“የወጣቶችን ሕልም ለማገዝ የሚሠራ ማንኛውም ድርጅት አብሮን ቢሠራ ደስተኞች ነን፡፡”
የአቶ ዜናዬነህ ግርማ የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል። ድርጅታቸው ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› በመጪዎቹ ዐሥር ዓመታት የሚተገበር፣ የትኩረት ማዕከሉንም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በሚገኙ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ዓመት በገጠር በከተማ በትምህርትና ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ወጣቶች ላይ ያደረገ መሪ ዕቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) ይፋ አድርጓል፡፡
ግዮን፡- ትኩረታችሁ የትኞቹ ወጣቶች ናቸው? የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች አካታችነት እንዴት ታዩታላችሁ?
ዜናዬነህ፡- እኛ የምንደርስባቸው አካላት እና አካባቢዎች የት ናቸው የሚለው የሥራችን ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ወጣቶች ላይ ስንሠራ ወጣት ሁሉም ቦታ ማለትም በገጠርም በከተማም አለ፡፡ ያልተማረና የተማረ ወጣት አለ፡፡
የእኛ ሥራ ትኩረት ያደረገው ወጣቶችን ስለኾነ ሁሉንም ወጣቶች ጋር መድረስ አለብን ብለን እናምናለን፡፡ በዋናነትም ሥራችን የኢትዮጵያ ወጣቶችን ፍላጎት ማመቻቸት ነው፡፡ ስለዚህ ወጣት ማነው ስንል አካል ጉዳተኛ፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣… ወዘተ ሁሉንም ዐይነት ወጣት ያካትታል፡፡ እድሜያቸው ከ15-35 ዓመት የኾኑ ወጣቶች ሁሉ እኛ የምንደርሳቸው ናቸው፡፡
ማረሚያ ቤት ያሉ ወጣቶችንም ጭምር ስንረዳ ነበር፤ እድል ያልተመቻቸላቸው ወጣቶችን ሁኔታዎችን በመቀየር የተሻለ ሥራ እንዲሠሩም እናደርጋለን፡፡ እኛ የወጣቶች የአስተሳሰብ አድማስ እንዲሰፉ እና ባለራዕይ እንዲሆኑ ነው የምንሠራው፡፡ የወጣቱ አስተሳሰብ ከተቀየረ ለሀገር ትልቅ ነገር ነው፡፡
ስንሠራ የምንጠቀምባቸው የተለያዩ ስልቶች አሉን፡፡ ወጣቶቻችን አዎንታዊ እሳቤ እንዲያመነጩ እናግዛለን፤ የልማት ዕይታቸው በመልካም የተቃኘ እንዲኾን አስተሳሰባቸውን መለወጥ ላይ እንሠራለን፡፡ ለዚህ የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ወጣቱ ንቁ ዜጋ እንዲኾን እንጥራለን፡፡
ግዮን፡- እነዚህ ሥልጠናዎችን ስትሰጡ ከውጭ ሀገራት የተገኙ ተሞክሮዎችን ታካትታላችሁ?
ዜናዬነህ፡- ሀገር በቀል የኾኑ ነገሮች አሉን፡፡ ከውጭ የምንማራቸው ነገሮችም አሉ፡፡ በመኾኑም በርካታ የተሞክሮ የልምድ ልውውጦችን እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የወጣት ማዕከላት ጥናት ተደርጎ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ተነፃፀሯል፡፡
በቅርቡ በቱርክ በነበረኝ ጉብኝት የቱርክ ወጣት ማዕከላት የሚሰጡት አገልግሎትና የኢትዮጵያ ወጣት ማዕከላት የሚሠጡት አገልግሎት ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ የቱርክ ወጣት ማዕከላት ምቹ የኾነ አጠቃላይ የወጣቶች አገልግሎት ይሰጥባቸዋል፡፡
እነሱ የወጣቶቹን አካልና አዕምሮ እንዲሁም የሥነልቦና አቅም የሚያጎለብቱ ማዕከላት አላቸው፡፡ በሥነጥበብ እና በባህል እንዲሁም በሌሎች መስክ በሁሉም መልኩ የወጣቶችን አዕምሮ መለወጥ የሚችሉ ተቋሞች አሏቸው፡፡
ሌላው ደግሞ ወደ ሕንድ ገጠር አካባቢ ሄደን በጣም የሚያስገርሙና የሚያስቀኑ ነገሮችን በተለይ በትምህርት ልማት ዙሪያ አይተናል፡፡ ይህን ወደእኛ ሀገር አምጥተን ለመተግበር አጋሮች ያስፈልጉናል፡፡ የክልል መንግሥታትም የተለያዩ መድረኮችን ለማዘጋጀትና መልካም ተሞክሮዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ መኾን ይኖርባቸዋል፡፡
ቱርክ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያ፣ ሲዊዘርላንድ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ እና ሎሌች ሀገሮችም ተዘዋውረን በተመለከትንባቸው ጊዜያት እንዴት ወጣቶቻቸውን እንደሚያበቁ ስንመለከት እኛ ሀገር የዘነጋናቸው ወይም መስራት ያለብን ሳንሰራ ያለፍናቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ተረድተናል፡፡
በቀጣይ 10 ዓመታትም እነኚህን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትና ልምድ መለወዋጥ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህ ይረዳም ዘንድ ቱርክ ላይ ‹‹Ethiopian Productivty Association›› ከሚባል ተቋም ጋር የመግባቢያ ሰነድ ውል ተፈራርመናል፡፡
ወጣቶቻችንን ለማብቃት፣ እንዲሁም ወጣቶችን የሚደግፉ ተቋማት ልምድ እንዲቀስሙም ወደ ቱርክ ለመውሰድና የመልካም ስራ ተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ አቅደናል፡፡ ይኼ የሚሠራው በሁለቱ ተቋማት ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር ነው፡፡ መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ያግዘናል ብለን እናምናለን፡፡ በዋናነት በተለይ ግን የቱርክን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንፈልጋለን፡፡
ግዮን፡- የ10 ዓመት እቅዳችሁን መከወን ጀምራችኋል?
ዜናዬነህ፡- የ10 ዓመት እቅዱ ባለፈው ሚያዚያ 2017 ዓ.ም ቦርዱ አጽድቆት ወደ ተግባር ሥራ ከገባን ሰንብተናል፡፡ ባለፉት 3 እና 4 ወራት ውስጥ አዲሱን የእቅድ መተግበሪያ ሥራዎችን ስንሠራ በመቆየታችን አዳዲስ አጋሮችን አግኝተናል፡፡ ይኼ አንዱ የእቅዱ ውጤት ማሳያ ነው፡፡
ግዮን፡- የአጋር ድርጅቶቻችሁን ስም መጥቀስ ይቻላል?
ዜናዬነህ፡- አጋር ድርጅቶቻችን በጣም በርካታ ናቸው፡፡ የግል ተቋማት፣ ባንኮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ እና መንግስታዊ የሆኑ ተቋማት፤ ሚዲያ፤ የእምነት ተቋማት ፣… ሌሎችም አብረውን ይሠራሉ፡፡
ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ ሜሪስቶፕ፣ የፊኒሽ ሪፊውጅ ካውንስል፣ ማላላፈንድ፣ የአለም አቀፉ ሪስኪው ኮሚቴና አምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ፤ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ማህበራት ጥምረት፤ ጥምረት ለስነተዋልዶ ጤና ማህበራት ተቋም፤ የፊንላንድ እና አውስትራሊያ ኤምባሲዎች ጋር አብረን እንሰራለን፡፡ ሌሎች በርካታ አዳዲስ ተቋማት ወደ እኛ ጋር በመምጣት የመግባቢያ ሰነዶችን በጋራ ለመስራት ተፈራርመናል፡፡
ግዮን፡- በተጨማሪ ለሌሎች አዳዲስ ተቋማትስ አብረዋችሁ እንዲሠሩ ምን ጥሪ ታቀርባላችሁ?
ዜናዬነህ፡- ማስተላለፍ የምፈልገው የምንሠራው ሥራ የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አለመኾኑን ነው፡፡ እንደተቋም የራሳችን እቅድና ተልዕኮ ቢኖረንም፣ ድርጅታን ለብቻው የሚሠራው ሥራ የለም፡፡ ሁሉንም የሚያደርገው በአጋርነት መንፈስ ነው፡፡ መሪ ልንኾን እንችላለን፡፡
ነገር ግን የወጣቶች ሥራ ላይ ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡ በርካታ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ወጣቶችን ‹‹የተቀመጠ ወይም ተደበቀ ፈንጅ›› ይላቸዋል፡፡
ወጣቶቻችንን በአግባቡ ወደ መልካሙ አቅጣጫ ካላመላከትናቸውና ካላበቃናቸው ችግሩ ከባድ ነው፡፡ በአንፃሩ ወጣቶችን ካበቃን እና ለልማት እንዲሳተፉ ካደረግን ትርፉ ከአንድ ሀገር እድገትም በላይ ነው፡፡ እኛ በርካታ ጥሩ ነገሮች ያሉን ጠንካራ ተቋም ነን፡፡ ወጣቶች ለተሻለ ህይወት እንዲሰሩ ከሚደግፉ ተቋማት ውስጥ የእኛ ተቋም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
ተቋማችን ወጣቶችን ለመርዳት የሚያስችል ክፍት እና ሁሌም እራሱን ለመማር የሚያዘጋጅ ተቋም ነው፡፡ የወጣቶችን ሕልም ለማገዝ የሚሠራ ማንኛውም ድርጅት አብሮን ቢሠራ ደስተኞች ነን፡፡ እኛም ከወጣቶች ጋር የሚሠሩ ተቋማትን አጋርነት እንፈልጋለን፡፡ እንዲሁም በሀገሪቱ ወጣት መር ለሆኑ ተቋማት በርካታ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
ግዮን፡- ተቋማችሁ በዚህ በ10 ዓመት እቅዱ በዋናነት ማሳካት የፈለገው ምንድን ነው?
ዜናዬነህ፡- የተልዕኮ ግባችንን በተለያየ መልኩ ከላይ ገልጬዋለሁ፡፡ ኾኖም ግን እንደወጣቶች አገልጋይ ድርጅት ዓላማችን ወጣቶችን በሁለንተናዊ መንገድ ማብቃትና አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ማጎልበት ነው፡፡
ለሀገር ሰላምና ብልጽግናን ለውጥ የሚያመጡ ወጣቶችን ማፍራት ነው የምንሻው፡፡ የፈጠራ ክህሎታቸው ያደገ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እና ተነሳሽነታቸው የዳበረ ባለርዕይ ወጣቶችን ለማፍራት እንሠራለን፡፡ እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን በርካታ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዞችንና ወጣት መር ተቋማትን በስፋት በክልል ከተሞች ለማቋቋም እንፈልጋለን፡፡
እንዲህ ዓይነት ኢንተርፕራይዞችን በመሠረትን ቁጥር ወጣቶቻችን ወደ አላስፈላጊ ነገር የመሄዳቸው መጠን እየቀነሰ ይሔዳል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ወጣቶች እየበቁና የመሪነት ሚና እና ለልማት ተነሳሽነት የሚጎናፀፉበት ሁኔታ ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡ ለሀገራቸው ትልቅ ነገር መሥራት የሚችሉ ወጣቶችን እንቀርፃለን ብዬም አስባለሁ፡፡
በተጨማሪም የባሕል ቅርሶቻችንን የምንጠብቅበትና አካታች ማኅበረሰብ የምንፈጠርበትን ሁኔታ የሚያስችል የሰላም እና ልማት ወጣት አርበኞች በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በተቋማችን በርከት ያሉ የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን፡፡
ግዮን፡- ተቋማችሁ ያገኛቸው ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቶች ምንን ምክንያት ያደረጉ ናቸው?
ዜናዬነህ፡- ዓለም አቀፍ እውቅናዎች ለተሠሩ መልካም ሥራዎች የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ሁለት የክብር ዶክትሬቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ይህ የተገኘው ለማኅበረሰብና ለወጣቶች በተሠሩት ሥራዎች ነው፡፡ ድርጅቱ ከ30 ያላነሱ የእውቅና ሰርተፍኬቶች እና ሜዳሊያዎች በምንሰራባቸው ክልሎች አግኝቷል፡፡ ይኼ ለማኅበረሰቡ ባበረከትናቸው በርካታ ሥራዎች ምክንያት የተገኘ ነው፡፡
ግዮን፡- የተፈጠረባችሁ ተነሳሽነት አለ?
ዜናዬነህ፡- ተነሳሽነት መፍጠሩ ብቻ ሳይኾን በሥራችን ላይ ይበልጥ እንድንዘጋጅና ተደራሽነታችን እንዲሰፋ ወጣቶች ላይ ይበልጥ እንድንሠራ ከዚህ በላይም ኃላፊት እንዳለብን መልዕክት ይሰጠናል፡፡ ሌጋሲዎቻችንን እንድናስቀጥል ይደግፈናል፡፡ እነዚህ ሽልማቶች ሳያዘናጉን ይበልጥ እንድንሠራ ያደርጉናል፡፡ አጋሮቻችንም ይበልጥ እንዲተማመኑብን ያደርጋል፡፡ ሕልም አለን አንተኛም፣ ሕልማችንን እናቀጣጥላለን፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ካለ?
ዜናዬነህ፡– የእኛ ድርጀት እቅዶች በጣም አጓጊ ናቸው፡፡ መልካም ምኞት መመኘት ጥሩ ነው፡፡ በምኞት ብቻ እንዳይቀር ደግሞ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ የኛ የ10 ዓመት መሪ እቅዳችን ሕልምን ከሥራ ጋር የሚያጣምር ነው፡፡ ተስፋን በተግባር መተርጎም እንሻለን፡፡
ወጣቶቻችን ተስፋ እንዳይቆርጡ እንፈልጋለን፡፡ ወጣቶቻችን አቅም አላቸው፤ አቅማቸውን በአዎንታዊ ጎኑ ለመቀየር በርካታ እገዛዎች ያስፈልጉናል፡፡ ስለ ሥራችን ብዙ አልተነገረም ፤ ሚዲያዎችም ሥራዎቻችንን እንድታጎሉ ነው የምንፈልገው፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 226
