በሱዳን ኤል-ዳይን የማስተማሪያ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 13 ህጻናት፣ ሁለት ነርሶች እና አንድ ዶክተርን ጨምሮ 64 ሰዎች ሲገደሉ 89 ሰዎች መቁሰላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ።
የሱዳን ጦር አርብ፤ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ በምትገኘው እና በተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በተያዘችው ከተማ ውስጥ ትልቅ ሆስፒታል ላይ ጥቃት ፈጽሟል መባሉ አስተባብሏል።
ዶ/ር ቴድሮስ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “በቂ ደም ፈስሷል” ያሉ ሲሆን ሁሉም ወገኖች ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የተጀመረውን ግጭት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
አርኤስኤፍ እንደሚገልጸው፤ በምስራቅ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል-ዳይን በሚገኘው ሆስፒታል በድሮን የተመታው ሙስሊሞች የኢድ በዓልን ባከበሩበት ዕለት ነው።
ሱዳን በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 ወደ የእርስ በርስ ጦርነት የገባችው በወታደራዊ ኃይል እና አርኤስኤፍ መካከል በተፈጠረው የስልጣን የበላይነት የመያዝ ሽኩቻ ነው። ሁለቱም ቡድኖች በ2021 መፈንቅለ መንግሥት በጋራ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ይታወሳል።
በግጭቱ ምክንያት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
ኤል-ዳይን የማስተማሪያ ሆስፒታል አርብ ምሽቱ ጥቃት በኋላ ከአሁን ከሥራ ውጭ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፤ ተፋላሚ ኃይሎች የሕክምና ተቋማትን በተደጋጋሚ ዒላማ ማረድጋቸውን አውግዘዋል።
