ዓድዋ! – የአደራ ደም እና የነፃነት አዋጅ !

Date:


ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን
)


ግዮን መጽሔት :- ዛሬ የምንተነፍሰው የነፃነት አየር፣ በኩራት ቀና ብለን የምንሄድበት መሬት እና እንደ አገር የምንጠራበት ስም በነፃ የተገኘ አይደለም፡፡ ይህ ክብር የተገነባው የገዛ ህይወታቸውን ለሞት አሳልፈው በሰጡ፣ ለአገራቸው ክብር ሲሉ እንደ ጧፍ በበሩ የዓድዋ ጀግኖች ደም እና አጥንት ነው፡፡ ​

እነዚያ ጀግኖች አባቶቻችን በጦር ሜዳ መካከል፣ ጥይት እንደ በረዶ በሚዘንብበት ሰዓት፣ እንደ ቅጠል እየተበጠሰ ለሚወድቅ አካላቸው ወይም ስለ ግል ህይወታቸው አልተጨነቁም፡፡  ከፊታቸው የታያቸው የሚወዷት አገራቸው በባዕድ ሳትገዛ  እንድትኖር፣ ልጆቻቸው በነፃነት እንዲያድጉ እና ሰንደቅ ዓላማቸው ዝቅ እንዳይል ብቻ ነበር፡፡ እነሱ ለኛ ዛሬ ሲሉ ትላንታቸውን የሰጡ፣ ለኛ ነገ ሲሉ የራሳቸውን ዛሬ የሰዉ ታላላቅ ባለውለታዎቻችን ናቸው፡፡


ውድ አንባቢያን፣


​130ኛው የዓድዋ ድል ክብረ በዓል በመላው ኢትዮጵያና በጥቁር አፍሪካውያን እንዲሁም የኢትጵያ ወዳጆች ዘንድ ታላቅ ታሪክ በመሆኑ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል፡፡ የዛሬ 130 ዓመት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የተገኘው የነፃነታችንን ዋጋ ለመለካት፣ የክብራችንን መሠረት ለመፈተሽ እና የነፍሳቸውን ዋጋ ከፍለው አገር ላቆሙልን ቅዱሳን ጀግኖቻችን ምስጋና ምንግዜም ይገባቸዋል፡፡


​እነዚያ በጦር ሜዳ የረገፉት ጀግኖች፣ አባቶቻችን ሞት ወደ እነሱ ሲመጣ አልሸሹም፡፡ ይልቁንም ሞትን እንደ ሰርግ ጥሪ በፈገግታ ተቀበሉት፡፡ ለምን? ምክንያቱም ከገዛ ህይወታቸው በላይ የሚበልጥ ትልቅ ህልም ነበራቸው፡፡


ያ ሕልም “ኢትዮጵያ” ትባላለች! ያ ሕልም “ነፃነት” ይባላል! እነሱ በጠራራ ፀሐይ የተቃጠሉት እኛ በጥላ ስር እንድንቀመጥ ነው፡፡ እነሱ በቁርና በበርድ  የተገረፉት እኛ በሞቀ ቤት እንድንኖር ነው፡፡ ዛሬ የምናሳየው ኩራት፣ የምንናገረው ቋንቋ እና የምንረግጠው መሬት ሁሉ የነዚያ ጀግኖች ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩልን የአባቶቻችን ውድ ስጦታ ነው፡፡


​ውድ አንባቢያን፣


​ጀግንነት ማለት በጦር ሜዳ ተሰልፎ ጥይት መተኮስ ብቻ አይደለም፡፡ ጀግንነት ማለት ከራስ በላይ ለሌላው መኖር ነው፡፡ ጀግኖች አባቶቻችን ሲዋደቁ ሲወድቁ ‹‹እኔ የት ልቀበር?›› ብለው አልተጨነቁም፡፡ ይልቁንም ‹‹አገሬ የት ትደርስ ይሆን?›› ብለው ነበር የተጨነቁት፡፡ እነሱ የፈሰሰው ደማቸው ለምድሪቱ ማዳበሪያ ሆኗል፡፡

የተከሰከሰ አጥንታቸው የኢትዮጵያን ዳር ድንበርን አጥሮታል፡፡ የዓድዋን ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የነፃነት ፋና እና የኢትዮጵያዊነት ማኅተም አድርገውት አልፈዋል፡፡ ይህ ታሪካዊ ዘመቻ ተራራን የመቧጠጥ ያህል የከበደ ቢሆንም፣ በአባቶቻችንና እናቶቻችን ጽናት ግን የማይታለፈው ታለፈ፣ የማይቻለውም ተቻለ፡፡


​​ዓድዋ የፍቅርና የአንድነት ጥሪ ሲሆን ከክፉ ጠላት የሚከላከል አንድ ልብ፣ ለአገር የሚራራ አንድ ነፍስ የታየበት ዘመቻ ነበር፡፡ ንጉሡ የክተት አዋጅ ሲያውጁ፣ ገበሬው እርፉን፣  ነጋዴው ሚዛኑን፣ ካህኑ መስቀሉን ትቶ ‹‹ለአገሬ!›› ብሎ በአንድ ቃል ተመመ፡፡

ከአራቱም ማዕዘናት የፈሰሰው ያ የአርበኞች ጎርፍ፣ ልዩነትን በኢትዮጵያዊነት ቀልጦ ዓድዋ ላይ ተገናኘ፡፡​ ​የዓድዋ ሰማይም በጭስና በባሩድ ሲታጠን፣ ጀግና አባቶቻችን  ለሥጋቸው ሳይሆን ለክብራቸው በአንድ ላይ ቆሙ፡፡ ​ዓድዋ የጦርነት ድል ብቻ አልነበረም፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆኑን ለዓለም ያበሰረ የወንጌል ቃል ነበር፡፡

ያ የጀግኖች ክንድ የነጭን ዘመናዊ መሣሪያ ሲያንበረክክ፣ በባርነት ቀንበር ስር ለነበሩ ሁሉ የነፃነት ተስፋ ሆናቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው ቃል በተግባር የታየበት፣ የታሪክ ማህደር በጀግኖች ደም የተከተቡበት የጌወርጊስ ታቦት ከመንበሩ በመውጣት አብሮ የዘመተበት  ታላቅ ቀን ነበረ፡፡


​ዛሬም 130ኛውን የዓድዋን ድል ስናከብር፣ አባቶቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ‹‹አገር ማለት ከራስ በላይ ነው›› የሚል ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ለዚህ ነው ዛሬም ድረስ የዓድዋ ድል በታሪክ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፣ በልባችንም ውስጥ ተፅፎ ይነበባል፡፡


የዓድዋ ድል በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ በጥንቃቄ የታቀደ ስልታዊ አመራር እና የኢትዮጵያዊያን  ተወዳዳሪ የሌለው ጀግንነት ውጤት የሆነው፡፡ ​


፩. የዓድዋ ጦርነት ስልታዊ አመራሮች (Strategy)


​የኢትዮጵያ መሪዎች በወቅቱ የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ብልሃት የተጠቀሙባቸው መንገዶች የሚደነቁ ናቸው፡-


• ​የደብዳቤና የዲፕሎማሲ ስልት፡ አፄ ምኒልክ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር በደብዳቤ በመገናኘት፣ የጣሊያንን ግፍ ለዓለም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ጣሊያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞራል ድጋፍ እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡


• ​የ‹‹መሸሽ›› እና የ‹‹መሳብ›› ስልት (Tactical Retreat)፡ የኢትዮጵያ ጦር ወደ መሀል አገር እየሸሸ በመምሰል ጣሊያን ሰራዊት ካስቀመጠበት ምሽግ በማስወጣት፣ ረጅም መንገድ እንዲጓዝና እንዲዝል ሲያደርጉት  ጠላት የሎጂስቲክስና የቀለብ ችግር እንዲገጥመው አሰችሏል፡፡


• ​የመረጃ መረብ (Intelligence)፡ እንደ ባሻዬ አውአሎም ያሉ የውስጥ አርበኞች ጣሊያኖችን በሀሰት መረጃ በማሳሳት፣ የጠላት ጦር ባልተዘጋጀበት ሰዓትና ባልፈለገው ቦታ እንዲገጥም አድርገዋል፡፡


• ​የውኃ ምንጭን የመዝጋት ስልት፡ በመቀሌው ከበባ ወቅት እቴጌ ጣይቱ ያሳዩት ብልሃት የሚጠቀስ ነው፡፡ የጣሊያንን ጦር የውኃ ምንጭ በመዝጋት፣ ጠላት ተጠምቶ እጁን እንዲሰጥ ወይም እንዲዳከም አድርገዋል፡፡


፪. የጀግኖች ታሪክና መስዋዕትነት


​በጦርነቱ ላይ ድንቅ ገድል የፈጸሙ ጀግኖች ብዙ ቢሆኑም፣ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-


​እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሃን ዘኢትዮጵያ)


​እቴጌ ጣይቱ ‹‹የኢትዮጵያ እናት›› ብቻ ሳይሆኑ፣ የጦር ስትራቴጂስትም ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ግንባር ድረስ በመገኘት ሰራዊቱን በማበረታታት፣ የውኃ ስልትን በመቀየስና የሴት አርበኞችን በመምራት የድሉ ዋነኛ ምሰሶ ሆነዋል፡፡


ራስ መኮንን ወልደሚካኤል


​የአፄ ኃይለሥላሴ አባት የሆኑት 15 ሺህ ጦር አስከትለው የዓድዋን ጦርነት የመሩ ሲሆን በዲፕሎማሲውም ሆነ በጦር ሜዳው ታላቅ ታሪክ የፃፉ ናቸው፡፡ በተለይም በመቀሌው ጦርነትና በዓድዋ ተራሮች ላይ ጦራቸውን በብቃት በመምራት የጠላትን ኃይል በመስበር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡


ራስ አሉላ አባ ነጋ


​‹‹የአፍሪካው ታላቅ የጦር መሪ›› በመባል የሚታወቁት አሉላ አባነጋ ለጣሊያኖች ትልቅ ራስ ምታት ነበሩ፡፡ የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመገመትና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ወደር አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ጣሊያን አገሬን ሊወር አይችልም›› በሚል ፅኑ አቋማቸው የድንበር ጠባቂ ተምሳሌት ሆነው አልፈዋል፡፡


ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ


​በመድፍ ተኳሽነታቸውና በጀግንነታቸው የሚታወቁት ባልቻ፣ አባ ነፍሶ የዓድዋ ጦርነት ሲጀመር በወጣትነት ዕድሜያቸው ድንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ የጠላትን ምሽግ በመድፍ በመምታትና የሰራዊቱን ወኔ በመቀስቀስ ረገድ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱት ጀግኖች አንዱ ናቸው፡፡
‹‹ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ›› ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡


አፄ ምኒልክ (አባ ዳኘው)


​እንደ አባት መሪ፣ እንደ ወታደር ጀግና ነበሩ፡፡ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በማሰለፍ፣ በጦር ሜዳው ላይ ሆነው ሰራዊቱን በመምራት ‹‹እምዬ›› የሚለውን ስም በደም የተከፈለ መስዋዕትነት አትርፈዋል፡፡ ገበየሁ ጎራ፣ በሻህ አቦዬ፣ ትንታጉ ታፈስ፣ ኧረ ስንቱን ልጥራ !! የዓድዋል የእነዚህና የሺዎች ስም ያልተጠቀሱ ጀግኖች ደም፣ ላብና ጥበብ ውጤት ነው፡፡


እናንተ ጀግኖች ሆይ! የታሪክ ማህደር ባይዘግባችሁም፣ ስማችሁ ባይታወቅም፣ መቃብራችሁ በሩቅ ቢሆንም፤ እኛ ግን ውለታችሁን በልባችን ሰሌዳ ላይ በትውልድ ቅብብል እናኖረዋለን፡፡ የእናንተ ብርታት የኛ ወኔ ነው፤ የእናንተ መስዋዕትነት የኛ ብርሃን ነው፡፡


​ዛሬም ድረስ ይህ ታሪክ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት ሆኖ እንዲያበራ አድርጋችሁት አልፋችሗል፡፡ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ የቀየረ፣ የሰው ልጅን የክብርና የነፃነት እይታ የለወጠ ክስተት ነው፡፡


ውድ አንባቢያን፣


የዓድዋ ድል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳደራቸው ዋና ዋና ተጽዕኖዎችን ለትዝታ ባነሳቸው ታሪኩን ሙሉ ያደርግልናል ብየ አስባለሁ፡፡


​፩. የጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የፓን-አፍሪካኒዝም መነሳሳት
​ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች “ማሸነፍ እንችላለን!” የሚለውን ተስፋ ያለመለመ ድል ነው፡፡


• ​የነፃነት ፋና፡ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ አፍሪካውያን እና በአሜሪካና በካሪቢያን ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦች፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ምሳሌ ሆነች፡፡


• ​የሰንደቅ ዓላማ ተምሳሌት፡ ሳይቀር ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በማመሳሰል (አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ) አድርገው ለብዙ የአፍሪካ አገራት የነፃነት ምልክት በመሆን፣ ዛሬ ድረስ ከ20 በላይ የሚሆኑ አገራት ተመሳሳይ ቀለም እንዲጠቀሙ ምክንያት ሆኗል፡፡​


፪. ዓድዋ  ‹‹ነጭ የማይሸነፍ ነው›› የሚለውን አስተሳሰብ መስበሩ
​በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን “የላቀ ዘር ነን፣ በጦርነትም አንሸነፍም” የሚል ትዕቢት ነበራቸው፡፡


• ​የታሪክ ለውጥ በማድረግ  ዓድዋ አውሮፓውያን በአፍሪካውያን የተሸነፉበት የመጀመሪያው ታላቅ የጦርነት ድል በመሆኑ፣ የአውሮፓውያንን ‹‹የበላይነት›› ትረካ አፈራርሶታል፡፡


• ​የጣሊያን መሸማቀቅ፦ ድሉ በጣሊያን መንግሥት ላይ ትልቅ ውድቀት አስከትሏል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍራንቸስኮ ክሪስፒ ስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡


​፫. ለጸረ-ቅኝ ግዛት ትግል መሰረት መሆኑ
​ዓድዋ የቅኝ ግዛት ዘመን ማብቂያ መጀመሪያ (End of the beginning) እንደሆነ አረጋግጧል፡፡


• ​ዓድዋ የመቋቋም ተምሳሌት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ድል በጋና፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያና በሌሎችም አገራት ለነበሩ የነፃነት ታጋዮች የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ካሸነፈች እኛም እናሸንፋለን” የሚል ወኔ ፈጥሯል፡፡


• ​ዲፕሎማሲያዊ እውቅና፦ ድሉን ተከትሎ ታላላቅ የአውሮፓ አገራት (እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ) ኢትዮጵያን እንደ ሉዓላዊት አገር እውቅና ሰጥተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ተገደዋል፡፡


​ዓድዋ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ትርጉምም (Ethiopianism) ነበረው፡፡
​በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው ቃል ከዓድዋ ድል ጋር ተዳምሮ፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያ ‹‹ቅድስት ምድር›› እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በኋላ ላይ ለራስተፋሪያኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡


​ባጠቃላይ፦ ዓድዋ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የአድሎና የጭቆና ቀንበርን ለመስበር ለሚታገሉ የሰው ልጆች ሁሉ የድል አርማ ሆኖ አገልግሏል፡፡
​ዓድዋ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት እንድትሆን ያደረጋት  ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ በወቅቱ የዓለምን መገናኛ ብዙኃን ያስደነገጠ እና ‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ?›› የሚያሰኝ የዓለማችን ታላቅ ዜና ነበር፡፡

ዜናው አውሮፓ ሲደርስ እንደ ዛሬው ፈጣን ኢንተርኔት ባይኖርም፣ በቴሌግራፍ አማካኝነት ሰደድ እሳት ሆኖ ነበር የተሰራጨው፡፡ ​በወቅቱ የነበሩ ዋና ዋና የዓለም ጋዜጦች ድሉን የዘገቡበት መንገድ እንዲህ ይነበባል፡፡​


​በጣሊያን አገር ዜናው ሲሰማ ሕዝቡ በመንገዶች ላይ ወጥቶ ተቃውሞ አድርጓል፡፡


* ጋዜጦች የጣሊያንን ጦር መሸነፍ ‹‹ታላቅ ውርደት›› እና ‹‹ብሔራዊ ሀዘን›› አድርገው ዘግበውታል፡፡


• ​ውጤቱ፦ በሮም፣ በናፖሊና በሚላን ከተሞች ‹‹ምኒልክ ይንገስ!›› (Viva Menelik!) እያሉ የገዛ መንግሥታቸውን የተቃወሙ ጣሊያናውያን ነበሩ፡፡


ይህ የሆነው ጦርነቱ ፍትሃዊ እንዳልነበር በማመናቸውና በሽንፈቱ በመበሳጨታቸው ነው፡፡


​የአሜሪካው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ በወቅቱ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተል ነበር፡፡
• ​ዘገባው፦ ‹‹ጣሊያኖች በአቢሲኒያ (ኢትዮጵያ) ክፉኛ ተመቱ›› የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡


• ​አድናቆቱ፦ ጋዜጣው አፄ ምኒልክን ‹‹የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ንጉሥ›› በማለት የገለጻቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ጦር ጀግንነትና የጦር ስልት ከአውሮፓውያን ጋር የሚመጣጠን እንደሆነ መስክሯል፡፡
​የእንግሊዝ ጋዜጦች ዜናውን የዘገቡት በከፍተኛ ጥንቃቄና በመገረም ነበር፡፡


• ​ትኩረቱ፦ ‹‹በአፍሪካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሽንፈት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡


• ​ትንታኔው፣ የአውሮፓውያን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መውደቁንና ኢትዮጵያ በጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በስትራቴጂም እንደበለጠች ጽፈዋል፡፡


​ፈረንሳዮች በወቅቱ በስዕላዊ ዘገባዎቻቸው ይታወቁ ነበር፡፡
• ​ስዕላዊ መግለጫ፦ Le Petit Journal የተባለው ጋዜጣ በግንባር ገጹ ላይ የዓድዋን ጦርነት የሚገልጽ ቀለም ያለው ስዕል አውጥቶ ነበር፡፡ ስዕሉ የኢትዮጵያን ጦር ግርማ ሞገስና የጣሊያንን ሠራዊት መፍረክረክ በግልጽ ያሳይ ነበር፡፡


• ​አመለካከታቸው፦ ለጣሊያን ሽንፈት ባይጸጸቱም፣ በአፍሪካ ውስጥ እንዲህ ያለ ኃያል መንግሥት መኖሩ ለአውሮፓውያን የወደፊት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡


​የጋዜጦቹ
ዘገባ አንድ የሚያደርጋቸው ነጥቦች፡
• ​ድንጋጤ ‹‹ጥቁር ሕዝብ ነጭን ያሸንፋል›› ብለው ጨርሶ አለማሰባቸው፡፡


* አፄ ምኒልክን
እንደ ጥበበኛና ኃያል መሪ መመልከታቸው፡፡
• ​የታሪክ ምዕራፍ እንደተዘጋ ቆጥረው የአውሮፓ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ጋሬጣ እንደገጠመው መረዳታቸው፡፡


​ዓድዋን በጋዜጣ የታተመ የነፃነት አዋጅ አርገውታል፡፡ ምክንያቱም የዓድዋ ድል በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው ጠረጴዛ ላይም የተረጋገጠ ድል ነበረው፡፡

“ግዮን” መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 5 2018 ዓ.ም ገበያ የወጣዉ የአለባቸዉ ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)ሰለ ዓድዋ ያቀረበልልን መጣጥፍ የመጨረሻውን ክፍል ነገ ይዘን እንቀርባለን።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...