርቡ የሀገርነት ዕውቅና ከኢትዮጵያ እንደምታገኝ ተስፋ ሰጪ የሚመስል መልዕክት ለሕዝቧ ማሻገሯ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በወቅቱ በጀርመን ድምጽ ራዲዮ (ዶቸቨሌ) በኩል ተሰርቶ የነበረ ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የሶማሊንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሱበትን የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ወደ ወደ መጨረሻ ስምምነትም ኾነ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የቴክኒክ ቡድን እስከማዋቀር ደርሰዋል። የቴክኒክ ቡድኑም የመጨረሻው ስምምነት ላይ ለመድረስ ‹‹ልዩ ዓለም አቀፍ የሕግ ኩባንያዎች እና የሶማሊላንድ የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት የሶማሊላንድን አቋም የተመለከተ ሰነድ ማዘጋጀት ጀምሯል›› ሲል አንድ ለመንግሥት ቅርበት ያለውን ምንጭ ዋቢ አድርጎ ጣቢያው ዘገባውን አስደምጦ ነበር።

በተጨማሪም ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ለምትፈልገው ወታደራዊ የጦር ሰፈር፣ በሊዝ ልትከራይ የምትችላቸውን ሦስት ቦታዎች ለይታ ማጠናቀቋም፣ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ ይፋ የኾነ ዜና ሲኾን፣ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ‹‹የነዚህን ሦስት ቦታዎች ስም በይፋ መግለጽ ነውር ባይሆንብንም፣ ጉዳዩ ግን ከኢትዮጵያ አቻችን ጋር በጋራ የምንወስነው በመኾኑ አሁን ላይ ይፋ አናደርግም›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር አያይዘው ታዲያ አንድ ሌላ ሐሳብም ተናግረዋል፡፡ ይኸውም ‹‹የመጨረሻውን ስምምነት እንደተፈራረምን እና ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን በምታሰፍርበት የጦር ሰፈር እና ተያያዥ በኾኑ ጉዳዮች መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ፣ በፍጥነት ውሣኔዋን በፓርላማዋ አጽድቃ ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ትሰጣለች፡፡ ምናልባትም በመጪዎቹ ሁለት እና ሦስት ወራት እነኚህ ጉዳዮች ይቋጫሉ ብዬ አስባለሁ›› ማለታቸው ነው፡፡

እንግዲህ እንዲህ ካሉ ዜናዎች መሠማት እና መራገብ በኋላ፣ ይፋዊም ባይኾን ውስጥ ለውጥ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቶች መታየት ጀምረዋል ሊባል ይችላል፡፡ በርግጥ የቅርቡን የአንካራ የእንነጋገር ጥሪ ያቀረበችውም ኾነ ጥያቄውን ይዛ ቱርክን የተማጸነችው ኢትዮጵያ መኾኗ በራሱ ለተለያየ ትንታኔ ክፍት ነው፡፡ በአንድ በኩል ቱርክ በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር መላውን የሀገሪቱ የባሕር ጠረፍ ለመጠበቅ ስምምነት ላይ ከመድረሷ አንጻር፣ ገላጋይ ከምትኾንበት ይልቅ ለሶማሊያ አድሎአዊ የምትኾንበት ዕድል ይሠፋል በማለት ‹‹የኢትዮጵያ አካሔድ አማራጭ ከማጣት የመነጨ እጅ የመሥጠት ምልክት ነው›› በማለት የተናገሩ ወገኖች አልጠፉም ነበር፡፡

እንዲህም ኾኖ ግን ሶማሊያ ነገሮችን ቀድሞ በነበራት ሞገደኝነት ከመቀጠል ይልቅ፣ ኢትዮጵያ ‹‹የባሕር መተንፈሻ ያስፈልገኛል›› የሚለው የከረረ አቋሟ መሠረት ያደረጋቸውን ተጨባጭ አመክንዮዎች ተረድቶ ‹‹አሸናፊ›› የሚያደርግ መፍትሔን ለመፈለግ የተስማማች መሥላ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቷ ሐሰን ሼህ መሐመድ በኋላ ላይ ሌላ መልክ ሊሰጡት ቢወድዱም፣ ሞቃዲሾ ቱርክ ላይ ለተደረገው ውይይት ይሁንታዋን ሰጥታ ወደ አንካራ ስታቀና፣ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ካቋረጠች በጋልሙድ ግዛት የሚገኘውን የሆብዮ ወደብን እንድትጠቀም እፈቅዳለሁ ከሚል አቋም ጋር ነው የሚለው ዜና መሠራጨቱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

እዚህ ጋር ታዲያ ‹‹ኢትዮጵያ ዕውቅና ሰጥታን 55ኛዋ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገር እንኾናለን›› ለሚሉት እንደ ሶማሌላንዱ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ላሉት የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ ከባሕር በር መተንፈሻ ጋር ተያይዞ የምታነሣውን ችግር በሶማሊያ በኩል ለመፍታት ወደሚያስችል እንዲህ ወዳለ አካሔድ መመለሷ በጎ ስሜት ይሠጣል ተብሎ አይታመንም፡፡ ነገሮችም ቢኾኑ በነበሩበት መቀጠላቸው ኢትዮጵያ አካሔዷን ላለመከለሷ ማሳያ ነው፡፡

ባለፉት ወራት ረጅም ታሪክ ባላቸው ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪቃ ጎረቤት ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የቆየው ውጥረት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳሳቢ የደህንነት ችግር ኾኖ መቆየቱን ተከትሎ፣ ጉዳዩ በዛ መንገድ መታሰቡም ኾነ እንዲያ ያለ ቅኝት እንዲይዝ መደረጉ ‹‹አግባብም ፤ ምክንያታዊም አልነበረም›› ለሚሉት መቀመጫውን ሃርጌሳ ያደረገው የሰላም እና ልማት አካዳሚ ዳይሬክተር ሞሃመድ ፋራህ አስተያየት፣ ‹‹በአንድ ወገን ሶማሊላንድ የዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና የመጠየቅም ኾነ የማግኘት መብት አላት፡፡ ኢትዮጵያም ደግሞ በሌላ ወገን ጥይት ሳትተኩስ ለሶማሌላንድ እውቅና የመስጠትም ኾነ የመንፈግ ሉዓላዊ መብቷ ኾኖ ሳለ ጉዳዩ ከጦርነት ዲቤ ጋር ተሰናስሎ መቀንቀኑ አግባብነት የለውም›› ሲሉ ይገኛሉ።

‹‹የሶማሌላንድ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ሕዝቡን፣ ፓርላማውን ብሎም ይኽ የመግባቢያ ሰነድም ኾነ ይኽን ተከትሎ የሚካሄደው ቀጣይ ስምምነት የሀገሪቱን ጥቅም እንደሚያስከብር ማሳመን ከቻለ፣ ሒደቱን የሚያኮላሽ እና ለቀጣናውም ደህንነት እንቅፋት የሚኾን አደጋ አይታየኝም›› ሲሉ ደግሞ መቀመጫውን በሶማሌላንድ ያደረገው የባርዋኮ የፖለቲካ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ሙባሪክ አብዱላሂም እንዲሁ ተናግረው ነበር።

ሶማሌላንዳውያን በዚህ መጠን ነገሩን ሕግን መሠረት አድርገው ብቻ ከዋናዋ ሶማሊያ ተነጥሎ ሀገር የመኾኑን እርምጃ ማሳለጥ ይቻላል ቢሉም፣ ጉዳዩ ግን እነሱ ባሰቡት ልክ ቀላል የማይኾንበት በርካታ ውስብስብ ቀጣናዊ ምክንያት መኖሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ከእነዚህ አካባቢያዊ ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛ ተደርጎ በበርካታ የነገሩ ታዛቢዎችም ኾነ በራሷ በሶማሊያ ባለሥልጣናት በኩል የሚጠቀሰው ደግሞ፣ ብዙ የተደከመለት የሶማሊያም ኾነ የአካባቢው ሰላም በአልሸባብ የመታወኩ እና በቁጥጥሩ ሥር የመግባት ዕድሉ ሊጨምር ይችላል፣ ይኽም የቀጣናውን ሁኔታ የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል የሚለው ሥጋት ነው።

በርግጥም በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ያለው ግንኙነት ከመካከረር እስከ ወዲያኛው መቋረጥ የሚያመራ ከኾነ፣ ለአካባቢው ሕልውና ‹‹አደገኛ ነው›› ተብሎ ታምኖበት የኖረውን አልሸባብ በመዋጋት ረገድ የነበረ የሀገራቱ የቅርብ ትብብር አደጋ ላይ ሊጥል መቻሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። አደጋው ደግሞ በሁለቱም ሀገራት በኩል ቢታይ ከባድ ፈተናን የሚጋርጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ያሰማራቻቸውን ወታደሮቿን ለፍላጎቷ ማስፈጸማያነት መደራደሪያ አድርጋ ብትጠቀማቸውም ኾነ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ምድሬን ለቅቀው ይውጡ ብትል፣ ሰርግና ምላሽ የሚኾንለት ሌላ ማንም ሳይኾን አልሸባብና አልሸባብ ብቻ ነው፡፡ የአልሸባብ ታጣቂዎች ደግሞ ቂማቸውም ኾነ የበቀል ፍላጻቸው በሶማሊያ ላይ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን በኢትዮጵያና በሌሎችም የአካባቢው ሀገራት ላይ ጭምር ትልቅ አደጋ በማድረስ የሚወራረድ ከመኾኑ አንጻር፣ ቱርክም ኾነች የተቀረው ዓለም ሀገራቱ በንግግር ችግራቸውን እንዲፈቱ ቢረባረብ የሚደንቅ አይኾንም።

የአልሸባብ ተጽዕኖ ደግሞ በዚህ ብቻ የሚገለጽ ላይኾን ይችላል፡፡ ታጣቂው ኃይል አልፎ ተርፎ በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ ‹‹ተጋረጠ›› የተባለውን ይኽን አደጋ፣ ለሶማሊያ ብሔርተኝነት መጋቢ በሚኾን መንገድ አስፍቶ ሊጠቀምበት ይችላል። የሶማሊያን ፌዴራላዊ መንግሥትን፣ የሶማሊያን የግዛት አንድነት መሸርሸር ከሚፈልጉ ውጫዊ ኃይሎች ሀገሩን የማስጣል ዐቅሙ እጅግ የደከመ አድርጎ በመሣል፣ ራሱን ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ ያላትን ‹‹የተስፋፊነት ምኞት›› መግታት የሚችል ብቸኛ ኃይል አድርጎ ሊያሳይ ይችላል። ይኼ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ያከናወናቸውን ትግሎች ሁሉ ለሶማሊያውያን ሕልውና የተደረጉ መኾናቸውን ማመሳከሪያ አድርጎ በማቅረብ፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያኑ 2006 አንስቶ ሶማሊያ ውስጥ ጦሯን በማዝመት ሞቃዲሾ ላይ ሥልጣኑን እንዲቆናጠጥ ድጋፍ ያደረገችለትን ቡድን ማስወገድ ምን ያህል ፍትሓዊ ጥያቄ እንደኾነ ለማሳመን ሊጠቀምበት ይሞክራል፡፡ አልሸባብ በርግጥም አንዳንዶቹን ጉዳዮች ማቀንቀን ከጀመረም ዋል አደር ብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ገና በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነቱ ተፈርሞ ቀለሙ ሳይደርቅ የሞቃዲሾው ፕሬዝዳንት ‹‹ብዙ ወጣቶች አልሸባብን እየተቀላቀሉ ነው›› የሚል ፕሮፓጋንዳ በዐደባባይ መጠቀማቸው ጠቅሞታል ሊባል ይችላል፡፡  

***

ሶማሊያ ግን በዚህ ብቻ ሳትገደብ፣ ቀደም ብለን የጠቀስነውን ለሁለቱም ሀገራት አደጋነቱ ይከፋል ያስባለውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከምድሯ የማስወጣቱን ጥያቄ በድፍረት ወደፊት ይዛው መጥታለች፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሼክ-አሊ፣ ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር ለሰላም ማስከበር ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች እስከ መጪው ዲሴምበር 2024 መጨረሻ ድረስ ከሀገሪቱ ተጠራርገው እንዲወጡ ትጠብቃለች ብለዋል። የደህንነት አማካሪው በዚህ በሀገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ባሰራጩት መልዕክት፣ ከመጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አንስቶ ለአንድ ዓመት የሶማሊያን ቁልፍ ተቋማት በሚጠብቁት የአፍሪካ ሕብረትና ዓለም አቀፍ አጋራት ሰራዊቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲኖሩ አንፈልግም ሲሉም ጨምረው ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሶማሌያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ያሏት ሲኾን፣ አብዛኞቹም ለሶማሌላንድ አዋሳኝ ከኾኑ አካባቢዎች በራቀ መልኩ መቀመጫቸውን ደቡብ ምዕራብ፣ ጁባላንድ እና ሂርሻቤሌ በተባሉት ሦስቱ የሶማሊያ ግዛቶች ያደረጉ ናቸው። ከእነዚህ ወታደሮች መካከል ጥቂቶቹ የ‹‹አፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ›› ሰራዊት አካል ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሲኾን ቀሪ ሌሎች የኢትዮጵያ ወታደሮች ደግሞ በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ የደህንነት ስምምነቶች ምክንያት ሶማሊያ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙ ናቸው።

ኾኖም ቀደም ብለን የጠቀስነውን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ሁሴን ሼህ አሊ መግለጫን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሰፈሩባቸው ግዛቶች መካከል አንዷ የኾነችው ጁባላንድ ግዛት፣ ባለሥልጣናት ያንን የሞቃዲሾ መንግሥት መግለጫ እንደማይቀበሉ እና እንዳሳዘናቸውም ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም። ይኽንንም የጁባላንድ ምክትል ፕሬዝደንት መሀሙድ ሳይድ ኤደን ‹‹እንዲህ ከተደረገ በብቸኝኘት ተጠቃሚው ‹ካራዋሪጅ› ብቻ ነው›› ሲሉ ሞቃዲሾ የአልሸባብ ታጣቂዎችን በምትጠራበት ሥም ተጠቅመው እንዲህ ያለው የሶማሊያ መንግሥት ውሣኔ ኢ-ምክንያታዊነትን አስረድተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት የጸጥታ ሚኒስትር ሀሰን አብዱልቃድር መሀመድም እንዲሁ ‹‹እኔም ኾንኩ የደቡብ ምዕራብ አስተዳደር ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ወታደሮች በግዛታችን መኖር ደስተኞች ነን›› በማለት ምላሽ የሰጡ ሲኾን፣ ‹‹በሶማሊያ ያለው የአፍሪቃ የሽግግር ተልዕኮ ጦር፣ ከአገሪቱ እንዲወጣ ከተፈለገ የጋራ የኾነ ውይይት መካሔድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ የትኛውም አንድ አካል በግሉ ተነስቶ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም›› በማለት የሞቃዲሾ መንግሥት አካሔድ ሌላው ቀርቶ የማዕከላዊ መንግሥቱን የበላይነት ተቀብለው እንደ ግዛት በሥሩ ባሉት አስተዳደሮች ሳይቀር ይኹንታ የተነፈገው መኾኑን አረጋግጠዋል፡፡ 

እንዲህ ያለው በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዙርያ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሀገሪቱ ይውጣ አይውጣ ውዝግብ ዙርያ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዐይነት አስተያየት ሳይሰጥ የቆየ ቢኾንም፣ አንዳንድ የጉዳዩ ታዛቢዎች ግን፣ ሞቃዲሾ የያዘችው አቋም ‹‹ለሶማሊያም ኾነ ለአፍሪካ ሕብረት ፈተናዎችን ይጋብዛል›› በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ለአብነት እንኳን ታዋቂዋ የአፍሪካ ቀንድ የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሳሚራ ጋይድ ‹‹እንዲህ ያለው የሶማሊያ መንግሥት ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረት የተባለውን እርምጃ እንዲወስድ በይፋ ተነግሮት የተገለጸ ስለመኾኑ እርግጠኛ አይደለሁም›› ካለች በኋላ፣ የሞቃዲሾ እና የአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት ‹‹በተባለው ጊዜው ውስጥ ተተኪ ኃይሎችን ለማዘጋጀት ጊዜ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ አይመሥሉኝም›› ብላለች።

ጋይድ አያይዛም በሶማሊያ ሕገ መንግሥት የብሔራዊ ደህንነት እና መከላከያ ኃይሎች በፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን እና ኃላፊነት ሥር ያሉ ከመኾናቸው አኳያ፣ የፌደራሉ መንግሥት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንገተኛ በኾነ መልኩ ከሀገራችን ይውጡ የሚለውን ውሣኔያቸው ተከትሎ፣ ሊከተል የሚችለውን ጉዳትም ኾነ ክፍተት እንዴት ሊሞሉት እንዳሰቡም ቢኾን ግራ አጋቢ ነው በማለት እንዳልተዋጠላት አስተያየቷን ሰንዝራ ነበር፡፡

እንግዲህ ይኽ ከኾነ ክጥቂት ወራት በኋላ ነው ሶማሊያ የግብጽ ጦር ሀገሪቱ ውስጥ እንዲሰፍር  ይኹንታዋን የሰጠችው፡፡ ይኽን ተከትሎም ግብጽ በሁለት የጦር አውሮፕላኖች የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር የነበሩት ውጥረቶቹ ሊካረሩ ችለዋል። ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ እንደጣላት በመግለጽ፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች። የሶማሊያ መንግሥትንም ‹‹ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል›› ስትል ከሳለች።

የአፍሪካ ሕብረት እና የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከሁለት ወር በፊት፣ 2,000 ያህል የሚኾኑ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ሀገሪቱን እንደሚለቁ ያረጋገጡ ሲሆን ተጨማሪ 2,000 ወታደሮች ደግሞ በያዝነው ሴፕቴምበር ወር መጨረሻ ከሀገሪቱ እንደቀነሱ አስታውቀዋል። ይህም ሶማሊያ ውስጥ የሚቀሩት የአፍሪቃ ሕብረት ወታደሮችን ቁጥር ወደ 9,500 ዝቅ የሚያደርገው ሲሆን፣ እንደ ሶማሊያ መንግሥት መግለጫ ከኾነ ግን፣ እነኚህ ቀሪ ወታደሮች በመጪው ጃንዋሪ 2025 በሚጀመረው አዲሱ ተልዕኮ አካል ኾነው ይቀጥላሉ።

ቪኦኤ ከሦስት ወር በፊት በጉዳዩ ዙርያ ውይይቶች መቀጠላቸውን ጠቅሶ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአፍሪካ ሕብረት ባለስልጣን ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ደግሞ፣ በአዲሱ ተልዕኮ የሚኖረው የሰራዊቱ ቁጥር እስከ 12,000 ሊደርስ የሚችል ሲኾን፣ ሶማሊያ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ የዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ ወታደሮች እንዲካተቱ ጥያቄ ማቅረቧን፣ የኢትዮጵያን ሰራዊት ግን ማየት እንደማትፈልግ መግለጽዋን አስነብቧል።

ኾኖም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ግብጽ ለማሰማራት ዕቅድ መያዟ ከሰሞኑን ይፋ ከኾኑት ዜናዎች መካከል አንዱ ኾኗል። ይኽ በርግጥም በአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካዊ ትኩሣት ላይ የሚኖረው ትርጉም ቀላል አይኾንም፡፡ እንዴት የሚለውን በሌላ ጊዜ የምንመለስበት ይኾናል፡፡  

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...