ኢትዮጵያና ሕንድ ለዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤቶች የቪዛ ነፃ መብትን በይፋ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ።
የሁለቱ አገራት መንግሥታት ቀደም ሲል የደረሱትን የቪዛ ነፃ ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችላቸውን የዲፕሎማቲክ ሰነድ ልውውጥ ዛሬ ጥር 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አከናውነዋል።
ስምምነቱ የሁለቱ አገራት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤቶች ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል። ይህም በአገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቀላጠፍና ተቋማዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማሪ በተገኙበት በተከናወነው በዚህ መርሐ ግብር ላይ፤ እርምጃው በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን ከፍተኛ የመተማመን ደረጃ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱ በወረቀት ላይ ብቻ ሳይወሰን በተጨባጭ ወደ ሥራ እንዲገባ ዝርዝር መመሪያ ተዘጋጅቶለት፣ ከዛሬ ጀምሮ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ያላቸው ዜጎች መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያና ሕንድ ከ2,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የንግድና የታሪክ ትስስር ያላቸው ሲሆን፤ የዛሬው ስምምነት ይሄንኑ ጥንታዊ ወዳጅነት ይበልጥ የሚያድስና አገራቱ በቅርቡ የጀመሩትን “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” በተግባር የሚደግፍ መሆኑ ተመላክቷል።
