ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጣሊያን እስራኤል በመላው ጋዛ አስቸኳይ፣ ፈጣንና ያልተቋረጠ የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽነት እንድትፈቅድ ጥሪ አቀረቡ።
የአራቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በጋዛ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ “እጅግ አስከፊ” መሆኑን ገልጸዋል። በጦርነቱ የተጎዳው የጋዛ ነዋሪ ሕዝብ በቅርቡ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ተጨማሪ ችግር እንደገጠመውም አስጠንቅቀዋል።
በመግለጫው መሠረት፣ ወደ ጋዛ መግባት የነበረባቸው 150 ሺህ ድንኳኖችና ሌሎች አስፈላጊ የሰብአዊ ዕርዳታ ቁሳቁሶች በድንበር ላይ ተይዘው እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
የጋዛን መግቢያና መውጫ ቦታዎች የሚቆጣጠረው የእስራኤል ጦር በበኩሉ፣ ከአሜሪካ በሚመራው የሰላም ቦርድና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጿል። 93 ሺህ ድንኳኖችንና የክረምት መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን የጫኑ 8 ሺህ 600 የዕርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባታቸውንም አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር አክሎም፣ የጋዛ መልሶ ግንባታ ሊጀመር የሚችለው ሐማስ ትጥቁን ሙሉ በሙሉ ከፈታ በኋላ ብቻ እንደሆነ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) በበኩሉ፣ በስፋት የተከሰተው የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት ለሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ መጠለያዎች መውደምና ወሳኝ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።
በተመሳሳይ፣ የአውሮፓ ህብረት ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ በጋዛ ያለውን “ቀጣይነት ያለውና አውዳሚ የሰብአዊ ቀውስ” በተመለከተ ያለውን ጥልቅ ስጋት ደግሞ ገልጿል። ህብረቱ እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕግን እንድታከብርም አሳስቧል።
