አዳም ረታ ሥራዎቹን ለአንባቢ ማድረስ የጀመረው ከ1970ዎቹ አንስቶ ነው። የአጫጭር ልብ ወለዶች፣ ግጥሞች እና የረዥም ልብ ወለድ ደራሲ የሆነው አዳም የመጀመሪያ ሥራው በ1977 ዓ.ም. በታተመው “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” መጽሐፍ ውስጥ ነው።
የደራሲው የመጀመሪያ ወጥ የአጭር ልብወለድ መጽሐፍ የሆነው “ማሕሌት” በ1981 ዓ.ም. ታትሟል። በአጠቃላይ፤ አዳም ረታ ስድስት የአጫጭር ልብ ወለድ እና አራት የረዥም ልብ ወለድ መፃሕፍትን አሳትሟል።
“ጭጋግ እና ጠል”፣ “አማሌሌ”፣ “መልክዓ ስብሐት” እና “Addis Ababa Noir” የተባሉ መድበሎች ውስጥም ትረካዎችና ሂሳዊ ዳሰሳዎችን አቅርቧል።
አዳም ረታ ብቻውን እንዲሁም ከሌሎች ደራሲያን ጋር በመሆን በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ካሳተማቸው ጋር በአጠቃላይ አስራ ሦስት መጽሐፍትን ለአንባቢዎች ያደረሰ ሲሆን አስራ አራተኛውን ደግሞ አሁን ለንባብ አብቅቷል።
የአዳም ረታ አዲሱ ‘መዝሙረ ሄላም’ የተሰኘው የረዥም ልብ ወለድ መጽሐፍ 1,008 ገጾች ሲኖሩት በአምስት ክፍሎች የተከፈለ ነው። ይህ የአዳም አዲስ መጽሐፍ ከዚህ ቀደም የሚጠቀማቸው እንደ ሕፅናዊነት ያሉ ሥነጽሑፋዊ ቴክኒኮች የያዘ መሆኑን በመጽሐፉ አርትኦት ላይ የተሳተፈው ቢኒያም አቡራ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የመጽሐፉ መቼት ከዚህ ቀደም እንደነበሩ የደራሲው ሥራዎች ከ1950ዎቹ ማለቂያ እስከ 70ዎቹ መጨረሻ ያሉ ናቸው።
መጽሐፉ መጠሪያ የሆነችው ሄላም ከዋና ገጸባሕሪያቱ አንዷ ስትሆን በሁሉም ክፍል ውስጥ ትገኛለች። ለሕፅናዊነት አጻጻፉ ኹነኛ ማስተሳሰሪያ በመሆን ታገለግላለች። ቢቢሲ ከአርታኢው ቢኒያም ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ. . .
ቢቢሲ አማርኛ- የአዳም ሥራ እንዲሁም አዳም ግዙፍ ስም ነው ያላቸው። በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢ ከማቅረብ ባሻገር በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ላይም የራሱን አሻራ ያኖረ ነው። አንተ የእርሱን ሥራ አርትኦት አንድትሠራ ሲሰጥህ መጀመሪያ የተሰማህ ስሜት ምንድን ነበር?
ቢኒያም አቡራ፦ መጀመሪያ በማኅበራዊ ሚዲያ ትውውቅ ብቻ ነው የነበረን። ከዚያ በአካል ስንገናኝ መጀመሪያ በጣም ልዩ የሆነ ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ቁጭ ብሎ የማውራት ዕድል እና ጊዜ ነበረን። በዚያን ወቅት የሚጠይቀኝ አንዳንድ ጥያቄዎች ነበሩ።
ምን ዓይነት ‘ስኩል ኦፍ ቶውት’ እንደምወድ፣ የሥነ ጽሑፍ ቲዎሪ ላይ ያለኝን ግንዛቤ ይጠይቀኝ ነበር። እነዚያ ጥያቄዎች ግን ለአርትኦት ብቁ ነው አይደለም የሚለውን ለመመዘን ፈልጎ መሆኑን ግንዛቤ አልወሰድኩም ነበር። እንደ ጨዋታ ነበር ያሰብኳቸው።
ኋላ ላይ ግን ለአርትኦት እንዳሰበኝ እና መጽሐፉን ሲሰጠኝ በጣም ልዩ የሆነ ስሜት ነው የተሰማኝ። ምክንያቱም ከእኔ ጋር ያለው የዕድሜ፣ የልምድ፣ የእውቀት ልዩነት በጣም ሰፊ ስለሆነ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ለራሳቸው ካላቸው ግምት አንጻር እንደዚህ ለታናናሾቻቸው ዕድል እና ጊዜን ስለማይሰጡ፣ ያንን ዕድል አገኛለሁ ብዬ ስላላሰብኩኝ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነበር።
በዚያ ውስጥ ትህትናውን ታያለህ። ከታናናሽ ለመማር ማሰቡ ብቻ ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ወይንም ደግሞ በታናናሾችህ ለመታረም ዝግጁ መሆን የአንተን ትልቅነት ነወ የሚያሳያው። ስለዚህ በጣም ነበር ደስተኛ የሆንኩት።
ቢቢሲ አማርኛ- የአዳምን አዲስ ሥራ ‘መዝሙረ ሄላም’ን እንድታነብ እና አርትኦት እንድትሠራ መመረጥህን ስታውቅ ድንጋጤ ነበረው? ይኼ ነገር ኧረ ለእኔ ከባድ ነው ብለህ ነበር?
ቢኒያም አቡራ፦ አዎ፤ ምክንያቱም እርሱ ያለው ስም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ እንደዚያ ዓይነት ነገር ላያድርብህ አይችልም። በተለይ ደግሞ በእኔ ዕድሜ፣ በእኔ ልምድ፣ በእኔ የእውቀት ደረጃ ላይ ስትሆን ለእዚህ ነገር ብቁ ነኝ የሚል ጥያቄ በውስጥህ ይኖራል። ግን ያ ሰው የመረጠህ፣ ያመነብህ፣ በሆኑ በሆኑ መመዘኛዎች እንደሆነ ታስብና የበለጠ ደስታ ይሰማሃል። ስለዚህ መጀመሪያ ላይ እንዳልከው እንደዚያ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኛል።
ቢቢሲ አማርኛ- በአርትኦቱ ላይ አንተ ብቻ ነህ የተሳተፍከው ወይስ ሌሎችም አሉ?
ቢኒያም አቡራ- መጽሐፉ ከወጣ በኋላ በአርትኦት የተሳተፉ ሰዎች ስም ዝርዝር አለ። ስለዚህ እኔ ብቻ አይደለሁም። መጀመሪያ ግን አላውቅም ነበር ። ሌሎች ሰዎች በአርትኦት እንደተሳተፉ ብዙም መረጃው አልነበረኝም። መጽሐፉ ሲወጣ ግን እኔ ብቻ አለመሆኔን አውቅያለሁ።
ቢቢሲ አማርኛ- አርትኦቱን ከሠራህለት በኋላ በሰጣሃቸው አስተያቶች፣ ቢስተካከሉ ባልካቸው ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዕድል አግኝተህ ነበር።
ቢኒያም አቡራ- አርትኦቱን ጨርሼ ከሰጠሁት በኋላ እርሱ ኢትዮጵያ አልነበረም። ስለዚህ አርትኦት የተሠራውን ጽሑፉን ከሰጠሁት በኋላ ንግግር የነበረን በጽሑፍ ነው። በወቅቱ እኔ ጥሩ ሁኔታ ውስጥ አልነበርኩም።
ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩኝ። ልክ ጨርሼ ለእርሱ ከላኩ በኋላ በሕይወቴ የሆነ ነገር ተከስቶ ስለነበር እኔ ሃሳቦቼን በጽሑፍ ላኩኝ እንጂ ከዚያ በኋላ በሥራው ላይ ቁጭ ብሎ የመነጋገር ዕድሉ አልነበረኝም። ተደዋውለን ነበር።
ግን መገናኘት አልቻልንም። ብዙ ጊዜ ለመገናኘት ሙከራ አድርገን ነበር በዚያ ወቅት። እኔ ግን በግል ጉዳይ የተነሳ በሰዓቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ ስላልነበርኩኝ መገናኘት አልቻልንም ነበር።
ቢቢሲ አማርኛ- በጽሑፍ የነበራችሁ ግንኙነት ላይ የእርሱ ስሜት ምን ነበር?
ቢኒያም አቡራ- በጽሑፍ የመጽሐፉ ‘ሰመሪ’፣ አንዳንድ መሻሻል ያለባቸው፣ አስተያየቶች፣ ሃሳቦች፣ መጽሐፉ ላይ ያለውን ነገር እዚያው እያሰመርኩ እንደሠራሁት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሥራዎችም ነበሩት።
እና እንደ ሪቪው፣ እንደ ሰመሪ፣ እንደ አንዳንድ ጥቆማዎች ብዙ ገጽ ነበር። እርሱን ካነበበ በኋላ የነበረው ዕቅዳችን በዚያ ጉዳይ ላይ በስልክ በደንብ ማውራት ነበር። ነገር ግን እኔ ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ያንን ማድረግ አልቻልንም።
ቢቢሲ አማርኛ- አዳም በርካታ መጽሐፍቶችን ለንባብ አብቅቷል። በእነዚያ መጽሐፍቶቹ ላይ አርትኦት ስለማሠራቱ የሚገልጽ ነገር አላገኘሁም። አርትኦት ሲያሰራ ይህ የመጀመሪያው ነው?
ቢኒያም አቡራ- ይህንን ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቸግረኛል። አላሠራም ለማለትም፤ አሠርቷል ለማለትም ይቸግረኛል። ግን አንድ የማስታውሰው የሸገር ቃለ መጠይቅ ላይ አለማየሁ ገላጋይ፣ መዓዛ ብሩ እና እርሱ በጋራ በነበራቸው ቆይታ አንደኛውን ታሪክ በአራት ወይንም በሦስት በኩል እንዲያልቅ ያደረከው ለምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ አንድ ግለሰብ፣ አርትኦት የሠራለት ይሁን አይሁን አላውቅም፣ የሰጠውን አስተያየት ካዳመጠ በኋላ አዳም ያ አስተያየት አልተስማማውም ነበር።
በዚያ ምክንያት ያንን ማድረጉን ሲናገር ሰምቻለሁ። ካልተሳሳትኩ ‘አለንጋና ምስር’ ላይ ያለ ታሪክ ይመስለኛል። ይህንን መነሻ አድርገን የምንናገር ከሆነ ምናልባት አርትኦት አሠርቶ ሊያውቅ ይችላል ልንል እንችላለን።
ግን አንዳንድ መጽሐፍቶቹ ከመታታማቸው በፊት ለሰዎች አስነብቦ ያውቃል። ለምሳሌ አፍን አርትኦት ያሠራ አያሠራ እርግጠኛ ባልሆንም ከመታታሙ በፊት ያነበበ ቢያንስ አንድ ሰው እንዳለ አውቃለሁ።
ቢቢሲ አማርኛ- የአዳም የመጨረሻ ሥራ አፍ ነበር። ከስምንት ዓመት በኋላ ነው መዝሙረ ሄላምን ለአንባቢዎቹ ያበረከተው። አዳም በሥራዎቹ ውስጥ ሁሉ የራሱን መልክ እና ልክ እየሠራ የመጣ ደራሲ ነው። በሥራዎቹም አዳዲስ ነገርን ያስተዋወቀ ነው። አንተ አዲሱ ሥራን ማንበብ ብቻ ሳይሆን አርትኦትም ላይ እንደመሳተፍህ ምን ይዟል ትላለህ?
ቢኒያም አቡራ- አዳም የስንብት ቀለማትን ያክል ትልቅ መጽሐፍ ከሰጠን በኋላ ሌላ ከዚያ የሚበልጥ ወይንም ከዚያ ጋር የሚስተካከል ሥራ መጻፉ፣ ጽፌ አልጨረስኩም ብሎ ማሰቡ አንድ ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ውስጡ በጣም ብዙ አዳዲስ ነገሮች ማኖሩ ደግሞ ይገርማል።
የስንበት ቀለማት 940 ገጽ ነው። አሁን ከሚወጡ ሌሎች ሥራዎች አንጻር ብናሰላው አስር መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ማለት ነው። ያንን ያህል ከጻፈ በኋላ ሌላ የምጽፈው አለ ብሎ ማሰብ እና መነሳት በራሱ ትልቅ ነገር ነው።
እዚህኛው መጽሐፉ ላይ ከስልት፣ ከመዋቅር አንጻር በጣም አዳዲስ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ‘አውቶፊክሽን’ በ’ፊክሽን’ ውስጥ ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል እናያለን። በመጽሐፉ ውስጥ አሮን የሚባል ገጸባህሪ አለ። አሮንን በመጠቀም በ’ፊክሽን’ ውስጥ ‘አውቶ ፊክሽንን’ ሲሞክር ትመለከታለህ።
በመዝሙረ ሄላም፣ ሄላም የምትባለው ገጸባህሪ በአንድ ምዕራፍ ውስጥ ራሷ የምትተርከው ክፍል ላይ እርሷን ከአርታዒ ጋር አብራ እንድትጽፍ ያደርጋታል። የአርታዒውንም ቃላቶች ያስገባል። አርታዒው ይህንን አውጪ ብሎኝ ነበር እያለች ነው የምትተርከው። እና የአርታዒ እና የደራሲ ትስስር በልብ ወለድ ውስጥ የሞከረበት መንገድ አለ። ይህ አዲስ ነገር ነው።
ከይዘት አንጻር ኢትዮጵያ ከምትገባባቸው የተለያዩ ማጦች የምትወጣባቸው መንገዶችን ወይንም ደግሞ ካለችበት ሕመም ውስጥ የመዳኛ መንገዱን ይጠቁማል። ይህም አዳም ጋር ምን ያህል ብዙ አማራጮች እንዳሉ ማሳያ ነው።
በተለይ በመዝሙረ ሄላም ውስጥ የምትገኘው ሄላም የምትባለው ገጸባህሪ ብዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን የምንቀርፍባቸውን የምናገኝባት ገጻባህሪ ናት። የአዳም የመዳኛ መንገዶች ወይንም ደግሞ አገራችን ካለባት ደዌ የምትፈወስበትን መድሃኒቶች ብዛታቸውን በደንብ ያሳየናል። ከይዘት አንጻር ማለት ነው።
እነዚያ ደግሞ የሚያሳይህ መንገዶች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውስጥ ለየት ያሉ አዳዲስ የሚባሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ነው የሚያመጣው። እና እየሄድንበት ያለነው መንገድ ስሁት መሆኑን እግረ መንገድ ይጠቁመናል። እነዚህ እነዚህ ነገሮች አዳዲስ ናቸው።
ሌላው የተለያዩ ገጸባህሪያትን ከዚህ በፊት ከነበሩት መጻሕፍት ወደዚህኛው መጽሐፍ በንዑስም ሆነ በዋና ገጻባህሪነት ይመጣሉ። ለምሳሌ ኦልቬቲን በሌላ መጽሐፉ ውስጥ የምናውቃት በሴተኛ አዳሪነት ነው። እዚህ ላይ ግን በሌላ መልኩ ነው የምትመጣው። እነዚህ እነዚህ ነገሮች በመዝሙረ ሄላም አንደ ልዩ ነገር መነሳት ይችላሉ።
ሌሎች መጻሕፍቶቹ ላይ የነበሩ መቼቶች ጋር የሚመሳሰሉ መቼቶችን ይፈጥራል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በሚገርም መልኩ አገላለጽን አለመድገሙ በጣም ይገርማል። ሌሎች መጻሕፍቶቹ ላይ የሌሉ ብዙ አገላለጾች እናገኛለን። ምን ያህል የአገላለጽ እና የቃላት ሃብታም መሆኑን የምናይበት ነው።
ቢቢሲ አማርኛ፡ አዳም በመዝሙረ ሄላም ውስጥ የእድገት በኅብረት ዘመቻን ማምጣቱን ሰምተናል። ከዚህ በፊት ሌሎቹን ታሪካዊ ሁነቶች ጠቅሷል ግን እድገት በኅብረት ዘመቻን አልተጠቀመም። በምን መልኩ ነው የተጠቀመው?
ቢኒያም አቡራ፡ አዳም ‘ይወስዳል መንገድ’ ላይ የማዘጋጃ ቤት ፍንዳታን በማምጣት የጻፈውን እናነባለን። ግራጫ ቃችሎችም ላይ ይኸው ክስተት ይጠቀሳል። አሁን መዝሙረ ሄላም ላይም ደግመን እናነበዋን። የታኅሣሥ ግርግርም ይወስዳል መንገድ ላይ አለ። እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ሁነቶችን በሌሎቹ መጻሕፍቶቹ ላይ ደጋግሞ ደጋግሞ ያመጣል።
የእድገት በኅብረት ዘመቻን ግን ብዙዎቹ መጽሐፍቶቹ ላይ አናገኝም። በወፍ በረር ካልተጠቀሰ በቀር። እዚህኛው ላይ ግን ሰፊ ምዕራፍ ሰጥቶታል። ያንን የቃኘበት መንገድ ከ’ኒው ሂስቶሪሲዝም’ ጋር በተቀራረበ መንገድ ነው።
የእድገት በኅብረት ዘመቻን የተለያዩ ሰዎች በሕይወት ታሪካቸው ውስጥ አካትተው ይጽፋሉ። ሲጽፉት የየራሳቸው ድምጸት አለ። ለምሳሌ የኢህአፓ አባል ከሆነ የእድገት በኅብረት ዘመቻን የሚያይበት መነጽር አለ። እንደዚሁ ደግሞ የደርግ ደጋፊ ከሆነ ደግሞ የራሱ መነጽር አለው።
Kአዳም ደግሞ የእድገት በኅብረት ዘመቻን በገጸባህሪያቱ በኩል አዲስ በሆነ መንገድ ነው የሚያሳየን። እዚያ ውስጥ የነበረውን መጠላለፍ፣ በጎም ነገር በማንሳት በደንብ ያሄሳል።
ቢቢሲ አማርኛ-ከአዳም ሥራዎች ሁሉ ለአንተ የትኛው ይበልጥብሃል?
ቢኒያም አቡራ- የአዳም መጽሐፍ እርስ በርሳቸው ለማወዳደር የሚቸግሩ ናቸው። ስለዚህ እንዲህ ላስቀምጥልህ፦ በእምቅነት ጉዳይ ምሳሌ መስጠት ስፈልግ “አፍን” እጠቅሳለሁ። ይሄ እምቅነት ግን ሌሎቹም ላይ አለ። ለምሳሌ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ”ም እምቅነት አለው። ግን “አፍ” ፣ ከይወስዳል የበለጠ እምቅ ነው።
አገላለጽን (description) በተመለከተ መደመም ሲያምረኝ “ግራጫ ቃጭሎች” ጋር አቀናለሁ። “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” በአስደማሚ አገላለጾች የተሞላ ስላልኾነ ነው? አይደለም።
ከአጫጭር ልብወለድ መድብሎቹ “ማኅሌት”ን አስቀድማለሁ። ያ ማለት እንደ “የብሩክታዊት ጠጠር … ኦቾሎኒ … ሕማማትና በገና … የድንች መዋስእት፣ ሦስት ቀኖች … …” ያሉ፣ ከማኅሌት ውጪ ያሉ የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ደካማ ናቸው ማለት ነው? አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹ “ማኅሌት” ላይ ካሉ አጫጭር ልብወለዶች የሚሻሉበት ጎን ነገር ሊኖራቸው ይችላል።
ከኒው ሂስትሮሲዝም (new historicism) አንጻር፣ ለየተራኪው ከሰጠው ድምፀትና አጻጻፍ መንገድ ልከኝነት አንጻር፣ ልብወለዶቻችን የዘነጉትን ነገር ከማካተት አንጻር፣ “መዝሙረ ሄላም”ን እላለሁ። እነዚህ ነገሮች “መረቅ” ላይ ስለሌሉ ነው? አይደለም።
በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ለጥሩ ስቲሪም ኦፍ ኮንሻስነስ (stream of consciousness) አጻጻፍ ኹነኛ አስረጂ ማሳየት ስፈልግ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ጋር ነው የምሄደው።
እናም የአዳም ሁሉም መጻሕፍቱ ዘመን አይሽሬ ናቸው። ነገር ግን አንድ የአዳም ረታ የምን ጊዜም ምርጥ ሥራ (masterpiece) የኾነ መጽሐፍ ጥራ ካልከኝ – የስንብት ቀለማት – እልሃለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ- በአርትኦት ስለተሳተፍክ መዝሙረ ሄላምን ትላለህ ብዬ ነበር።
ቢኒያም አቡራ – (ሳቅ) መዝሙረ ሄላም የራሱ የሆነ ውበት እና ልዩ የሚያደርገው ነገር አለው። የአዳም መጻሕፍት አንዳቸውን ከሌላኛቸው ጋር እንዳይነጻጸሩ ሆነው የተሠሩ ናቸው። ይወስዳል መንገድን ከስንብት ቀለማት አታነጻጽረውም። ምክንያቱም የጋራ ነገሮቹ ውሱን ናቸው። የሚጠቀመው የሥነ ጽሑፍ ቲዎሪ ጽንሰ ሃሳብ ከአንዱ መፍሐፍ ሌላኛው ላይ ስለሚጨምርበት በጣም ያስቸግራል።
አንዱ መጽሐፍ ላይ ‘ማጂካል ሪያሊዝም’ ሰፊ ስፍራ ቢይዝ፣ በሌላኛው ደግሞ ‘ዲኮንስትራክሽን’ ይጎላል። በሌላኛው ደግሞ ‘ኒው ሂስትሮሲዝም’ ይሆናል የጎላው። ስለዚህ የመቼት መመሳሰል እና የጭብጡ ተቀራራቢ መሆን ቢያስተሳስራቸውም እርሱ ካለው የአገላለጽ ብዙነት የሥነ ጽሑፍ ጽንሰ ሃሳቦች አንዱ ከሌላኛው እንዲለዩ ያደርጋል።
ቢቢሲ አማርኛ- አዳም በዘፈቀደ ሳይሆን በንባብ የደረጀ ይሁነኝ ብሎ ሥራዎቹን የሚያዋቅር ነው ወይስ ንሸጣው ጎልቶ የሚታይበት ደራሲ ነው?
ቢኒያም አቡራ – አዳም ላይእነዚህ ነገሮች ተቀላቅለው ነው የማገኛቸው። ሥራው ውስጥ ይህንን ነገር ይሁነኝ ብሎ ካላደረገው አይመጣም የምትለው አለ። አንዳንድ ነገሮቹ ደግሞ ንሸጣ ነው የምትለው አለ። አዳምን ከሌሎች ደራሲዎች የሚለየው ወይንም ትልቅ ያደረገው እንደዚህ ዓይነት መዓት ነገሮች ስላሉት ነው።
አንዳንድ ሰው የተጠና ነገር ይዞ ስለሚጽፍ ደረቅ ይሆናል። የአንዳንዶች ደግሞ ንሸጣ ይሆንና በደንብ ስሜት ይኖረዋል፤ ሌላኛው ነገር ይጎላል። አዳም ግን ይሁነኝ ብሎ የሚያበጃጃቸው ነገሮችም አሉት። በንሸጣም የተጻፉት ሥራዎች አሉት።
አንዳንድ ፀሐፊዎች አገላለጻቸው አሪፍ ነው፤ ቋንቋቸው ቃላታቸው ያምራል፤ ታሪክ ግን ይጎላቸዋል። አንዳንዶች ታሪክ አላቸው፤ አገላለጽ ባዶ ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ ሥነ ጽሑፋዊ ማዕቀፉ እና ጽንሰ ሃሳቡ ባዶ ይሆናል። አዳም ግን አንድ ደራሲ የሚያስፈልጉት ሁሉም ግብዓቶች ተሟልተው ያሉት ደራሲ ነው። አሉት ከማለት ባሻገር ደግሞ የመመጠን አቅሙ ለሥራዎቹ ውበት እንዲጎላ አድርጓል።
BBC
