ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በሞስኮ እየተካሄደ ባለው የሁለቱ አገራት የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የኒውክሊየር ኃይል ምስጢራዊ መረጃዎችን የመጠበቅ ስምምነት (NDA) መፈራረማቸው ተገለፀ።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳንዶካን ደበበ እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የሮሳቶም (ROSATOM) ኢነርጂ ፕሮጀክቶች ዋና ዳይሬክተር አንድሬ ሮዝድስትቪን ተፈራርመዋል።
ይህ ሚስጥራዊ መረጃዎችን የመጠበቅ ስምምነት የተፈረመው ሁለቱ አገራት የኢትዮጵያን የመጀመሪያ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታና ልማት ለማፋጠን ቀደም ብለው የተገቡትን ስምምነቶች ተግባራዊ የማድረግ የቁርጠኝነት አካል ነው ።
በመስከረም ወር፣ ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ እና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መካከል መፈረሙ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) ዘመናዊ በሆነው እንዲሁም ደህንነቱ በተጠበቀው VVER-1200 ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደሚገነባ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን አስታውቀዋል።
