በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በተከሰተ ከባድ የእሳት አደጋ ቢያንስ 30 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
አደጋው በጊዛ ግዛት ሥር በሚገኘውና በብዛት የመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በሚኖሩበት ዋራቅ አካባቢ መከሰቱ ተገልጿል። ከአደጋው ስፍራ የተቀረጹ ምስሎችም ከፍተኛ የእሳት ነበልባልና ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ ያሳያሉ።
የግብፅ ጤና ሚኒስቴር በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ለመታደግ 39 አምቡላንሶች ወደ ስፍራው መላካቸውን ገልጿል። በአደጋው የቆሰሉ 15 ሰዎችም ወደ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቋል።
በግብፅ የሚዲያ ዘገባዎች መሠረት፣ አደጋው በካይሮ ቀለበት መንገድ ላይ የነዳጅ ጭነት የያዘ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በመፈንዳቱ መከሰቱ ተገልጿል። የአደጋው መንስኤና የጉዳቱ መጠን በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል።
